Sunday, February 15, 2015

እራሳችንን እንጣል!

ዲቮሽን ቁ.158/07፣ እሁድ፥ የካቲት 8/07 ዓ.ም.
(በዶ/ር በቀለ በላቸው)

እራሳችንን እንጣል!

የእግዚአብሔር ኃይል ድንቅ ነው፡፡ ይህንን ኃይል የምንስበው ደግሞ ከቃሉ ጋር ባለን ቁርኝትና ጸሎት መሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ነገር ግን እውነተኛ እግዚአብሔር ደስ የሚሰኝበት ጸሎት መጸለይ እንደ ቀላል መታየት የለበትም፡፡
አንደኛው ተግዳሮት የጨለማው ጥላ በጸሎት ላይ ያለ የሌለ ኃይሉን ስለሚያሳርፍ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ በተለይ በዚህ በምዕራቡ ዓለም ካለው የሥራ ጫናና ባተሌነት የተነሣ፣ ጉልበትን ለጸሎት ማጠፍ እጅግ ከባድ ነው፡፡ ከዚህም የተነሣ አንዳንዴ የጭለማው ዓለም ተጽዕኖ በሕይወታችን ላይ በግልጽ ይታያል፡፡
ከሚታወቁት ተጽዕኖዎች አንዱ ነፍሳችንን ማዋከቡና መረጋጋትና ሰላም እንዳይኖረን ማድረጉ ነው፡፡ ታዲያ ከዚህ ወከባ ለመዳን የተገኘውን አጋጣሚ ሁሉ ጨክኖ በሱ ፊት መሆንን ግድ ይለናል፡፡ ጌታ በምሕረቱ የእረፍት ጊዜዎችን ሲያመቻችልን ደግሞ፣ሳይሰስቱ ለጸሎት መጠቀሙ አስተዋይነት እላለሁ፡፡
ሰይጣን ምንጩን በማናውቀው ምክንያት በኀዘንና በድብርት ሊመታን ይችላል፡፡ እርካታ የለሽና ቅብጥብጥ ሊያደርገንም ይችላል፡፡፡ ከአፋችንም የምስጋና ቋንቋ በማራቅ ነፍሳችን ከማትወጣበት ወኅኒ ሊያኖራት ይችላል፡፡ ለዚህ ነው በተለያዩ ነገሮች ሊውጠን ያሰፈሰፈ ባላጋራ በየደጃችን እንደሚገኝ መገንዘቡ አስተዋይነት የሚሆነው፡፡ ለዚህም ነው “በመጠን ኑሩ ንቁ” (1 ጴጥሮስ 5››) የተባልነው፡፡ “አንተ የምትተኛ ንቃ፣ክርስቶስም ያበራልሃል” (ኤፌሶን 5፡14) ተብለንም ተመክረናል፡፡
ለመጸለይ ስናስብ የማይመጣ የአዚም ዓይነት የለም፡፡ ስልኩ ይንጫጫል፣ሰውነታችንን እንቅልፍ እንቅልፍ ይለዋል፣ ጆሮአችን ወሬ ያምረዋል፣ ሌሎች የሚሠሩ ነገሮች ትዝ ይሉናል፤ ሌላም ሌላም፡፡ እኒህን ተግዳሮቶች አሽቀንጥረን ነው ለጸሎት በጌታ ፊት የምንወድቀው፡፡ ቢሆንም ተግዳሮቱ ጸሎት ጀምረንም አያባራም፤ እየጠነከረ ይቀጥላል፡፡ እንዳውም ከምንጸልይበት ሳያስነሳን አያርፍም፡፡ ስለዚህ አንዳንዴ በኃይል በእምነት እየተቃወሙ የጠላትን ሥራ ማፍረስ ጥሩ ነው ብዬ እመክራለሁ፤ በተደጋጋሚ ጠቅሞኝ አይቻለሁና፡፡
ይህንን ጽሑፍ ከማዘጋጀቴ በፊት፣ ባልተሳኩልኝና ባልሆኑልኝ ነገሮች ኀዘንና ድብርት ተጫጭኖኝ ከአልጋዬ ላይ መነሣት አቅቶኝ ነበር፡፡ በዛ ከባድ መንፈስ ውስጥ እያለሁ፣ የእግዚአብሔር መንፈስ አንድ ቃል ወደ መንፈሴ አመጣና አነበብኩት፡፡ ደስ የሚለው ነገር፣የጊዜው መልእክት ነበር፡፡ እንዲህ ይላል፡- “የሚቀጠቅጥ በአንተ ላይ ወጥቶአል፤
-ምሽግን ጠብቅ፣
-መንገድንም ሰልል፤
-ወገብህን አጽና፣
-ኃይልህንም እጅግ አበርታ”! (ናሆም 2፡1፤አፅንዖት የእኔ)
አዎ! እጅግ ገራሚ የሆነ የሰዓቱ የመንፈስ ቅዱስ መልእክት ነበር፡፡ ለመጣልኝ መልእክትም ጌታን አመስግኜ፣ በመሀል በመሀል በኃይል በእምነት እየተቃወምኩኝ ቢያንስ ለሁለት ሰዓት ጸለይኩ፡፡ ከዚያም የሆነ የአዚም ጉም ከላዬ ላይ ሲነሣ ታወቀኝ፡፡ መለቀቅና መፈታት ተሰማኝ፡፡ የምስጋና ዝማሬም ካፌ መውጣት ጀመረና የመንፈስ ቅዱስ ኃይል እጅግ አስደነቀኝ፡፡ ከዚያም ተመሳሳይ ሁኔታ ላይ ያለ አይጠፋም ብዬ ይህችን አጭር መልእክት ጫጭሬ አስተላልፍኩ፡፡
ዋናው መልእክቴም ይሄ ነው፡-ቃሉ “እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበል በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ” (ዕብራውያን 4፡16) ይላልና፣ በነፍሳችን መታገሉን ትተን፣ የተትረፈረፈ እረፍትና ሰላምን በሚሰጠው አምላክ ፊት እራሳችንን ሳናቅማማ እንጣል!

እረፍት በማን ?

ዲቮሽን ቁጥር 157/07 ቅዳሜ
( በ ጌታሁን ሐለፎም )

እረፍት በማን ?
ለሰላም ሳነሳ ከረጅም ጊዜ በፊት ያየሁትን ስዕል አስታወስኩኝ :: በጣም በሚነዋወጥ ባህር ላይ አንዲት ወፍ በአንዲት ከባህሩ ስር በወጣች ቀጭን ሰንበሌጥ ላይ ያለስጋት ቁጭ ብላ ትታያለች ፣
የወጀቡ መናወጥ ለጉድ ነው ፣ እሷ ግን ድንጋጤም አይታይባትም ፣ ለመብረር ያሰበችም አትመስልም ፍጹም ተደላድላለች :: ትርኢቱ በሆነው ባልሆነው ለምንፈራ እና ለምንደነግጥ ለእኛ ያስቀናል ፣ ወይ መታደል ያስብላል:: ለመሆኑ በዚያ በሚያስፈራ እና በሚያስደነግጥ ወጀብ ወፏ ለምንድ ነው ፍርሃት ያልታየባት ለምንድን ነው ያልተሽበረችው ? ብለን ብንጠይቅ ፡ መልሱ ቀላል ነው ወፏ መብረር ስለምትችል የወጀቡ ግርግር ስጋት ሊፈጥርባት አይችልም ።
መቸስ የፃድቅ ሰው አይን በራሱ ላይ ነው። ይላል እና ቃሉ ፡ እራሴን አየሁ ፡ ቅዱሳን ወገኖቼን አሰብኩ ፡ ለምንድነው የምንናወጠው ? በሆነው ባልሆነው ለምንድን ነው ልባችን የሚርደው ? የጌታ ጥበቃ የት ሄዶ ?
በዚህች ትንሽ ፍጥረት አይምሮ ውስጥ መብረር መቻሏ ታላቅ ድፍረት በውስጧ እንዲፈጠር አድርጓታል ፣ በቃ አትደነግጥም ። ይህንን ጥበብ ማን ሰጣት ይህንን ተፈጥሮ ማን አደላት ? ጌታ ።
አሁን ያለንበትን ዘመን ስናይ ከመቸውም በበለጠ ፣ ምድር በከፍተኛ የሰላም ማጣት ፣ ወጀብ እና ነውጥ ውስጥ እንደምትገኝ መረዳት ይቻላል ::ምንም እንኳ ሰላምን በምድር ዙሪያ ለማምጣት የተለያዩ ሙከራወች በተለያዪ ተቁዋሞች ቢካሄዱም፣ በጠረጴዛ ዙሪያ ሀያላኖች ቢመክሩም ፣ ከረጅም ዘመን በፊት የተቋቋሙ የመንግስታት ድርጅቶች የተነሱበትን አላማ ግብ ሳይመቱ እዚህ ደርሰዋል ።
እንዲያውም በምድር ላይ እንደዚህ ያለ የፍርሃት እና የሰቀቀን ድምፅ ታይቶ እና ተሰምቶ አይታወቅም ::
የዜና ማሰራጫወች በጎ እና ተስፋ ያለበትን ወሬ ማሰማት ከተው ቆይተዋል ። ሁሉም የሞት ወሬ ፣ የሽብር ዜና። ምክኒያቱም የአለም ገጽታ ተልለውጧል ፣ በየትኛውም ስፍራ የጦርነት ድባብ ነግሷል ምን ይደረግ ሰላምን የሚወክል ጠፋ ሰላምን የሚያመጣ ታጣ ::
ሁሉ አሸባሪ ሁሉ ገዳይ ሆነ ::ዛሬ ማእበሉ እና ወጀብ በበዛበት በዚህ አስከፊ ዘመን እንደ ወፏ በጸጥታ ለማረፍ ሌላ አማራጭ የለም ፣ ከአንዱ ከሰላም አባት በስተቀር፣ ሌላ መፍትሄ አይገኝም እሱም እየሱስ ነው :።
የሰላምን መንገድ የሚያመላክት ሌላ መጽሃፍ አይገኝም :: ሰላም በክርስቶስ ካልሆነ በስተቀር ፈጽሞ አይታሰብም :: በዚህ ሰዓት እኔና እናንተ እንደወፏ በርጋታ እና ያለ ስጋት ልንቀመጥ ያስፈልገናል :: ንጉሱ ላይ ተደግፈን፡ሩጫችን የጌታ ነው ፡ ኑሮአችን የሱ ነው፡እኛ የራሳችን አይደለንም፡
ባለ ቤት አለን፡እሱ ደግሞ የሁሉ የበላይ ነው፡አስተማማኝ።
በወጀብ ውስጥ እረፍት የሆነውን ጌታ አስረግጠን እንወቀው። ከሚደነግጠው ጋር አንደንግጥ ከሚፈራው ጋር አንፍራ :: በወጀብ እና ባውሎ ነፋስ መንገድ ባለው አምላክ እንታመን ።ወፍዋ በወጀብ ባውሎነፋስ እንዳትናወጥ የሚያስችል ተፈጥሮ ያላበሳት እግዚአብሔር ነው ።
እኛ ደግሞ ወፍዋ የሌላት ሰብእና አለን ። ክርስቶስ ወዶን ስለኛ ሞቶ ከዘላለም የሞት ፍርሀት ነፃ አውጥቶናል።ከጌታ የተነሳ ዋጋችን እጅግ ታላቅ ነው።
ጌታም በ መዝ.(46) 10 ላየ ሲናገር እንዲህ ብሎአል ``ዕረፉ እኔም አምላክ እንደሆንኩ እወቁ ``
ይህ መልእክት ለሌሎች ይጠቅማል ብለው ካሰቡ ሼር በማድረግ የጌታን መንግስት ያገልግሉ።

“እባክህን፣ የአኪጦፌልን ምክር ወደ ከንቱነት ለውጠው?”

ዲቮሽን ቁጥር 156/07፣ አርብ፣ የካቲት 6/07
(በማርታ ሲሳይነህ)

“እባክህን፣ የአኪጦፌልን ምክር ወደ ከንቱነት ለውጠው?” 2ኛ ሳሙ፡15፡ 31
ይህንን ጸሎት ያደረገው፣ እግዚአብሔር እንደ ልቤ ያለው ንጉሥ ዳዊት ነው። ንጉሥ ዳዊት እግዚአብሔር ምን እንደሆነ፣ ማን እንደሆነ፣ የኃይሉንም ሆነ የቁጣውንም ጥግ፣ እንዲሁም የሥልጣኑን የበላይነት፣ የማያቋርጥ ምሕረቱንና ፍቅሩን ከልጅነቱ ጥንቅቅ አድርጎ በማወቁም፣ በመዝ 111፡ 10 “የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው” በማለት ይናገራል። እስከመጨረሻውም ድረስ፣ ጠላቶቹን ሁሉ ያሸነፈው በዚሁ መርሁ ነው። “ዕድሜም፣ ባለጠግነትንም፣ ክብርንም ጠግቦ በመልካም ሽምግልና ሞተ” 1ኛ ዜና፣ 29፡ 28፣ ተብሎ እስከተነገረለት ድረስ፣ ይህንን ፍርሐት ጠብቆ፣ ተግብሮም አሳይቶናል።
ዓመጸኛው አቤሴሎም፣ እንደ አባቱ ብርቱ ጦረኛ እና ብልሕም ነበር። ብልሕ በመሆኑም ነው፣ 2ሳሙ 15፡8 “ወደ ኬብሮን ለእግዚአብሔር እሰግዳለሁ” ብሎ አባቱን ዋሽቶት በሚሔድበት ጊዜ፣ አኪጦፌልን ይዞት የሔደው። የዳዊት አማካሪ የነበረው “አኪጦፌል፣ የሚሰጠው ምክር የእግዚአብሔርን ቃል እንደ መጠየቅ ይቆጠር ነበር፤ ዳዊትም ሆነ አቤሴሎም የአኪጦፌልን ምክር የሚቀበሉት በዚህ ሁኔታ ነበር” 2ሳሙ16፡23።
አኪጦፌል፣ የተናገረው ሁሉ ከመሬት ጠብ የማይል፣ በምክር ግሩም የሆነ፣ ኃያል ጦረኛ ነው። አቤሴሎምንም፣ “ኣባትህ ከተዋቸው ቁባቶቹ ጋር ግባና ተኛ፣ ከዚያም አንተ አባትህን እጅግ የጠላህ መሆንህን መላው እስራኤል ይሰማና አብሮህ ያለው ሁሉ ክንዱ ይበረታል” 2ሳሙ 16፡ 21-22 ብሎ፣ ከሰው ልማድ ውጭ የሆነውን ድርጊት መላው እስራኤል እያየው፣ ከአባቱ ቁባቶች ጋር በጠራራ ጸሐይ፣ እንዲተኛ ያደረገው ሰው ነው።
ዳዊት፣ አቤሴሎምን ሸሽቶ፣ እያለቀሰ፣ በባዶ እግሩ የደብረ ዘይትን ተራራ እየወጣ ሳለ፣ “ከአቤሴሎም ካሴሩት መካከል አንዱ አኪጦፌል ነው” የሚል መረጃ ደረሰው። ያ፣ የእግዚአብሔርን ልዕለ-ኃያልነት እና ወሰን የለሽ የማድረግ ብቃት፣ የሚያውቀው ዳዊት ግን፣ እያለቀሰም፣ እንባውን መንታ፣ መንታ አድርጎ እያወረደም፣ ዙፋኑን ጥሎ እየሸሸም፣ ቢሆን፣ በእግዚአብሔር መደገፉን አላቋረጠም፤ “እግዚአብሔር ሆይ፣ እባክህን፣ የአኪጦፌልን ምክር ወደ ከንቱነት ለውጠው” 2ኛ ሳሙ፡15፡ 31 በማለት እግዚአብሔርን ተማጸነ። እግዚአብሔርም፣ በምዕ. 17 ላይ እንደምናየው፣ የአኪጦፌልን ምክር መና አደረገው። በሕይወት ዘመኑ ለመጀመሪያ ጊዜ፣ ምክሩ ተቀባይነት ሳያገኝ የቀረው አኪጦፌልም፣ አንድም ስለተናቀ፣ አንድም፣ ዳዊት እንደሚያሸንፍ በማወቁ እና የሚከተለውን መዘዝ በማወቁ፣ 17፡23 ላይ በገዛ እጁ ታንቆ ሞተ።
ዛሬ፣ የእኔና የእናንተ አኪጦፌል ማነው? ምንድነው? እውነት የሆነ፣ እውነትነቱ ግን፣ ግን በእኔና በእናንተ ላይ፣ ውርደትን፣ ሽንፈትን፣ ኃዘንን፣ የማያባራ ለቅሶን፣ የሚያስከትል፣ አኪጦፌሊያዊ ምክር ምንድነው? እውነት ከመሆኑ የተነሳ፣ “በኔና በሞት መካከል አንድ እርምጃ ብቻ ቀረ” ያስባለን (1ኛ ሳሙ 20፡2)፣ እውነት ከመሆኑ የተነሳ፣ “ልቤ በላዬ ተናወጠብኝ፣ የሞት ድንጋጤም ወደቀብኝ፣ ፍርሀትና እንቅጥቅጥ መጡብኝ፣ ጨለማም ሸፈነኝ፣ በርሬ ዐርፍ ዘንድ እንደ ርግብ ክንፍን ማን በሰጠኝ”፣ መዝ 55፡ 4-6 ያስባለን፣ አኪጦፌላችን ምንድነው?
እጸልያለሁ፤ አብ አባት ሆይ፣ “እግዚአብሔር በሚፈሩት፣ በምሕረቱ በሚታመኑትም ይደሰታል” መዝ 147፡11 ተብሎ እንደ ተጻፈ፣ እኔና ሕዝብህን፣ ሊያዋርድና ሊያጠፋ፣ የተሸረበ ማንኛውም አኪጦፌሊያዊ ምክር ሁሉ፣ ዛሬ፣ አሁን፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ከንቱ ይሁን!!!!!!! አሜን
------
ትምህርቱ ጠቅሞዎታል? እንግዲያውስ ሼር እና ላይክ ያድርጉ፤ ጌታ ይባርክዎ!
----------------
‘የወንጌላዊው እጮኛ’ አዲስ መጽሐፍ በገበያ ላይ ውሏል። ለተጨማሪ መረጃ በ0911 678158 ወይም በ0911 803092 ይደውሉ።

እንቁልልጭ ቢበዛም!

ዲቮሽን ቁ.155/07፣ ሐሙስ፥ የካቲት 5/07 ዓ.ም.
(በማርታ ሲሳይነህ)

እንቁልልጭ ቢበዛም!

“እስማኤልን ብቻ ባርከህ ባኖርክልኝ” (ዘፍ 17፡18)
ይህንን ያለው፣ የእግዚአብሔር ወዳጅ፣ ወይም ጓደኛ ሆኖ ሳለ፣ የተስፋው ቃል “ላም አለኝ በሰማይ” የሆነበት፣ ሽማግሌው አብርሐም ነው። ሁልጊዜም፣ አብርሐምንና እግዚአብሔርን ሳስባቸው በፊቴ መጥቶ ድቅን የሚልብኝ ጥብቅ ጓደኝነታቸው ነው። አብርሐም፣ ዘፍ 12፡7 ላይ “ታላቅ ህዝብ አደርግሐለሁ” ያለውን አንድ እግዚአብሔርን አምኖ፣ ከሥጋ ዘመዶቹና ወገኖቹ ተነጥሎ በ75 ዓመቱ ወጣ።
ከዘመድ እና ከወዳጅ፣ መለየትን መቼም የደረሰበት ሰው ያውቀዋል! እንደገና በ12፡7 ላይ፣ “ይሕችን ምድር ለዘርህ እሰጣለሁ” ብሎ ወዳጁ እግዚአብሔር ቃል ገባለት። ቢሆንም ግን፣ ከጥጋብ የወጣው አብርሐም፣ ጭራሽ ተራበ (12፡10)፣ ይህም አለፈና፣ እግዚአብሔር አሁንም “ዘርህን እንደ ምድር ትቢያ አበዛዋለሁ” አለው (13፡16)። ቀጥሎም፣ “ከአብራክህ የሚከፈል ልጅ ወራሽህ ይሆናል” አለው (15፡5)።
ይሕ ሁሉ ሲሆን፣ ለአብርሐም፣ የልጅ ጉዳይ የሁልጊዜ ጥያቄው እንደሆነበት አለ። አንድ ልጅ ‘የሕልም እንጀራ’ ለሆነበት ለአብርሐም፣ እግዚአብሔር ግን፣ ምን ገዶት? የትውልዱን ራዕይ አሳየውና፣ “በአራተኛው ትውልድ ዘርህ ወደዚህ ምድር ይመለሳል” አለው(15፡16) ። አብርሐም ይህን ጊዜ በልቡ፣ ‘ወይ አንተ! ትቀልዳለህ? እኔ አንድ ልጅ እንዳማረኝ ልሞት ነው፣ አንተ ስለ አራተኛ ትውልድ ትናገራለህ? ምናለበት ዝም ብትል?’ የሚል ይመስለኛል።
በመጨረሻም፣ 11 ዓመት ሙሉ የልጅ ጠኔ ለያዘው ለአብርሐም፣ በሳራ በኩል ዘዴ ተዘየደለትና፣ ከአጋር በ86 ዓመቱ እስማኤልን አገኘ። “እንዲያው እስከ ዛሬ ድረስ ይህን ማድረግ ስችል፣ እግዚአብሔርን አጉል ስጠብቅ 11 ዓመታትን አቃጠልኩ፤ እስከዛሬ እኮ የዓሥር ዓመት ልጅ አደርስ ነበር! ምንኛ ሞኝ ሰው ነኝ!” ያለ ይመስለኛል።
እስማኤል፣ ወደ 13 ዓመት ሲሆነው፣ አሁንም እግዚአብሔር፣ ምን ተስኖት? (17፡1-14) ላይ፣ “ዘርህን አበዛለሁ” እያለ፣ ሰፋ ያለ የትውልድና የግዝረትን ኪዳን ይናገረዋል። አሁን፣ የ99 ዓመቱ አብርሐም፣ አባት ስለሆነ፣ ደረቱን ነፋ፣ አድርጐ፣ እግዚአብሔር ከመጀመሪያ ጀምሮ እስካሁን የገባለትን ኪዳን፣ በልዩ ብርታት እያስታወሰ፣ በእጁ የያዘውን እስማኤልን እያሰበ፣ ወዳጁ እግዚአብሔርን ያደምጠዋል።
ጉድ የፈላው 17፡15 ላይ፣ የቃልኪዳን ልጁ፣ ከሣራ እንደሚወለድ ሲነግረው ነው። ይህን ጊዜ፣ አብርሐም፣ እንደመከፋት ያለ ሳቅ ሳቀና፡- እንዲያው፣ ቀልዱን ተወውና፣ “እስማኤልን ብቻ ባርከህ ባኖርክልኝ!” ዘፍ 17፡18 ይለዋል። ጐመን በጤና ዓይነት ንግግር ነው! ሆኖም፣ ምን ተስኖት፣ የሆነው እግዚአብሔር፣ በ90 ዓመቷ ሣራን አሰባትና፤ ከ25 ዓመታት በኋላ፣ አብርሐም፣ በመቶ ዓመቱ ይስሐቅን አገኘ። የተስፋው ቃልም ተፈጸመ።
ዛሬም፣ እግዚአብሔርን፣ በልዩ ልዩ ሁኔታ ለጠበቅነው፣ ከተስፋ ቃላችን መዘግየት የተነሳም፣ ተስፋ ቆርጠን፣ መልካም አማራጭ የመሰለንን እስማኤልን ለያዝን፣ እግዚአብሔርንም፣ “ሌላው ሌላው ሁሉ ቀርቶብኝ፣ እንቁልልጭ ያልከኝ ነገር ሁሉ ቀርቶብኝ፣ እስማኤልን ብቻ ባርከህ ባኖርክልኝ”፣ ለምንለው፣ ለእያንዳንዳችን፣ በእርግጥ፣ ይስሐቅ ይወለዳል፤ ኤፌ 3፣20 “ከምንለንምነው ወይም ከምናስበው ሁሉ በላይ እጅግ አብልጦ ማድረግ ለሚቻለው”፣ ለእግዚአብሔር፣ ምንም የሚያቅተው ነገር የለምና”!!!!!!
----
ትምህርቱ ጠቅሞዎታል? እንግዲያውስ ሼር እና ላይክ ያድርጉ ፤ ጌታ ይባርክዎ!
- - - - - -
የወንጌላዊው እጮኛ አዲስ መጽሐፍ በገበያ ላይ ውሏል ። ለተጨማሪ መረጃ በ0911 678158 ወይም በ0911 803092