Sunday, November 2, 2014

ነጻነት–ነጻ አይደለም!

ዲቮሽን ቁ.53/07     እሁድ፣ ጥቅምት 23/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)

ነጻነት–ነጻ አይደለም!

በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻነት አወጣን፤ እንግዲህ ጸንታችሁ ቁሙ እንደ ገናም በባርነት ቀንበር አትያዙ(ገላ 5፡1)።

ነጻነት ነጻ አይደለም–ዋጋ ተከፍሎበታልና! ነጻነታችን በነጻ አልተገኘም–ስለነጻነታችን ክርስቶስ ተሰውቷልና! ስለነጻነታችን ጌታችን ኢየሱስ ደዌያችንን ተቀብሎ፣ ሕመማችንን ታምሞ፣ ስለ መተላለፋችን ቆስሎ፣ ስለ በደላችንም ደቅቆ ስለ ኃጢአታችን ሞቷል!

ወገኖች ሆይ፣ በነጻነት እንድንኖር ለአርነት ተጠርተናል! ከእርስ በርስ ጥላቻ ነጻ እንድንወጣ ተጠርተናል! ከብሔር መነቃቀፍ፣ ከቋንቋ መዘላለፍ፣ ነጻ እንድንሆን ተጠርተናል! ከፖለቲካ ግጭት፣ ከተቃውሞ ፍጭት፣ ከሥጋ ጦርነት ነጻ እንድንሆን ተጠርተናል!

ወገኖች ሆይ፣ በፍቅር–በደስታ፣ በሰላም–በትዕግሥት፣ በቸርነት–በበጎነት፣ በእምነት–በየውሃት፣ ራስን በመግዛት በነጻነት እንድንኖር ለአርነት ተጠርተናል!

ወገኖች ሆይ፣ ነጻነታችንን በሚቀለብስ በማንኛውም የባርነት ቀንበር እንዳንያዝ ልንጠነቀቅ ይገባል! ሥጋን ከክፉ መሻቱና ከምኞቱ ጋር ሰቅለን በመንፈስ እየኖርን በመንፈስ እንድንመላለስ ተጠርተናል!።

ወገኖች ሆይ፣ ነጻነታችን በነጻ አልተገኘም–ዋጋ ተከፍሎበታል! ከምኞት–ከዝሙት፣ ከእርኩሰት–ከመዳራት፣ ከጣዖት አምልኮ–ከሟርት፣ ከጥል–ከክርክር፣ ከቅንዓት–ከቁጣ ነጻ፣ ከአድመኝነት–ከመለያየት፣ ከመናፍቅነት–ከምቀኝነት፣ ከስካር–ከዘፋኝነት…የባርነት ቀንበር ተመልሰን እንዳንያዝ ልንጠነቀቅ ይገባል!

ወገኖች ሆይ፣ ነጻነታችን በነጻ አልተገኘም–ዋጋ ተከፍሎበታል! ስለሆነም እንደገናም በባርነት ቀንበር እንዳንያዝ ጸንተን ልንቆም ይገባል!

-------------------------

(ይህን ዕለታዊ ዲቮሽን ላይክና ሼር ያድርጉ፣ ወዳጅ ጓደኞችዎም እንዲያገኙ ያግዙ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!)