ዲቮሽን ቁ.168/07፣ ረቡዕ፥ የካቲት 18/07 ዓ.ም.
(በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)
(በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)
ሁለት ጊዜ ሰማሁ!
እግዚአብሔር
አንድ ነገር ተናገረ እኔም ይህን ሁለት ጊዜ ሰማሁ፤ ኃይል የእግዚአብሔር
ነው! (መዝ 62፡11 አዲሱ መደበኛ
ትርጉም)
በአሮጌው
(ቀሐሥ) ትርጉም፣ ‹‹እግዚአብሔር አንድ ጊዜ ተናገረ፥ እኔም ‹‹ይህን ብቻ››
ሰማሁ፣ ኃይል የእግዚአብሔር ነው፡፡›› ይላል፡፡ ከአሮጌው ትርጉም በስተቀር በርካታዎቹ ትርጉሞች፣ ‹‹ሁለት ጊዜ ሰማሁ›› ብለው ይተረጉማሉ፡፡
በርግጥ፣
እግዚአብሔር የተናገረው አንዴ ነው፡፡ የመጀመሪያው ዋናው ነገር ይኼ ነው – የእግዚአብሔር መናገር! ሁለተኛው ዋና ነገር የኛ ድምጹን
መስማት ነው! ጌታ የሚናገረውን ድምጹን መስማት መቻል ከእኛ የሚጠበቅ ትልቅ ኃላፊነት ነው!
ወገኖች
ሆይ፣ መዝሙረኛውን አስቡ! ጌታ እግዚአብሔር አንድ ጊዜ ተናገረ፣ መዝሙረኛው ዳዊት ሁለት ጊዜ ሰማው! የሚገርም ነገር ነው! ግን
አንዴ የተነገረውን ሁለት ጊዜ መስማት ማለት ምን ማለት ነው?
ታውቃላችሁ፣
አንዴ የተነገረውን ሁለት ጊዜ መስማት ድንቅ ችሎታ ነው! አንዴ የተነገረውን ሁለት ጊዜ መስማት ማለት፣ የሰሙትን ነገር ማስተዋል
ማለት ነው! የሰሙትን ነገር ማስተዋል ማለት ደግሞ ‹‹ማዳመጥ›› ይባላል!
ወገኖች
ሆይ፣ ጌታ እግዚአብሔር አንድ ጊዜ የተናገረውና፣ መዝሙረኛው ዳዊት ሁለት ጊዜ የሰማው ነገር ምንድነው? ጌታ አንዴ የተናገረው መልዕክት፣
‹‹ኃይል እግዚአብሔር ነው!›› የሚል ነው፡፡
ታውቃላችሁ፣
ኃይል እግዚአብሔር ነው!
ወገኖች
ሆይ፣ እግዚአብሔር ይናገራል፣ ‹‹ኃይል እግዚአብሔር ነው›› ይላል፡፡ ይህንን ድምጽ ደጋግመን እንስማ! ኃይል እግዚአብሔር ነው!
ይህንን እግዚአብሔርን ድምጽ እንደ ገደል ማሚቱ ጧት ቀንና ማታ ደጋግመን እንስማ! ኃይል እግዚአብሔር ነው!
ወገኖች
ሆይ፣ ኃይል እግዚአብሔር ነው! ከችሎታችንና ከአቅማችን በላይ፣ ከምንችለውና ከምንሸከመው በላይ የሆነ ፈተና ያጋጠመ ሲመስል የእግዚአብሔርን
ድምጽ አጥርተን እንስማ! ኃይል እግዚአብሔር ነው!
ወገኖች
ሆይ፣ አያልፉት እንቅፋት፣ አይችሉት ተግዳሮች፣ አይሞክሩት ትግል፣ አይወጡት ነገር ሲያጋጥም የእግዚአብሔርን ድምጽ አጥርተን እንስማ!
ኃይል እግዚአብሔር ነው!
ወገኖች
ሆይ፣ እግዚአብሔር ተናግሯል፣ ‹‹ኃይል እግዚአብሔር ነው›› ይላል፡፡ ይህንን እግዚአብሔርን ድምጽ እንደ ገደል ማሚቱ፣ ጧት፣ ቀንና
ማታ ደጋግመን እንስማ!
--------------------------------
(ትምህርቱ
ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክ ያድርጉ፣
ጌታ ይባርክዎ!)