Monday, August 31, 2015

አዎን አሸብሽቤአለሁ፣ አሁንም አሸበሽባለሁ!!!!!!!!!

ዲቮሽን 356/07፥ ማክሰኞ፥ ነሐሴ 26/07 ዓ/ም
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ) አዎን አሸብሽቤአለሁ፣ አሁንም አሸበሽባለሁ!!!!!!!!! እንዲያውም ከዚህ ይልቅ ራሴን በፊቱ ዝቅ አደርጋለሁ፣ ከዚህም የባሰ የተናቅሁ እሆናለሁ። 2 ሳሙ 6፡21 ዳዊት ነው ለሜልኮል እንዲህ ያላት። እኛስ ስንት ዓይነት ሜልኮሎች ዙሪያችንን ከብበውናል እኮ አላስተዋልንም እንጂ! ልብ ብንል በብዙ አእላፋት ሜልኮሎች ተከበናል። ገንዘባችን ሜልኮል ነው፣ ፎቃችን መኪናችን ሜልኮል ነው፣ ትምህርታችን ሜልኮል ነው፣ መንግሥታዊ ኃላፊነታችን ሜልኮል ነው፣ ዘመዶቻችን፣ ቤተሰቦቻችን ሜልኮሎች ናቸው፣ ውበት ደምግባታችን ሜልኮል ነው፣ ዝና ከበሬታችን ሜልኮል ነው፣ ጓደኞቻችን ሜልኮል ናቸው፣ አልፎ ተርፎም ልብሳችንም እኮ ሜልኮል ነው፣ (አያድርስ ነው መቼም፣ ለጥቂቶቻችን ደግሞ መንፈሳዊ አገልግሎታችንም ሜልኮል ነው::) ሰዎችም ቁሶችም አንዳቸውም እኮ ከብዙ ሞቶች አላዳኑንም። ግን እኛ እግዚአብሔርን ላመለክን እነሱ እንቅፋት ይሆኑብናል!!!!! ምቀኞች!!!!! ስለዚህ ሜልኮሎቻችንን ዛሬ እንዲህ እንላቸዋለን፡ "እናንተ ባለ ብዙ ጫፍ ተራሮች ሆይ፣ እግዚአብሔር ሊኖርበት የመረጠውን ተራራ፣ በእርግጥ እግዚአብሔር ለዘላለም የሚኖርበትን ተራራ ለምን በምቀኝነት ዓይን ታያላችሁ?" መዝ 68:16 እግዚአብሔርን ደግሞ እንዲህ እንለዋለን:: ዋይታዬን ወደ ሽብሸባ ለወጥህልኝ። ማቄን አውልቀህ ፍስሓን አለበስኸኝ። እንግዲህ ነፍሴ ታመስግንህ፣ ዝምም አትበል፣ እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፣ ለዘላለም አመሰግንሀለሁ። መዝ 30:11 --------- ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 10 ቀን ቀርቶታል

Sunday, August 30, 2015

ማልጄ እነሳለሁ!!!!

ዲቮሽን 355/07፥ ሰኞ፥ ነሐሴ 25/07 ዓ/ም (በእህት ማርታ ሲሳይነህ) ማልጄ እነሳለሁ!!!! በገናም መሰንቆም ተነሱ፤ እኔም ማልጄ እነሳለሁ። እግዚአብሔር ሆይ በሕዝብ መካከል እዘምርልሃለሁ። መዝ 108፡2 ታዲያ የሰላም እንቅልፍ ለሰጠን ለእግዚአብሔር ማለዳ ደግሞ እንነሳና እናመሰግነዋለን። አዲስ ዝማሬ እኮ ነው ሌሊት በአፋችን የጨመረው! ለፈዋሻችን፣ ለአዳኛችን፣ ነቀፌታችንን ላስወገደው ለእግዚአብሔር! ነፍሳችንን ከወህኒ ላወጣት፣ በተዘጋው ቤታችን ገብቶ ሰላም ለእናንተ ይሁን ብሎ ሰላሙን ላፈሰሰብን፣ መዋረዳችንን ላየው፣ እንባችንን ለዘላለም ላበሰው ለኢየሱስ! አዲስ ዝማሬ!!! ቀስቃሽ ሰው አንፈልግም አሁን! እስራታችን ተበጥሶ፣ ወጥመዱ ተሰብሮ እኛም አምልጠን በዓይናችን ያየን ሰዎች እኮ ነን! ስለዚህ ዛሬ የማንንም ፈቃድም፣ ይሁንታም አንፈልግም፣ ማልደን እንነሳለን! አዲስ መዝሙር፣ አዲስ ምስጋና እናቀርብለታለን! አሁን ለሃጢያት፣ ለእርኩሰት ጊዜ የለንም! አሁን መካኒቱ ሰባት ወልዳለች፣ እያልን ነው የምንዘምረው። ከፍ ከፍ ብሎ ከብሮአልና፣ ለእግዚአብሔር እዘምራለሁ፣ ፈረሱንና ፈረሰኛውን በባህር ውስጥ ጥሎአልና! እያልን እንዘምራለን። አሁን ለልቅሶ ጊዜ የለንም! ይልቅስ ነቀፌታዬን ከሰው መካከል ያስወግድልኝ ዘንድ ጌታ በተመለከተበት ወራት እንዲህ አድርጓልና፣ እያልን እንዘምራለን!!!! ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች፣ መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴት ታደርጋለች፣ የባሪያይቱን ውርደት ተመልክቷልና፣ ብርቱ የሆነ እርሱ በኔ ታላቅ ስራ አድርጎአልና፣ ስሙም ቅዱስ ነው፣ ምሕረቱም ለሚፈሩት እስከ ትውልድ ትውልድ ይኖራል እያልን። እንዘምራለን። ያልጠፋነው ከእግዚአብሔር ምሕረት የተነሳ ነው። ርኅራኄው አያልቅምና፣ ማለዳ ማለዳ አዲስ ነው፣ ታማኝነትህ ብዙ ነው። ሰቆ ኤር 3፡2 --------- ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 11 ቀን ቀርቶታል

Saturday, August 29, 2015

ተኛሁ፣ አንቀላፋሁ!!!!

ዲቮሽን 354/07፥ እሁድ፥ ነሐሴ 24/07 ዓ/ም
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)


ተኛሁ፣ አንቀላፋሁ!!!! እኔ ተኛሁ፣ አንቀላፋሁም እግዚአብሔር ደግፎኛልና ነቃሁ። መዝ 2፡5 ዳዊት ምንም የሚያስተኛ ነገር ሳይኖር እኮ ነው እንዲህ ያለው። ያውም መንግስትን ያህል ነገር በገዛ ልጁ ተነጥቆ በባዶ እግሩ እየተንከራተተ እኮ ነው፣ ለጥ ብሎ የተኛው! ያውቀዋላ! እግዚአብሔርን ማን መሆኑን ጥንቅቅ አድርጎ ያውቀዋላ! ሽብር እና ድንጋጤ ቢበዛም፣ የሚያባንን እና የሚያስቃዥ ነገር በዙሪያችን እያለ ለጥ አድርጎ የሰላም እንቅልፍ የሚሰጠን ጠባቂያችን እግዚአብሔር ብቻ ነው። ትጉህ እረኛ፣ አይተኛ አያንቀላፋ! አይደክመው አይታክተው! የእኛ እግዚአብሔር ከሁሉ በላይ ነው። ከሳኦልም ከአቤሴሌምም በላይ ነው። ከተቃዋሚዎቻችን ሁሉ በላይ ነው። እረ አንተ የሁሉ የበላይ ነህ እንበለው ወዳጆቼ!!! ሰይጣን እኮ የተጣለ ነው:: እንዴት ሰይጣንን፣ ሟርተኛን፣ ጠንቋይን፣ አስማተኛን ፈርተን ዓይናችን ፈጦ ያድራል! እንዴት በሽታን፣ ህመምን፣ ድህነትን ፈርተን ስንባንን እናድራለን! የስከዛሬው ይበቃቸዋል። ከሳሻችን የተጣለ የተወረወረ ነው!!!!! ስለዚህ በሰላም እንኖራለን፣ እንወጣለን እንገባለን፣ እንተኛለን። ተኝተን ራእይ እናያለን። ድንጋጤ፣ ፍርሐት፣ ቅዥት የሚባል የለም!!! ወንጌላችን ደግሞ አያረጅም፣ ፋሽን እኮ አይደለም አንድ ወቅት የምናምርበት ሌላ ጊዜ የሚያልፍበት!!! በሰላም እተኛለሁ፣ አንቀላፋለሁም፣ አቤቱ አንተ ብቻህን በእምነት አሳድረህኛልና። መዝ 4፡8 --------- ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 12 ቀን ቀርቶታል

Friday, August 28, 2015

እግዚአብሔር ይሔ ነው!!!!

ዲቮሽን 353/07፥ ቅዳሜ፥ ነሐሴ 23/07 ዓ/ም
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)



እግዚአብሔር ይሔ ነው!!!!


እነሆ አምላካችን ይህ ነው፤ በእርሱ ታመንን እሱም አዳነን። በማዳኑም ደስ ይበለን፤ ሐሴትም እናድርግ። ኢሳ 25፡9


እግዚአብሔር እንዲህ ነው! ዘርህ፣ ትምህርትህ፣ እድሜህ፣ ቀለምህ፣ አገርህ ምናምን አይልም። ይህ ነገርህ ስለተበላሸ ይህን ማድረግ አልችልም አይልም። አደራ ቢሰጠው እንደ ሰው አይረሳም። ወይ አይመቸኝም በጀትም ሆነ ፋሲሊቲ የለኝም አይልም።


በተዘጋ በር ላይ ሰላም ለእናንተ ብሎ መምጣት አያቅተው! ግን እንዴት ገባ? እያልን እንኳን መጠየቅ አንችልም። መቃብሩንስ ፈንቅሎ ተነስቶ አይደል እንዴ፤ ማን ድንጋዩን አነሳለት!


ሲናገር የእኛን አቋም እያየ አይደለም፣ እንኳን በሕይወት በአጸደ ስጋ እያለን፣ የእኛ ጌታ ኢየሱስ እኮ ለሞተው አልዓዛር ለተቀበረው፣ ለሸሸተው፣ 'አልዓዛር ተኝቷል' ብሎ፣ ሰው ከእንቅልፍ እንደሚቀሰቀስ ቀሰቀሰው።


በዚህ አላበቃም፣ የእኛን ጌታ ከቶ በምን እንመስለዋለን! ከቶ ከማንስ ጋር እናወዳድረዋለን! ለደረቁት አጥንቶችስ ቢሆን፣ ከመሽተት ከመግማት ላለፉት፣ ማንንም በጠረናቸው ለማይስቡት፣ የተራበ ቁራና የተራበ ጅብ እንኳን የማይፈልጋቸውን፣ እንጨት የሆኑ አጥንቶችን፣ 'በሕይወት ኑሩ' ብሎ ሲናገር ምንም አልሰጋም እኮ!!!


እረ በሱ ብቻ ተማመኑ! ሥጋ ለባሽ ሁሉ ከንቱ ነው! አብርሃምን እኮ፣ 'አንድ ብቻውን በሆነ ጊዜ ጠራሁት፣ ባረክሁት አበዛሁትም' ብሎ የተናገረውን ጌታ ነው የምናመልክ። ዘመን የማያነሳውን፣ ዘመን የማይጥለውን ኢየሱስን እኮ ነው እኮ የምንከተል። ሥንቱ ይወራ!!!!!


ስለዚህ ኑ፣ በእግዚአብሔር ደስ ይበለን! የትም ቦታ ሆነን በምንም ሁኔታ ሆነን፣ በቃ በእግዚአብሔር ደስ ይበለን።


እግዚአብሔር ፈራጃችን ነው። እግዚአብሔር ህግ ሰጪያችን ነው። እግዚአብሔር ንጉሳችን ነው። ኢሳ 33፡22

---------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 13
ቀን ቀርቶታል

Thursday, August 27, 2015

እግዚአብሔር ዓዋቂ ነው!!!!

ዲቮሽን 352/07፥ አር፥ ነሐሴ 22/07 ዓ/ም
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)


እግዚአብሔር ዓዋቂ ነው!!!!


እግዚአብሔር አዋቂ ነውና፣ እግዚአብሔር ሥራውን የሚመዝን ነውና:: 1ኛ ሳሙ 2:3


እንግዲህ እግዚአብሔር አዋቂ ነው ስንል ምን እያልን ነው? ከወር ከሁለት ወር በኋላ የሚሆነውን ያውቃል እያልን ነው? ወይስ ከተወለድን እንደምናድግ፣ ካደግንም ሥራ እንደምንይዝ፣ ስራ ከያዝንም እንደምናገባ፣ ካገባንም እንደምንወልድ ያውቃል ማለት ነው? ወይስ ከታመምን መድሃኒታችንን ባግባቡ ከወሰድን እንደምንድን ያውቃል ማለት ነው? ወይስ ጠዋት ተነሰቼ ቤተክርስትያን እንደምንሔድ ያውቃል ማለት ነው? ወይስ በፍርድ ቤት የያዝነውን ክርክር እንደምንረታ ያውቃል ማለት ነው? ወይስ ፈተናችንን በርትተን ካጠናን እንደምናልፍ ያውቃል ማለት ነው? አ-ይ-ደ-ለ-ም!!!


እግዚአብሔር አዋቂ ነው ስንል፡ ዓልፋ እና ዖሜጋ ነው ማለታችን ነው። የእኛን ብቻ አይደለም የመሠረታትን የዓለምን እና በውስጧ ያለውን ነገር አካሔድ ገና ጥንት ያውቀዋል ማለት ነው። እረ ገና እናትና አባታችን ሳይተዋወቁ፣ ሊጋቡም ሊዋለዱም ሳያስቡን እግዚአብሔር ያውቀናል!!! ስንቱን ልንገራችሁ! ብቻ በዚህች ዓእምሮአችን የእግዚአብሔርን አዋቂነት መተንተን አንችልም። ሞኝ ብቻ ነው ቸኩሎ፡ እግዚአብሔር የለም የሚለው። ሰነፍ ብቻ ነው፣ በአፉ ፈጥኖ እግዚአብሔር የለም እያለ በፊዚክስና እና በጂኦሜትሪ ሊያስቀምጥ የሚቸኩል!!!!



አልቃሻዋን ሐና ዘማሪ፣ ጭምቷን ሳራ ሳቂታ፣ ጨቅጫቃውን አብርሐም የብዙሃን አባት፣ ተጠራጣሪውን ዘካርያስ የመንገድ ጠራጊው አባት ያደረገውን እግዚአብሔር እንግዲህ በምን እንመስለዋለን!



ልቤ በእግዚአብሔር ጸና፣ ቀንዴ በእግዚአብሔር ከፍ ከፍ አለ፣ አፌ በጠላቶቼ ላይ ተከፈተ፤ በማዳንህ ደስ ብሎኛል።1ሳሙ 2፡1 --------- ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 14ቀን ቀርቶታል

Wednesday, August 26, 2015

ከድንቢጥ እንበልጣለን!!!!!

ዲቮሽን 351/07፥ ሐሙስ፥ ነሐሴ 21/07 ዓ/ም 
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)
ከድንቢጥ እንበልጣለን!!!!!
አትፍሩ፣ ከብዙ ድንቢጦች እናንተ ትበልጣላችሁ። ማቴ 10፡31
እግዚአብሔር ሁልጊዜ እየተጨነቅን ግራ ብናጋባው እኮ ነው፣ ቢያንስ ቢያንስ ከድንቢጥ ትበልጣላችሁ ያለን። ከአንበሳም፣ ከዝኆንም፣ ከነብርም አላወዳደረን እኮ! የምሕረቱ ልክ አልገባን ሲል፣ እንዲያው ስናሳዝነው፣ አንጀቱን ስንበላው ጊዜ፣ ቢጨንቀው እኮ ነው፣ አይ ልጆቼ፣ ቢጠፋ ቢጠፋ፣ ከድንቢጥ ትበልጣላችሁ ያለን!
እንዲያው ዋጋችሁ አታውቁትም? በደም መገዛታችሁን አታውቁትምን? በመስቀል ላይ የተሰቃየሁት ለማን ሆነና፣ መቼም ለድንቢጥ አይደለም እያለን እኮ ነው!
የሚስብ ውበት ወይም ግርማ ያልነበረኝ፣ ሰዎች እንዲወዱኝም የሚያደርግ መልክ ያልነበረኝ፣ በሰዎች የተናቅሁና የተጠላሁ፣ የሕማም ሰውና ስቃይ ያልተለየው የተባልኩ፣ ሰዎች ፊታቸውን ያዞሩብኝ፣ በእግዚእሔር እንደተመታ፣ እንደተቀሰፈ፣ እንደ ተሠቃየም የተቆጠርኩት፣ የተጨነቅሁት የተሰቃየሁት፣ እንደ ጠቦት ለዕርድ የተነዳሁት፣ አሟሟቴ ከክፉዎች ጋር የሆነ፣ ለማን ይመስላችኋል ሲለን እኮ ነው፣ አትፍሩ፣ ከብዙ ድንቢጦች እናንተ ትበልጣላችሁ፣ ብሎ እንደገና የሚያባብለን።
እኛ እምናመልከው እኮ፣ ከመቅደስ የሚበልጠውን፣ ከዮናስ የሚበልጠውን፣ ከሰሎሞንም የሚበልጠውን.... ኢየሱስን ነው!!!!
እግዚአብሔር እረኛዬ ነው፣ የሚያሳጣኝም የለም። መዝ 23:1
---------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 15 ቀን ቀርቶታል

መሠቃየታችን የእግዚአብሔር ፈቃድ ነበር!!!!!

ዲቮሽን 350/07፥ ረቡዕ፥ ነሐሴ 20/07 ዓ/ም 
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)
መሠቃየታችን የእግዚአብሔር ፈቃድ ነበር!!!!!
መድቀቁና መሰቃየቱ ግን የእግዚአብሔር ፈቃድ ነበር። ኢሳ 53፡ 10
እና ዛሬ ልላችሁ የምፈልገው፣ በመከራ መድቀቃችን እና መሰቃየታችን የእግዚአብሔር ፈቃድ ነበር ነው ልላችሁ የምወደው። በእርግጥ መከራን ያየ ሰው ምን ማለቴ እንደሆነ ያውቀዋል።
ስንንከራተት፣ ስንዋረድ፣ የሰው መሳቂያ እና መሳለቂያ ስንሆን፣ እኛም በሰቀቀን ሰውነታችን ሲያልቅ፣ አሄሄሄ! ስንቱን ልንገራችሁ.... አንድ አይዞህ ባይ ሲጠፋ፣ ሰውም እሰይ ክፋቱ አገኘው! እያለ አፉን ሲከፍትብን! ለምን መሰላችሁ? ብዙ ድል፣ ብዙ ምስጋና፣ ብዙ ዝማሬ ወደፊት ይጠብቀን ስለነበረ ነው።
እኛ ተራ ሰዎች ስላላይደለን፣ የሚገጥመን መከራም ተራ አይደለም። እግዚአብሔር ማንን እንደጣለ ይጥለናል? እስኪ እግዚአብሔርን የሚከስ ማነው? የት ላይ በቃሉ ሳይገኝ ቀረ! ስለዚህም እርሱ ብዙዎችን ይወርሳል፣ ከኃያላንም ጋር ምርኮን ይካፈላል። ኢሳ 53፡12 እንደተባለ፣ ውሎአችን ከኃያላን እና ከነገስታት ጋር ስለሆነ፣ የተጠራነውም ለዓለም ሁሉ ስለሆነ፣ ገና የብዙዎች መጠለያም ስለምንሆን እኮ ነው ድቅቅ ስቅይት ያልነው።
እንጅ ለሞትማ ቢሆን፣ ብዙዎች እኮ ሞተዋል!!! እኛም እንደ መድቀቃችን እና መሰቃየታችን ቢሆን ኖሮማ ድራሻችንም አይገኝ ነበር እኮ! ግን ይህን ያየነውን የዳሰስነውን፣ የቀመስነውን፣ የበላነውን ኢየሱስን ለዓለም ሁሉ ማዳረስ ስላለብን ነው ያ ሁሉ መከራ በእኛ ላይ የሆነው። እና ለዛሬዋ ቀን ሲል ነው እንዲህ መድቀቃችን እና መሰቃየታችን!!!!!!!
እግዚአብሔር የሠራት ቀን ይህች ናት፤ በእርስዋ ሐሤትን እናድርግ ደስም ይበለን። መዝ 118፡24
---------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 16 ቀን ቀርቶታል

Tuesday, August 25, 2015

በምድረበዳችን አፈራን!!!!!!

ዲቮሽን 349/07፥ ማክሰኞ፥ ነሐሴ 18/07 ዓ/ም 
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)

በምድረበዳችን አፈራን!!!!!!

እግዚአብሔር በመከራዬ አገር አፈራኝ። ዘፍ 41፡52

እንግዲህ እግዚአብሔር የኃይሉ ልክ ከሰው ዓእምሮ በላይ መሆኑን ሊያሳየን ተንቀሳቅሷል። እኛ አንዳንዴ እግዚአብሔርን ለሰው እንዳደረገው እንዲያደርግ ስለምንፈልግ የምንጠብቀውም ያንኑ ነው። እሱ ግን ምንም እንኳን ዓላማው አንድ ቢሆንም፣ እሱም እኛን ማዳን ሲሆን፤ አሰራሩ በራሱ ምርጫ ላይ ላይ የተመሠረተ ነው።
መከራችንን እግዚአብሔር አስረስቶ ዝም አላለም። አያልቅበት የእኛ ጌታ! ደግሞ አበዛን። ፍሬ አፈራን። ጠላታችን ሊገለን፣ሊያሳብደን፣ እስረኞችና ባሪያዎች አድርጎ ሊያስቀረን ነበር ወደ ምድረ በዳ የወሰደን። ከሰው ከዘመድ ነጥሎ፣ ከአማኞች ከወገናችን ሁሉ ነጣጥሎ፣ ጓደኞቻችንን ሁሉ ከእኛ አርቆ፣ አንድ ቀን በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ገብተን ራሳችንን እንድንጠላ ከዚያም ራሳችንን እንድናጠፋ ነበር ዓላማው። በዘላለም ፍቅር እንደተወደድን ያላወቀ ጅል!!!!!!
እኛ እኮ በዘላለም ፍቅር ተ-ወ-ደ-ና-ል። ገና ሳንወልድ፣ ገና ሳንጸነስ፣ ፍሬያማ እንድንሆን ተጠርተናል። ስለዚህ ኢየሱስ ሁሉንም ለበጎ አደረገልን። አሁንስ ጠፍተው ይሆናል እያሉ ሰዎች ሁሉ ሲጠብቁን ጭራሽ ተገኘን፣ ደርቀው ቀርተዋል እያሉ ሲያሟርቱብን እኛ ግን ለምልመን አረፍነው። አይገርምም ወገኖቼ?
በምድረበዳ ላይ ማፍራት የሚቻለው ከኢየሱስ ደም የተነሳ ብቻ ነው። እና በመከራችን አገር አፈራን። ኤፍሬም ሆነልን። እንግዲህ ክብር ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ እንሰጣለን እንጅ ሌላ ምን እንላለን!!!! አንድ ነጠላ ነበርን፣ ግን አልፈን ተርፈን አገር ሆንን! ዳርቻችን ሰፋ!
ሕዝብን አበዛህ፣ አቤቱ ሕዝብን አበዛህ፣ አንተም ተከበርህ፣ የአገሪቱንም ዳርቻ ሁሉ አሰፋህ። ኢሳ 26፡15
---------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 17 ቀን ቀርቶታል

ምናሴ ሆነልን!!!!!!

ዲቮሽን 348/07፥ ሰኞ፥ ነሐሴ 18/07 ዓ/ም 
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)

ምናሴ ሆነልን!!!!!!

እግዚአብሔር መከራዬንና የአባቴን ቤት አስረሳኝ። ዘፍ 41፡50
ያ ሁሉ ለቅሶ ያ ሁሉ የማይታለፍ የሚመስለው የመከራ መንገዳችን አለፈ። በየመንገዱ በየአደባባዩ ስናለቅስ በየቤተክርስትያኑ ስናለቅስ፣ በየጓደኞቻችን ስናለቅስ፣ የጌታ የማዳን ክንድ ወዴት ነው እያልን እንባችን እንደ ጎርፍ ሲፈስ .... በቃ ጌታ በቃ ሲለው ሃዘናችን አበቃ። ረሳነው። እግዚአብሔር አስረሳን።
የሚያድነን እና የሚታደገን ማነው? ወዴት ቤተክርስትያንስ ይኬዳል? እውነት የእግዚአብሔር ቃል ይሠራል ወይ እያልን የተንከራተትንበት ያ ጊዜ አለፈ። አሁን እኮ አንዳንዶቻችን የመከራችንን ዓይነት እንኳን በቅጡ አናስታውሰውም። ምናሴ ሆነልን።
አሁን ዮሴፍ ወንድሞቹ ሊገድሉት ሲማከሩ፣ ከዚያም ሲሸጡት፣ ከዚያም የጲጥፋራ አሽከር ሲሆን፣ ከዚያም ሲሾም፣ ከዚያም እሥር ቤት ሲወርድ፣ በእስር ቤት ላገኘው የመጠጥ አሳላፊ፣ ከዚህ እስር ቤት አስወጣኝ እያለ ሲማጸን፣ ሰውዬውም ሲረሳው፣ ...... አ..ቤ....ት... ስንት የጨለማ ጊዜ እኮ አለፈ!!!
እውነት በዚያን ጊዜ ዮሴፍ ስለራሱ ምን ይሰማው ይሆን? ያው ጠዋትና ማታ በሰው አገር ታሥሮ እንባውን ቁርስ ምሳና እራት አድርጎ፣ በትካዜ በጨለማ ቤት ሲቀመጥ... በግብጽ ምድር ላይ ኃላፊ፣ የንጉሥ አማች፣ የትውልዱ ተስፋ ይሆናል ብሎ ማን አመነ!!! ግን ይገርማል! ሆነ። በቃ ሆነ። ምክንያቱም መከራው የበዛበት እኮ ባለ ራእይ ስለነበረ ነው።
እና ዛሬ ምናሴ ሆነልን። መከራችንን እግዚአብሔር አስረሳን። ታዲያ ደስ አይልም-ወገኖቼ!!!!
የጻድቃን መከራቸው ብዙ ነው፣ እግዚአብሔር ግን ከሁሉ ያድናቸዋል። መዝ 34፡19
---------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 18 ቀን ቀርቶታል

ተሻገርን!!!

ዲቮሽን 347/07፥ እሁድ፥ ነሐሴ 17/07 ዓ/ም 
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)

ተሻገርን!!!

እነዚህማ በዚያ ስፍራ አይገኙም፤ የዳኑት ብቻ ይሄዳሉ። ኢሳ 35፡5
አይ ጠላት!!! የሞተ መሆኑን ራሱ በራሱ ጊዜ ማስመስከር ፈለገና፣ በሰረገላና በፈረስ ሆኖ ሊያሳድደን ጀመረ አይደል? እኛ፣ በጌታ መንፈስና እና ኃይል እንደምንንቀሳቀስ አላወቀ! የትኛው ቴክኖሎጂ እና ጥበብ ነው፣ ውሃን እንደ ግድግዳ ያቆመ! የትኛው አስማተኛና ጠንቋይ ነው ተከታዮቹን በውሃ ውስጥ ያስኬደው! የትኛው የሉሲፈር ጥበብ ነው በእሳት ውስጥ ጭፍሮቹ ሲያልፉ የታደጋቸው!
እኛማ ድነናል! ጠላት ይስማ! ድ-ነ-ና-ል!!! ኢየሱስ በመስቀል ላይ ኃጢያታችንን በደላችንን መከራችንን ሁሉ ተ-ፈ-ጸ-መ ብሎ አዲስ ሰው አድርጎናል።
ስለዚህ በውሃ ውስጥ እንሄዳለን፣ አንሰጥምም!! በእሳት ውስጥ እናልፋለን አንቃጠልም፣ ነበልባሉም አይፈጀንም!!!!
ለእኛ የተከፈተ መንገድ ለእኛ ብቻ ነው። ጠላትን አይመለከተውም።
አይ ጠላት ሞኙ፣ ደሞ ብሎ ብሎ አባታችን ለእኛ በከፈተው መንገድ ሊሄድ ያምረዋል? ምን ያለው ትእቢተኛ እና ክፉ ነው! ምንስ ያህል አመፀኛ ነው! ለነገሩ አንዴ ለጥፋት ስለተጻፈ፣ መከታተሉ አይቀርም። ምክንያቱም እግዚአብሔር የጠላታችን መታሰቢያው እስከማይገኝ ድረስ ነውና ድምጥማጡን ማጥፋት የሚፈልገው፣ ስለዚህም ዝም ይለዋል።
ዲያብሎስ ከነጭፍሮቹ ሰጠመ፣ እኛ ግን በደረቅ ተሻገርን። የፈርዖን ፈረሶች፣ ሰረገሎችና፣ ፈረሰኞች ተሰብስበው ሰጠሙ፣ እኛን ግን አምላካችን ውሃውን ግራና ቀኝ እንደግድግዳ አድርጎልን በደረቅ ባሕሩን ተሻገርን።
ዐይን ያላየውን፣ ጆሮ ያልሰማውን፣ የሰውም ልብ ያላሰበውን እግዚአብሔር ለሚወዱት አዘጋጅቷል። 1ቆሮ 2፡9
---------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 19 ቀን ቀርቶታል

Saturday, August 22, 2015

ዘፀአት ሆነልን!!!!!

ዲቮሽን 346/07፥ አርብ፥ ነሐሴ 16/07 ዓ/ም 
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)

ዘፀአት ሆነልን!!!!!

ልክ አራት መቶ ሠላሳው ዓመት በተፈጸመ ዕለት የእግዚአብሔር ሰራዊት ሁሉ ግብፅን ለቆ ወጣ። ዘፀ 12፡41
እፎይ፣ ነፃነታችን እኮ እውነት አይመስልም አይደል? ግን ሆነ።
እስከዛሬም የቆየነው የአምላካችን ልክ፣ ማንነት፣ ወርድና ስፋት፣ ለምድር ሁሉ መታወቅ ስላለበት፣ እንዲሁም የጠላቶቻችን በኩሮች ሁሉ መቀሰፍ ስላለባቸው ነው። እንጂ ግብፅን በዝብዘን እንደምንወጣማ የታወቀ ጉዳይ እኮ ነው!!! (ዘፀ 3፡22)።
ታዲያ፣ ዛሬ ዘፀአት ሆነልን!!
ያ፣ እግዚአብሔርን አላውቅም፣ እስራኤልንም አለቅም እያለ ሲፎክር የነበረው፣ ፈርዖናችን (እያንዳንችን እኮ ስንት ዓይነት ፈርዖንና ሠራዊቱ ሲገዛን ኖሯል! ዝርዝሩን እናንተ ሙሉበት) የኤልሻዳዩ ሰዓት ሲደርስ፣ እናንተ እስራኤላውያን ከሕዝቤ መካከል ውጡ! በጠየቃችሁት መሠረት እግዚአብሔርን አምልኩ ብሎ ጭራሽ ሸኘን እኮ!
ድሮስ፣ የእኛ ጌታ በኩር በኩሩን እያነቀ ቋ፣ ቋ፣ ቋ፣ ሲጥ ሲያደርግበት ወዶ ነው የሚለቀን! እኛም ዘመናችንን ሁሉ እግዚአብሔርን እናመልካለን። ልጆቻችን፣ የልጅ ልጆቻችንም ሁሉ ሲጠይቁን፣ “ከባርነት ምድር ከግብፅ እግዚአብሔር በሐያል ክንዱ አወጣን። ፈርዖን እኛን አለቅም ብሎ ልቡን ባደነደነ ጊዜ፣ ከሰው ጀምሮ እስከ እንስሳ ድረስ በኩር ሆኖ በግብፅ የተወለደውን ሁሉ እግዚአብሔር ገደለው።” እያልን እንመሰክራለን!!!
ዐይኖቼ የባልንጦቼን ውድቀት አዩ፣ ጆሮዎቼም የክፉ ጠላቶቼን ድቀት ሰሙ። መዝ 92:11
---------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 20 ቀን ቀርቶታል

በማትረፍረፍ የታወቀ!!!!

ዲቮሽን 345/07፥ አርብ፥ ነሐሴ 15/07 ዓ/ም 
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)

በማትረፍረፍ የታወቀ!!!!

ፊትህን አያለሁ ብዬ አላሰብሁም ነበር። እነሆም እግዚአብሔር ዘርህን ደግሞ አሳየኝ። ዘፍጥ 48፡ 11
የእኛ እግዚአብሔር በማትረፍረፍ የታወቀ ነው። የተትረፈረፈ ሰላም፣ የተትረፈረፈ ይቅርታና ምህረት፣ የተትረፈረፈ ባለጸግነት እና ሕይወት የሚገኘው በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ብቻ ነው።
ያዕቆብ፣ ስለ ሞተ ልጁ ሲያለቅስ ዓመታት ተቆጠሩ። ያ ብላቴናው ዮሴፍ ባይን ባይኑ እየሄደበት ብዙ ተክዟል። እንዲያው በቀበርኩት፣ ሬሳውን እንኩዋን ባየሁት እያለ! እንዲያው የልጄን ቀን በሰጠኝ እያለ ያዕቆብ ሲያለቅስ፣ ማስደነቅ የሚያውቀው የእኛ እግዚአብሔር ግን፣ በራሱ ሰዓት እና ጊዜ ከች አለ።
ያውም ዮሴፍ ሲመጣ መለመላውን ሆኖ አይደለም። ለተራበች ምድር ብቸኛ ተስፋ ሆኖ!!!! የልጁን ዓይን ብቻ ለማየት ምንም የተስፋ ጭላንጭል ያልነበረው ያዕቆብ፣ ዕልፍ ብሎ፣ የዮሴፍንም ልጆች አየ: ኤፍሬምና ምናሴን!!!!!!! እሥራኤል አያት ሆነ እኮ ነው እያልኩዋችሁ ያለሁት!!!!! እረ አለ ገና!!!!
ያዕቆብ የልጁን ሬሳ እንኩዋን ቢያገኝ ደስታው ወደር አልነበረውም። ደመ-ከልብ ሆኖ የቀረ መስሎት እኮ ነው በሀዘን ሲብሰለሰል የኖረው!!!! ወይም ደግሞ አካሉ ጎድሎ፣ ወይ ጎስቁሎ ቢመጣለት፣ እጅግ ይደሰት ነበር።
ሆኖም ግን.....
ዮሴፍ ባለፀጋ፣ ሀገረ ገዥ ሆኖ፣ አግብቶ ወልዶ፣ ተትረፍርፎ መጣ።
እግዚአብሔር ነዋ!!!!!!!
አንድ ሲጠየቅ አሥር እጥፍ አድርጎ በመስጠት የታወቀ የእኛ እግዚአብሔር ብቻ ነው። ኦ መንፈስ ቅዱስ ሆይ፣ እንዴት ግሩም ነህ!!!!!
እንግዲህ በእኛ እንደሚሠራው ኃይል መጠን ከምንለምነው ወይም ከምናስበው ሁሉ ይልቅ እጅግ አብልጦ ሊያደርግ ለሚቻለው (ኤፌ 3: 20) ለእግዚአብሔር አምልኮ እና ስግደት፣ ክብር ይገባዋል።
---------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 21 ቀን ቀርቶታል

ዮሴፍ በሕይወት አለ!!!!!!!

ዲቮሽን 344/07፥ ሐሙስ፥ ነሐሴ 14/07 ዓ/ም
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)

ዮሴፍ በሕይወት አለ!!!!!!!

ዮሴፍ የላከለትን ሠረገላዎች ሲያይ የአባታቸው የያዕቆብ መንፈስ ታደሰ። ከዚያም እስራኤል፣ “ልጄ ዮሴፍ በሕይወት አለ፣ ከመሞቴ በፊት ሂጄ ልየው”አለ። ዘፍ 45፡28

በጣም የምትፈልጉት ነገር ሞቷል ብሎ ጠላት መርዶ የነገራችሁ ምንድን ነው? ለመሞቱም ጠላት ምልክት በደም ነክሮ ያረጋገጠላችሁ ነገር ምንድነው? እናንተም ጌታ የተናገረኝ ነገር እንዴት ሳይሆን ቀረ እያላችሁ በስብራት ትኖራላችሁ አይደል? ነገሩ ትዝ ሲላችሁ ስታለቅሱ ስንት ዓመት ሆናችሁ ይሆን?

የሰማነው መርዶ ባለማረጋገጫ ስለሆነ፣ ይህማ የልጄ እጀ ጠባብ ነው፤ ክፉ አውሬ በልቶታል በእርግጥም ዮሴፍ ተበጫጭቆአል፣ እያልን ስንት ዓመታት አለፉ! ጠላትም ስብራታችንን እያየ ሲዘባነንብን፣ ብዙ ዓመታት ተቆጠሩ አይደል? በመጨረሻም፣ በሐዘን እንደተኮራመትን ወደ መቃብር እንወርዳለን ብለን ደመደምን አይደል! ስንት ውሸትን በማስረጃ እያስደገፈ ሲያስደንግጣችሁ እና ሲያባንናችሁ ኖረ አይደል!

አሁን አንገት የመድፊያው ጊዜ የጠላት እንጅ የእኛማ አይደለም! አሁን ጠላት ከነዘርማንዝሩ ለቅሶ ይቀመጥ፣ ምክንያቱም የተቀበረው የጠላት ልጅ እንጅ የእኛ ዮሴፍማ በሕይወት አለ። ዮሴፋችን በሕይወት አለ።

ዛሬ እግዚአብሔርን እንዲህ እንለዋለን፣
---------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 22 ቀን ቀርቶታል

ሮኆቦት ሆነልን!!!!!

ዲቮሽን 343/07፥ ረቡዕ፥ ነሐሴ 13/07 ዓ/ም 
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)

ሮኆቦት ሆነልን!!!!!

አሁን እግዚአብሔር ሰፊ ቦታ ሰጥቶናል፤ እኛም በምድር ላይ እንበዛለን። ዘፍጥረት 26፡22
ካንድ ቦታ ወደሌላው ስትፈናቀሉ፣ ካንድ ሥፍራ ወደ ሌላው ስትሔዱ፣ የያዛችሁት ሁሉ ብትን ብሎ ሲጠፋ ታለቅሳላቸሁ አይደል? የጀመራችሁት ነገር ዳር ሊደርስ ሲል ሲጨናገፍ፣ እናንተም ስታለቅሱ፣ ጠላትም ስታለቅሱለት፣ ዳዊት ጋ እንደፎከረው፣ “በእግዚአብሔር ተማምኖአል፣ እንግዲህ እርሱ ያድነው፣ ደስ የተሰኘበትን እስኪ ይታደገው” መዝ 22፡8 እያለ ይፎክርባችኋል አይደል? አይ ጠላት ሞኙ! ትንቢት እያወጣብን መሆኑን መች አወቀ! አላወቀም እንጅ እያንዳንዷ የእንባ ዘለላችን የጸሎት መስዋዕት ናት!
ብናለቅስስ? እናልቅሳ? ያለቀስነው እኮ ወደ አባታችን ነው። የተከራከርነው እኮ ከአባታችን ጋር ነው። ከንፈር መጦ ዝም ወደማይለው አባታችን እሪ ኡኡኡ ድረስልን ብለን ብናለቅስስ? እናለቅሳለን! ጠላት ምናገባው? እኛ ያለቀስነው፣ ባሕሩን ከፍሎ ወደሚያሻግረን አምላካችን! እኛ ያለቀስነው በምድረበዳ እንደ መንጋ ወደሚመራን አምላካችን! እኛ የምናለቅሰው ዐለቱን በምድረበዳ ሰንጥቆ እንደ ባሕር የበዛ ውሃ ወደሚያጠጣን አምላካችን፣ ምንጭ ከቋጥኝ አፍልቆ ውሃን እንደ ወንዝ ወደሚያወርደው አባታችን!
አሃ! አይ ጠላት! አልቃሻ እያለ ዝም ሊያሰኘን እኮ ነው! ነጭናጫ እያለ ሊወርሰን እኮ ነው! ሞኝ! እኛስ አንገኝም። ኤሴቅንም ጠላት ይውሰድ፣ ስጥናንም ለራሱ ያድርገው! እኛን የሚመጥነን ሮኆቦት ብቻ ነው። ምክንያቱም ብዙ ስለሆንን፣ ትንንሽ ነገር አ-ይ-መ-ጥ-ነ-ን-ም።
ወደ ሰፊ ስፍራም አወጣኝ፣ ደስ ተሰኝቶብኛልና አዳነኝ። መዝ 18፡19
-----
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 23 ቀን ቀርቶታል

ጌታ ነዋ!!!!!!

ዲቮሽን 342/07፥ ማክሰኞ፥ ነሐሴ 12/07 ዓ/ም 
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)

ጌታ ነዋ!!!!!!

ስለዚህ እንደሞተ ሰው ከሚቆጠር ከዚህ ከአንድ ሰው፣ እንደ ሰማይ ከዋክብት የበዛና እንደ ባህር ዳር አሸዋ ተቆጥሮ የማያልቅ ዘር ተገኘ። ዕብ 11፡12

የአብርሐም የአንድ ልጅ ጥያቄ ለዘመናት ከእግዚአብሔር ጋር ሲያጨቃጭቀው ቆይቷል። አይ እግዚአብሔር! እንዴት ድንቅ ነው! ዔሊኤዘር ይወርሰኛል እያለ ሲፈራ የነበረው አብርሐም፣ የትውልድ ሁሉ አባት ለመሆን በቃ። ተረት አይመስልም? ግን እውነት ነው!

እግዚአብሔር እንዲህ ነዋ! እግዚአብሔርን ምንም ነገር አያስፈራውም። ሳይንስ አያስፈራውም፣ እድሜ አያስፈራውም፣ መልክዓምድራዊ አቀማመጥ አያስፈራውም፣ ሞት አያስፈራውም፣ መንግስታት አያስፈሩትም፣ ..እሱ ግን ሥራውን በራሱ ጊዜ ይሠራል! ከለመንነውም ከጠየቅነውም በላይ ማድረግ ይችላል።

ታዲያ ዛሬ በሰውም በእናንተም ዓይን የሞተው ነገር ምንድን ነው? የተቀበረውስ አልአዛር የትኛው ነው? እግዚአብሔር እልፍ ያለ ነገር በእያንዳንዳችን ሕይወት ላይ አይቷል። መንፈስቅዱስን ዝም ብላችሁ አመስግኑት። እወድሐለሁ በሉት።

አምላክ ሆይ፣ ለእኔ ያለህ ሐሳብ እንዴት ክቡር ነው። ቁጥራቸውስ እንደምን በዛ! ብቆጥራቸው ከአሸዋ ይልቅ ይበዛሉ። መዝ 139፡17
---------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 24 ቀን ቀርቶታል

Monday, August 17, 2015

ትልቅ ለማኙ /Asker of Big

ዲቮሽን 341/07፥ ሰኞ፥ ነሐሴ 11/07 ዓ/ም 
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)

ትልቅ ለማኙ /Asker of Big

ለምነኝ መንግስታትን ለርስትህ፣ የምድርንም ዳርቻ ግዛት እንዲሆንህ እሰጥሀለሁ። መዝ 2፡8

ህፃን ልጅ አባቱ/እናቱ ሁሉን ማድረግ የሚችሉ ነው የሚመስለው። ስለዚህ ሲጠይቅ አይሳቀቅም። ወላጆቼ ገንዘብ ወይ ዓቅም ላይኖራቸው ይችላል ብሎ አያስብም። የፈለገውን ይጠይቃል። ያምናቸዋል፤ ይመካባቸዋል። ይኮራባቸዋል።

የእኛ እግዚአብሔርስ?

አሁን እግዚአብሔርን አይተነዋል። ቀምሰነዋል። ዳስሰነዋል። አይደለም እንዴ?

ታዲያ ጥያቄያችንም ልክ እንዳየው ሰው ነው። አሁን ደጀሰላም ላይ ተቀምጠን ምጽዋትን አንለምንም። አሁን አሥር እና አምስት ሳንቲም ብቻ አንለምንም። አሁን ከህመማችን ብቻ እንዲፈውሰን አንለምንም። አሁን ከኤኮኖሚ ድህነት ብቻ ነጻ እንድንወጣ አንለምንም። አሁን የትዳር አጋር ብቻ አንለምንም። አሁን መኖሪያ ቤት ወይ መሰል ነገር ብቻ አንጠይቅም።

አሁን ልመናችን ተቀይሯል። ዋናውን አግኝተነዋላ!!!! እሱም እኮ፡ ለምነኝ መንግስታትን ለርስትህ፣ የምድርንም ዳርቻ ለግዛትህ እሰጥሀለሁ ብሎናል። ስለዚህ It is time to exercise our child right. ቀላል እንለምናለን እንዴ?! እንጮሀለን እንጂ!! እ--ን--ለ--ም--ና--ለ--ን!! አህዛብን ለቤተክርስትያን፣ የምድርንም ዳርቻ ለግዛታችን የሚሰጠውን፡ እሱን እግዚአብሔርን እንለምናለን። አናቋርጥም። እንጮሐለን!! ሰጭውን ላልከበደው፣ እኛን ለማኞቹን ምን አሳቀቀን ወገኖቼ? በተራው እዚያው ጠላታችን ይሳቀቅ እንጂ!!

ዋ! ኋላ መንግስተ ሰማያት ላይ ሔዳችሁ ከመቆጨት፣ ይሔ ሁሉ ለኔ ነበር እንዴ? ከማለት፣ ዛሬ የምትፈልጉትን ሁሉ በስሙ ጠይቁ።

ለተቀበሉት ሁሉ ግን፣ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው። ዮሐ 1፡12
---------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 25 ቀን ቀርቶታል

Sunday, August 16, 2015

ጵኒኤል ሆነልን!!!




ዲቮሽን 340/07፥ እሁድ፥ ነሐሴ 10/07 ዓ/ም 
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)

ጵኒኤል ሆነልን!!!

እግዚአብሔርን ፊት ለፊት አየሁት፣ ሰውነቴም ድና ቀረች። ዘፍ፡ 32፤30

እንግዲህ ጨዋታችን ከፍ ብሏል። ወጋችን ተቀይሯል። አሁን ዋናውን አገኘን። እነ ሎጥን ተለማምጠን ስናስወግድ፣ እነ ላባን እግሬ አውጭኝ ብለን ስናመልጥ፣ እነ ዔሳውን እዛው በሩቁ ብለን ስናርቃቸው፣ ቋንቋችን ሁሉ ተቀየረ። አልፈን ተርፈን ከእግዚአብሔር ጋር እኩል ማውራት ጀመርን። እረ መታገልም ጀመርን። ሪስሊንግ ነገር ሞካከርን!!!!

በሰው ልማድ ቀረ፣ የሚለው ቃል አሉታዊ ነው። እከሌ እንዴት ሆነ? ሲባል፣ ታሞ ቀረ፣ ወይም ድሃ ሆኖ ቀረ፣ ጎስቁሎ ቀረ። ሳይሆንለት ቀረ። ወ.ዘ.ተ. ነው የሚባለው።

አሁን ግን እኛ ድነን ቀረን። ቡቱቱ ኮልኮሌያችን ጋር መጓተት ስናቆም፣ በቃ እግዚአብሔርን ፊት ለፊት አገኘነው። እሱም ቁርጠኛ መሆናችንን ፈተነን፤ የወዳጅ ትግል ታገለን።

እውነት ወስናችሁ ከሎጥ ተለያችሁ? ከላባስ የምር ኮበለላችሁ? ዔሳውንስ ሸኛችሁት፣ አለና እንግዲያማ፣ አሁን ሌላ ስም ይውጣላችሁ ብሎ፡ እስራኤል ተባልን።

አሁን ጠላት ቢፈልገን መታወቂያችን ስለተቀየረ ጎረቤትን ሁሉ አይታችኋል ቢባሉ፣ አንገኝም። ምክንያቱም የጥንቱ ስማችን ተቀየረ። በድሮ ስማችን አገር ቢታሰስ የለንም፣ አንገኝም። ስም ከሰማይ ወጥቶልናል። ናፍቆታችንን አገኘነውና በሁሉም አቅጣጫ ድነን ቀረን። ጵኒኤል ሆነልን!!!!!

ሁልጊዜ እግዚአብሔርን በፊቴ አየዋለሁ፤ በቀኜ ነውና አልታወክም። ስለዚህ ልቤን ደስ አለው። ምላሴም ሐሤት አደረገች። ሥጋዬም ያለ ሥጋት ዐርፎ ይቀመጣል። መዝ 16፡8-9
---------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 26 ቀን ቀርቶታል

Saturday, August 15, 2015

ጨዋታችን ተቀየረ!!!!!

ዲቮሽን 339/07፥ ቅዳሜ፥ ነሐሴ 9/07 ዓ/ም
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)
ጨዋታችን ተቀየረ!!!!!
ያዕቆብም ደግሞ ጉዞውን ቀጠለ፣ የእግዚአብሔርም መላእክት ተገናኙት። ዘፍ 32፡1
መቼም ሰውና ሰው ሲገናኝ እና ሰውና መልአክ ሲገናኝ ጨዋታው አንድ አይነት አይሆንም። ከአጎቴ ላባ ቤት እኮ ባዶ እጃችንን አልወጣንም፤ መሰለን እንጂ።
ብዙ ነገር በዝብዘን፣ ማርከን፣ ተትረፍርፈን ወጣን። አሁን ጠረናችን መላእክትን መሳብ ጀመረ። አሁን እንቅፋት የሚሆኑ ሰዎች ሳይሆኑ፣ አሁን መላእክትን በአካል ማየት ጀመርን። መዓዛችን ተቀየራ!!!!
አጎቴ ላባ ከመሔዱ አፍታም ሳይቆዩ የመላእክት መምጣት አይገርማችሁም!! በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ሁሉ ስላንተ ያዛቸዋልና። መዝ 91:11 This is entirely a divine design.
በመንገድ ስንሔድ አሳዳጅ አይደለም ያኘነው-መላእክትን ነው። ምን ምን አሏችሁ? ምን ምን አጫወቷችሁ? ምን ምስጢር ነገሯችሁ? ምን መልእክት አመጡላችሁ? ጉድ ነው መቼም! እንዴት ታድለናል! መላእክቱን ስለእኛ የሚያዝ እግዚአብሔር ይባረክ!!!!! አሜን!!!!!
አሁን እናት አይመክረን አባት፣ እህት አይመክረን ወንድም፣ አጎታችን ላባ አያስፈራራን፣ ያ ሊገድለን ቀን ቀጠሮ ይዞ የነበረው ወንድማችን ዔሳው ጦር አይሰብቅብን። መላእክትን አግኝተናላ!!!!
እራሳቸው መላእክት ተልከው መጡልን---- በአካል አየናቸው!!!! ታድለን!!!! እፎይ!!!!!!!
በቃ ተለወጥን! እንዴት ግሩም ነገር ነው! ገና ከእናታችን ማህፀን ሳንወጣ እኮ ነው ትንቢት የተጀመረው። ጉዞ ወደ ቃልኪዳናችን........... ደስ ሲል!
ታዲያ እንዳትዘናጉ፣ ከአጎቴ ላባ ጋር ተሳስመን እንደተለያየነው ሁሉ ከወንድሜ ዔሳው ጋርም እንዲሁ አድርጉ። እሽ??? አደራችሁን፣ ምንም መዳበል የሚባል ኑሮ የለም!!!!!!
እዛው በሩቁ፣ እሽ??? አደራ!!! አጎቴ ላባ ወደ አገሩ እንደተመለሰው ሁሉ፣ ወንድሜ ዔሳውም ወደ አገሩ በሰላም ይመለስ። ደባል አንፈልግም!!!! እንደገና ጭቅጭቅ ውስጥማ አንገባም!!!! ስንት ስራ የሚጠብቀን ሰዎች እኮ ነን!
ከዚያም ዲያብሎስ ትቶት ሄደ፣ መላእክትም አገለገሉት። ማቴ 3:11
---------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 27 ቀን ቀርቶታል

አጎቴ ላባ ስሞኝ ተመለሰ!!!

ዲቮሽን 338/07፥ አርብ፥ ነሐሴ 8/07 ዓ/ም
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)
አጎቴ ላባ ስሞኝ ተመለሰ!!!
በማግስቱም ላባ የልጅ ልጆቹን እንዲሁም ሴቶች ልጆቹን ስሞ መረቃቸው፤ ከዚያም ወደ አገሩ ተመለሰ። ዘፍ 31፡55
ያዕቆብ ለአጎቱ ለላባ በታማኝነት ሲገዛለት ኖረ። ላባም ሳያስበው አሪፍ ባሪያ አገኘ። “አንተማ የዐጥንቴ ፍላጭ የሥጋዬ ቁራጭ ነህ” እያለ፣ እያሞካሸው ለዓመታት ገዛው። ዘፍጥረት 13፡14
በኋላ በስተመጨረሻ ግን እግዚአብሔር በቃ ሲል፣ ያዕቆብ ኮበለለ። ለካስ ለገዥዎችም ገዥ አለ!!!!
ላባስ ከእንግዲህ ምን ስልጣን አለው!? ትንሽ ማንኮሻኮሽ መፍጠሩ ግን አልቀረም። አንዴ ሳትሰናበቱኝ ምነው? እያለ (አዛኝ ቅቤ አንጓች!!!!)፣ አንዴ አምላኮቼን ሰርቃችኋል እያለ (ጉድ ነው መቼም የሚሰረቅ አምላክ!!!!)፣ አንዴ ከፈለኩኝ ልጎዳህ እችላለሁ እያለ (አይሞክረውም ነበር፣ ድሮስ አዝኖለት ነው!!!!!) እንደ እብድ አስር ነገር ሲለፈልፍ ቆየና፣ ሀቁን አፈረጠው። "አምላካችሁ ያዕቆብን ደግም ክፉም እንዳትናገረው ብሎ አስጠነቀቀኝ" ብሎ እውነቱን ተናገረ!!!!! እሰይ የእኛ እግዚአብሄር!!!!
ከዚያም የልጅ ልጆቹን እንዲሁም ሴቶች ልጆቹን ስሞ መረቃቸው፤ ከዚያም ወደ አገሩ ተመለሰ። ዘፍ 31፡55።
ሲችል እያስፈራራ እያንገራገረ፣ ሳይችል እያባበለ፣ ሲገዛው የኖረውን ላባ፣ ያዕቆብ ለዘላለም ተገላገለው!!!!!!
ከዚያስ? ከዚያማ፣ ያዕቆብ ጉዞውን ቀጠለ። (32:1) እሰይ!!!!!!!!
ቁርስና ምሳ እየሰጡ ዘላለም ሊገዙን የወደዱ አጎቶቻችን ላባዎች ምንም ምርጫ ስለሌላቸው፣ ትእዛዝ ከሰማይ ስለወጣባቸው፣ ሲፈልጉ መርቀውን ሲፈልጉ ረግመውን ዛሬ ሔዱ። መሸሸጊያ ይሆኑናል፣ ያልናቸው አጎቶቻችን ላባዎች፣ መማጸኛ ይሆኑናል ብለን ሲገዙን የኖሩት ሁሉ፣ ዛሬ እየሳሙን ወደ አገራቸው ተመለሱ።
ዛሬ፣ ለዘመናት እንደ ላባ አጎት የሆኑባችሁ ሁሉ፣ ለዘላለም ሔደዋል።
አጎቴ ላባ ስሞኝ ተመለሰ!!! (Uncle Laba kissed me & departed from me FOREVER & returned to his place)
ያልኩት ገብቷችኋል? ከዚያስ?፣ ከዚያማ እንደ ያዕቆብ ጉዞአችንን ቀጠልና!!! ጉዞ እግዚአብሔር ወደ አየልን……..
ነገርን ሁሉ በጊዜው ውብ አድርጎ ሰራው። መክ 3:11
ማን?
ኢ-----የ-----ሱ-----ስ።
---------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 28 ቀን ቀርቶታል

ኃያላን ወደቁ!!!!

ዲቮሽን 337/07፥ ሐሙስ፥ ነሐሴ 7/07 ዓ/ም
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)
ኃያላን ወደቁ!!!!
ኃያላን እንዴት ወደቁ!? 2ኛ ሳሙ 1፤19
ስለጀግንነታቸው ምናልባት ሌሎች ሰዎች ከሚያውቋቸው በበለጠ፣ ሌሎች ወታደሮችና አብረዋቸው የሚኖሩ ሠራዊቶቻቸው ከሚያውቋቸው በላይ፣ ዳዊት ሳኦልንና ዮናታንን ይበልጥ ያውቃቸዋል። ሐያልነታቸው እስከምን እንደሆነ ከሌሎች እስራኤላውያን በተሻለ ዳዊት ልቅም እድርጎ ይገባዋል። እንዲያ ሲያርበደብዱት፣ በረሐ ለበረሐ ሲያስለቅሱት፣ ሲያስርቡት እና ሲያስጠሙት፣ ሲያንከራትቱት የነበሩትን እነዚህን ሁለት ሰዎች ዳዊት በደንብ አድርጎ የጀግነታቸውን ልክ ያውቀዋል።
ለካስ ሁሉም ልክ አለውና ጀግናም፣ ይወድቃል!!! ማመን ቢያቅተው ዳዊት እንዲህ አለ፤ ኃያላን እንዴት ወደቁ? 2ኛ ሳሙ 1፤19
እኛስ አሁን እያርበደበዱን፣ እያስደነገጡን፣ እያሳቀቁን ያሉ ስንት ጀግና የሆኑ፣ ሀጢያቶች፣ ልማዶች፣ ወጎች፣ እውቀቶች የሉም ብላችሁ ነው? መቼስ እንደ አቅም አቅማችን እኮ ብዙ ዓይነት ኃያላን፣ ሲያስጨንቁን እና ሲያሳድዱን አልኖሩም ብላችሁ ነው? አንዴ ኃጢአት ሲጀግንብን፣ አንዴ በሽታ ሲጀግንብን፣ አንዴ ሞት ሲጀግንብን፣ አንዴ ችግር ሲጀግንብን አልኖረም ብላችሁ ነው?
ግን ለኃያላንም የገዙበት ጊዜ በቃቸውና፣ ወደቁ። በቃ ወደቁ።።።።።።።። ምንም ማድረግ አይቻልም፡ ወ----ደ-----ቁ።።።።።። የኃያላን ሁሉ ኃያል ኢየሱስ መጣባቸዋ!!!
እግዚአብሔር የጽዮንን ምርኮ በመለሰ ጊዜ ሕልም እንጅ እውን አልመሰለንም ነበር። በዚያን ጊዜ አፋችን በሣቅ፣ አንደበታችንም በእልልታ ተሞላ። በዚያን ጊዜም በህዝቦች መካከል እግዚአብሔር ታላቅ ነገር አደረገላቸው ተባለ። እግዚአብሔር ታላቅ ነገር አደረገልን፤ እኛም ደስ አለን። መዝ 126: 1 አ---ሜ----ን።
---------ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 29 ቀን ቀርቶታል

ምድረበዳየን ወደድኩት!!!!

ዲቮሽን 336/07፥ ረቡዕ፥ ነሐሴ 6/07 ዓ/ም
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)
ምድረበዳየን ወደድኩት!!!!
ከሕዝብ ግርግር አወጣኸኝ፣ የሕዝቦች መሪ አድርገህ አስቀመጥኸኝ። መዝ 18፡43
በመከራ እያለፋችሁ ይሆን?
እግዚአብሔር ለእኛም ሆነ ለሰው ደስ የማይሉ የሕይወት መንገዶቻችንን እንዴት አድርጎ እንደሆነ ሳይታወቅ፣ ወደ መልካም ይለውጠዋል።
ድቅድቁን ጭለማ፣ ምንም ተስፋ የማይታይበት መንገዳችንን እግዚአብሔር ለሹመት ያደርገዋል።
ለካስ እኛ እያለቀስን፣ ለካስ እኛ እየከፋን የንግሥና ትምሕርት ቤት ገብተን ነው። ለዚያ እኮ ነው እግዚአብሔር ዝም የሚለው። ነገ የሚያደርግልልንን ስላየ፣ አይ ልጆቼ ያዘጋጀሁላችሁን ብታውቁ እኮ ያሁኑ ጨለማ እንደ ንጋት ፀሐይ ይሆንላችሁ ነበር እያለ፣ የእኛ ኢየሱስ ዝምምም ይላል።
ሰዎች ሲንቁን፣ ሲሰድቡን፣ ስንታመም፣ ስንሳቀቅ፣ ስንሸማቀቅ፣ የሚያጽናና ሲጠፋ፣ ሰው ፍለጋ ስንንከራተት ዓይናችን በእንባ ሲታጠብ---- ምስጢሩ እኮ፡ የንግስና ትምህርት ቤት ገብተን ነው።
እንዴ! እሱ እግዚአብሔር ነዋ! ሕይወታችን በመከራ እየተቀመመ ሙሉ ሰው ሊወጣን እኮ ነው።
እና ዛሬ "እግዚአብሔር ሆይ ምድረበዳየን እወደዋለሁ። ስለምድረበዳየ አመሰግንሃለሁ" ብንለውስ?
ግዴላችሁም፣ እንበል። አስደናቂ ነገር ከፊታችን ስላለ እኮ ነው! ገባችሁ ያልኩዋችሁ? በሁሉም አቅጣጫ ሙሉ ሆነን ልንገለጥ እኮ ነው! ባለሙሉ ስልጣን የክርስቶስ እንደራሴ ልንሆን ነው እኮ!!!
አባብላታለሁ፥ ወደ ምድረ በዳም አመጣታለሁ፥ ለልብዋም እናገራለሁ። ከዚያም የወይን ቦታዋን፥ የተስፋ በርም እንዲሆንላት የአኮርን ሸለቆ እሰጣታለሁ፤ በዚያም ከግብጽ ምድር እንደ ወጣችበት ቀን እንደ ሕፃንነትዋ ወራት ትዘምራለች። ሆሴዕ 2:16
---------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 30 ቀን ቀርቶታል

Monday, August 10, 2015

ሙሉ በሙሉ አዲስ /Brand New/!!!!!

ዲቮሽን 335/07፥ ማክሰኞ፥ ነሐሴ 5/07 ዓ/ም 
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)


ሙሉ በሙሉ አዲስ /Brand New/!!!!!


ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል። 2ኛ ቆሮ 5፡17


በቤተክርስትያን ውስጥ እያለን፣ የእግዚአብሔርን ቃል እያወቅን፣ በዚያ በገባን እና በተረዳነው ልክ እንዳንመላለስ ብዙ እንቅፋቶች አሉብን። አንዱና ዋናው ዓእምሮአችን ነው። ይህ ዓእምሮአችን የማያስታውሰው ነገር ስለሌለ፣ በተለይ ክፉ ክፉ ገጠመኞቻችንን ከትቦ ስለሚያስቀር፣ የሕይወት እርምጃችን በመንፈስ ሳይሆን በስጋ እንዲሆን ይጫነዋል።


ለዚህም ነው፣ “እኔ እንዲህ ሆኜ የቀረሁት የሙት ልጅ ስለሆንኩ ነው፣ ቤተሰቤ በመጥፎ አስተዳደግ ስላሳደገኝ ነው፣ እናቴ ወይም አባቴ ጥቃት ስላደረሱብኝ ነው፣ በቂ የቀለም ትምህርት ስላላገኘሁ ነው፣ እልም ያለች ገጠር ውስጥ ስላደግሁ፣ ወይም በፈረንጅ አገር ስለኖርኩ ወ ዘ ተ ... እንላለን።


ተመልሰን ወደ ኃጢአት ስንገባም፣ ክርስቶስን ደስ የሚያሰኘውን ሕይወት መኖር ያቃተኝ፣ እንዲህ እና እንዲያ ስለሆንኩ ነው፣ እንዲህ ባይሆን ኖሮ እንዲህ አይሆንብኝም ነበር.... የሚሉ ልብን የሚያዝሉ ነገሮች ከአፋችን እናወጣለን። የምንናገረው ነገር እውነትነት ሊኖረውም ላይኖረውም ይችላል።


ሰይጣንም ይችን የኛን ደካማ ተፈጥሮ እንደ መልካም አጋጣሚ እየተጠቀመ፣ እስረኞች አድርጎን ሊኖር ይፈልጋል። ሞኙን ይፈልግ!!!!!


ዛሬ ሰይጣንን ከነ ሰበባ ሰበቡ ቻው ቻው እንለዋለን። አእምሮን ሁሉ ከአሁን ሰዓት ጀምሮ ለክርስቶስ እንማርካለን።
እኔ የኢየሱስን ምልክት በሥጋዬ ተሸክሜአለሁና፣ ከእንግዲህ ወዲህ ማንም አያስቸግረኝ። ገላትያ 6፡17 እናንተስ ወገኖቼ?


---------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 31 ቀን ቀርቶታል