ዲቮሽን 353/07፥ ቅዳሜ፥ ነሐሴ 23/07 ዓ/ም
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)
እግዚአብሔር ይሔ ነው!!!!
እነሆ አምላካችን ይህ ነው፤ በእርሱ ታመንን እሱም አዳነን። በማዳኑም ደስ ይበለን፤ ሐሴትም እናድርግ። ኢሳ 25፡9
እግዚአብሔር እንዲህ ነው! ዘርህ፣ ትምህርትህ፣ እድሜህ፣ ቀለምህ፣ አገርህ ምናምን አይልም። ይህ ነገርህ ስለተበላሸ ይህን ማድረግ አልችልም አይልም። አደራ ቢሰጠው እንደ ሰው አይረሳም። ወይ አይመቸኝም በጀትም ሆነ ፋሲሊቲ የለኝም አይልም።
በተዘጋ በር ላይ ሰላም ለእናንተ ብሎ መምጣት አያቅተው! ግን እንዴት ገባ? እያልን እንኳን መጠየቅ አንችልም። መቃብሩንስ ፈንቅሎ ተነስቶ አይደል እንዴ፤ ማን ድንጋዩን አነሳለት!
ሲናገር የእኛን አቋም እያየ አይደለም፣ እንኳን በሕይወት በአጸደ ስጋ እያለን፣ የእኛ ጌታ ኢየሱስ እኮ ለሞተው አልዓዛር ለተቀበረው፣ ለሸሸተው፣ 'አልዓዛር ተኝቷል' ብሎ፣ ሰው ከእንቅልፍ እንደሚቀሰቀስ ቀሰቀሰው።
በዚህ አላበቃም፣ የእኛን ጌታ ከቶ በምን እንመስለዋለን! ከቶ ከማንስ ጋር እናወዳድረዋለን! ለደረቁት አጥንቶችስ ቢሆን፣ ከመሽተት ከመግማት ላለፉት፣ ማንንም በጠረናቸው ለማይስቡት፣ የተራበ ቁራና የተራበ ጅብ እንኳን የማይፈልጋቸውን፣ እንጨት የሆኑ አጥንቶችን፣ 'በሕይወት ኑሩ' ብሎ ሲናገር ምንም አልሰጋም እኮ!!!
እረ በሱ ብቻ ተማመኑ! ሥጋ ለባሽ ሁሉ ከንቱ ነው! አብርሃምን እኮ፣ 'አንድ ብቻውን በሆነ ጊዜ ጠራሁት፣ ባረክሁት አበዛሁትም' ብሎ የተናገረውን ጌታ ነው የምናመልክ። ዘመን የማያነሳውን፣ ዘመን የማይጥለውን ኢየሱስን እኮ ነው እኮ የምንከተል። ሥንቱ ይወራ!!!!!
ስለዚህ ኑ፣ በእግዚአብሔር ደስ ይበለን! የትም ቦታ ሆነን በምንም ሁኔታ ሆነን፣ በቃ በእግዚአብሔር ደስ ይበለን።
እግዚአብሔር ፈራጃችን ነው። እግዚአብሔር ህግ ሰጪያችን ነው። እግዚአብሔር ንጉሳችን ነው። ኢሳ 33፡22
---------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 13
ቀን ቀርቶታል
No comments:
Post a Comment