Friday, August 7, 2015

ተስፋዎቻችን!!!

ዲቮሽን 329/07፥ አርብ፥ ነሐሴ 1/07 ዓ/ም
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)



ተስፋዎቻችን!!!

አንተ ለምድር ዳርቻ ሁሉ፣ በርቀት ላለውም ባሕር ተስፋ ነህ። መዝ 65:5

መቼም ይህ ድብልቅልቁ የወጣበት ዘመን፣ ከእግዚአብሔር ይልቅ ብዙ ሌሎች 'ተስፋዎቻችንንና እና ረዳቶቻችንን' እያስቆጠረን ነው። በአይነትም በብዛትም እጅግ በርካታ ስለሆኑ እነሱን ሁሉ እዚህ መጥቀስ አይቻልም። እኔም እናንተም እናውቃቸዋለን እኮ!!!! ለቁጥር የሚያዳግቱ 'ረዳቶቻችን እና ተስፋዎቻችን' በዙሪያችን አሉ።

እንዲያው እነዚህ የተደገፍናቸው ነገሮች ሸንበቆ ሲሆኑብን፣ “የሚረዳኝ የለምና ከእኔ አትራቅ፣ አሁንስ ተስፋዬ ማነው? እግዚአብሔር አይደለምን?፣ ወይም በሰው ከመደገፍ በእግዚአብሔር መደገፍ ይሻላል፣ ወ.ዘ.ተ. የሚሉ እንጉርጉሮ አዘል ጥቅሶችን ለይምሰል ያህል እንጠቀማለን።

ግን ሕይወታችን እኮ የሚቀናበረው እግዚአብሔር እንዳለው ነው እንጅ፣ በደገፋዎቻችንን ብዛት እንዳልሆነ የየግል ሕይወታችን ምስክር ነው። ስንቱ የተደገፍንበት መንገድ ላይ እየቀረ እኮ ባላስልጣኑ ኢየሱስ ብቻ ዛሬም ነገም ለዘላለምም ከእኛ ጋር ይዘልቃል።

ስለዚህ፣ ለምን አንጨክንም? እግዚአብሔርን ከረዳቶቻችን እንደ አንዱ ለምን እናየዋለን? ከመታመኛዎቻችን እንደ አንዱስ ለምን እንቆጥረዋለን? ከተስፋዎቻችንስ እንደ አንዱ ለምን ይሆናል?

ኧረ ተስፋ ያልነውን ነገር ሁሉ ዛሬ እግዚአብሔር ያስጥለንና፣ በውሃው ላይ መራመድ ይሁንልን!

ከአብርሃም ጋር ያደረገውን ኪዳን፣ ለይስሐቅም በመሐላ የተሰጠውን ተስፋ አይረሳም። መዝ 105:9
አባትዬ እባክህ ብቻህን በሕይወታችን ላይ ታይ። አንተን ብቻ መታመን ይሁንልን? ሰምተህኛልና ተባረክልኝ።
---------
እለታዊ ዲቮሽኑ ሊጠናቀቅ 35 ቀን ቀረው

“ ሕይወት ግልጽ ናት ”

ዲቮሽን 330 / 07 ሓሙስ ሓምሌ 30/07
( ወንድም ጌታሁን ሓለፎም )


“ ሕይወት ግልጽ ናት ”

“ ሕይወትም ተገለጠ አይተንማል እንመሰክርማለን ፤ከአብ ዘንድ የነበረውንም ለእኛም የተገለጠውንም የዘላለምን ሕይወት እናወራላችኋለን ” 1ኛ ዮሓ 1፡-2

እርግጥ ነው ! እውነተኛውን የመለኮት ፍቅር የቀመሰና ያጣጣመ ፤ የጌታን ቸርነት እና እርህራሔ ያየና የተረዳ ፤ ህያው የሆነውን ሰማያዊ ድምጹን የሰማ ፤ በአምሳሉ የተፈጠረ የስው ልጅ ይቅር እና ጉእዛን ብለን የምንጠራቸው ተራሮች እና ወንዞች እንኳን ሳይቀሩ ስለ እግዚአብሔር አምላክነት ያወራሉ ፤ ስለ ጌትነቱ ይዘምራሉ ስለ ሁሉን ቻይነቱ እልል ይላሉ ። ያውቁታልና !

በአብ ዘንድ ለዘመናት ተሰውሮ የበበረው የዘላለም ሕይወት በመሲሁ በኩል ለሰው ልጆች ዘላለማዊ ደህንነት ተገልጧልና እየተደነቅን እየተገረምን የማዳኑን የምስራች እንናገራለን ፤ አዎ የምስራቹ ይዘመራል ፤ ይሰበካል ፤ እንደ እብድ ይጮሓል ቃላችንም ምድሪቷን ይከድናል ! ዝም ማለት አይቻለንም !

ይሔ የተገለጠው ሕይወት ዘላለማዊ የሆነ በረከት ነውና በመካከላችንም የከበረ ስለሆነ ይህንን ስለ አየን እና ስለቀመስን እንዲሁም ስለዳሰስነው እናወራላችኃለን ያየነውን እና የቀመስነውን በውነት እንናገራለን እንጽፍላችኋለን !

ስንከተለው ላፍታም አልተለየንም እና ታማኝነቱን አረጋግጠናል ! ስናዝን አጽናንቶናል ፤ ተስፋ ስንቆርጥ ወደ ነፍሳችን ተጠግቶ አይዟችሁ ብሎናል ስለዚህም እኛ ፍቅሩን የቀመስን ፤ አደራረግ እና አሰራሩን ያየን ፤ ምስክርነታችን እውነት ነውና እንጽፍላችሗለን ።

እነ ሓዋርያው ዮሓንስ በነበያት የትንቢት ቃል ስለ ሰው ልጆች ኃጢያት ሊሞት እና በሦስተኛው ቀን ሊነሳ ይገባዋል ስለ ተባለለት አዳኝ “ኢየሱስ ክርስቶስ ” በምድር ላይ ሦስት አመት ተኩል ባገለገለበት ወቅቶች አብረውት እየወጡ እየገቡ በቅርብ ሥራውን አይተዋልና ቀርበውም ዳሰውታልና ፤ መልካምነቱን ታእምራቱን ጠግበዋል እና ዝም ሊሉ አልቻሉም ነበር !

እኛም መሲሁን አግኝተነዋልና ደግሞም ስለቀመስነውና ስለዳሰስነው እንናገራለን ። የሞተና ተስፋ የተቆረተበት ነገራችን በጌታ ትንሳኤ አግኝቶ እንደገና ህይወት ዘርቷልና ይህንን ሊያደርግ የሚቻለው ብቸኛው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው እያልን እናወራላችኋለን እንጽፍላችኋለን !

ክርስትና ሓይማኖት አይደለም ። ክርስትና እውነት እና ሕይይወት ነው ስለዚህ ይኖርበታል ፤ እንዲሁም የሚቀመስ ፤ የሚዳሰስ ደግሞም የሚታይ ነው እና ያጣጥሙታል ! ስለዚህም ያወሩታል ፤ ይዘምሩታል ይመሰክሩለታል ይጽፉታል ።
አሜን ! የክርስቶስ ወንጌል የተቸገሩትን ነጻ ለማውጣት ፤ የታሰሩትን ለመፍታት የታመሙትን ለመፈወስ እንዲሁም በአጋንንት የተያዙትን ነጻ ለመልቀቅ ወሳኝ ነውና የጌታን ማዳን በቀመሱና እውነትን በተረዱ የመንግስቱ ወራሾች ይሰበካል ፤ ይነገራል !

ሁላችንንም ካህናት እና የመንግስቱ ወራሾች ያደረገን መድሓኒአለም ይባረክ !

--------
እለታዊ ዲቮሽኑ ሊጠናቀቅ 36 ቀን ቀረው