Sunday, June 7, 2015

በፍጹም አልጥልህም!!!!!!!

ዲቮሽን 271/07 ሰኞ ሰኔ 1/07
(
በእህት ማርታ ሲሳይነህ)

በፍጹም አልጥልህም!!!!!!!


እርሱ ራሱ አልለቅህም፣ ከቶም አልተውህም ብሎአልናዕብ 13 5

እንግዲህ ጌታን፣ ካንተ ወዴት እንሄዳለን? ስንለው፣ የእርሱ ምላሽ የዘላለም ጥም ቆራጭና የማያንቀዠቅዥ ይሆናል። በመከራ መካከል ብንሄድ እንኳን እርሱ ህይወታችንን ይጠብቃታል። በጠላቶቻችን ቁጣ ላይ እጁን ይዘረጋል፣ በቀኝ እጁም ያድነናል። ሰይጣን፣ ሊገድለን ሲያደባ፣ ከብዙ ሞቶች ጌታ ታድጎናል። በአጠገባችን ሺህ፣ በቀኛችን አስር ሺህ ሲወድቅ፣ ከብርቱዋ ከጌታ እጅ የተነሳ በህይወት ኖርን።

እርሱ ራሱ፣ ጌታ በገዛ አንደበቱአልለቅህም፣ ከቶ አልተውህም፣ በፍጹም አልጥልህም፣ስላለን እነሆ ዛሬ የሱን ማዳን ለማውራት ባለ ተራዎች ሆነናል። በተባረክነው ልክ ልንባርክ፣ የጠፉትን ፈላጊ ያዘኑትን አጽናኝ ልንሆን፣ የዛሉትን ልናበረታ፣ ወንጌልን በዓለም ዙሪያ እስከ ምድር ዳርቻ ለማድረስ እድለኞች ሆንን። ምክንያቱም፣ እርሱ ራሱ፣ አልጥላችሁም ስላለን!

ጌታ፣ እርሱ ራሱ፣ አልተዋችሁም ስላለን፣ ‹‹አድነን›› ባልነው ጊዜ፣ ጩኸታችንን ስለሰማልን፡ ስለራራልን፣ ከምናውቀውና ከማናውቀው፣ ከምንገምተውና ከማንገምተው ውርደት እና ጉድ ሁሉ ጠብቆን፣ እነሆ ዛሬን ለማየት በቃን።

አባት ሆይ፣ የልመናችንንን ድምጽ ሰምተሀልና እንወድሀለን፤ ጆሮህን ወደ እኛ አዘንብለሀልና በህይወት ዘመናችን ሁሉ ስምህን እንጠራለን (መዝ 116) አላሳፈርከንም፣ ሞት ሲገባን ህይወትን ሰጠህን፣ ውርደት ሲጠብቀን በክብር አቆምከን፣ መጠጊያ እና መሸሸጊያ ሁነን ባልንህ ጊዜ ሁሉ ከጠላት ክፋትና አመጻ ሰውረህናልና ተባረክ። ምስጋናችን ወደ ማደሪያህ ይግባ። እንወድሀለን።

ትምህርቱ ጠቅሞዎታል? እንግዲያውስ እባክዎ ላይክ እና ሼር ያድርጉ፣ ጌታ ይባርክዎ!!!

አልለቅህም!!!!!!!

ዲቮሽን 270/07 ግንቦት 29/07
(
በእህት ማርታ ሲሳይነህ)

አልለቅህም!!!!!!!

ከእግዚአብሔርም ሆነ ከሰው ጋር ታግለህ አሸንፈሀልና ከእንግዲህ ስምህ እስራኤል እንጅ ያዕቆብ አይባልም(ዘፍ 32 28)

በክርስትና መንገድ ላይ፣ አርአያ የምናደርጋቸው የእምነት አባቶች በሙሉ ጨቅጫቆች ናቸው። በትጋት ከእግዚአብሔር ጋር የሚጨቃጨቁ፣ የሚለምኑ የሚታገሉ፣ ካንተ ወደ ማን እንሔዳለን? የሚሉ ሁሉ የተስፋ ቃላቸውን በእጃቸው አስገብተዋል። አንድ አማኝ፣ የህይወቱ መርህ ሊያደርግ የሚገባው እግዚአብሄርን ብቻ ተስፋ ማድረግ ነው። እግዚአብሄር ደግሞ፣ አማኞች ሁሉ ፈጽመው በእሱ እንዲደገፉ ይፈልጋል።

የአማኝ የእምነት ትጋት በፍሬው ይታያል። እግዚአብሄርን ደስ የሚያሰኘውን ነገር እለት እለት ለማወቅ ይጥራል፣ እንከን የሆነበትን ነገር፣ መንፈስ ቅዱስ እንደሚያጠፋው በማመን ፈቃደኛ ሆኖ እጅ መስጠት ይኖርበታል። ያልቻለውን ነገር ለእግዚአብሄር አደራ እየሰጠ በማንኛውም እንቅስቃሴው ውስጥ ሁሉጊዜ እራሱን እየመረመረ፣ እግዚአብሄርን ደጅ መጥናትና፣ ካልባረክኸኝ አልለቅህም፣ ካላዳንከኝ አልለቅህም፣ ካልፈወስከኝ አልለቅህም፣ ይቅር ካላልከኝ አልለቅህም፣ ብሎ ነገሩን ሁሉ፣ በኤልሻዳዩ እግር ስር ማስቀመጥ መለማመድ ይኖርበታል። ይህ በአንድ ጊዜ የሚመጣ ሳይሆን፣ በሒደት እያዳበርነው፣ እያሻሻልነው የምንመጣው ጉዳይ ነው።

የዓለምን እውቀት እና ጥበብ፣ የዓለምን ተረትና ምሳሌ፣ የሰዎችን ጥበብ ወይም ውሳኔ፣ ሳናስተናግድ፣ ጌታ እግዚአብሄር ከዚህ ሁሉ በላይ መሆኑን ማመንና ማወቅ፣ ምድራዊውንም ሆነ ሰማያዊውን ህይወታችንን ሰላማዊ ያደርገዋል።

አባት ሆይ፣ ካንተ ጋር ፈጽሞ መጣበቅ ይሁንልን። የሰዎች እውቀት እና ድምዳሜ ዛሬ ከዓእምሯችን ላይ የተፋቀ ይሁን። ሰዋዊ የአኗኗር ስልታችና እና ቀመራችንም ዛሬ፣ ከእኛ ላይ እንደ ቅርፊት ይውደቅና በመንፈስ ቅዱስ ኃይል መመላለስ ይሁንልን። ካንተ በሆነ ጥበብና መገለጥ ሙላን። ሰምተህኛልና ተባረክ።


ትምህርቱ ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክ ያድርጉ?