Wednesday, May 27, 2015

መካሪዬ!!!!!



ዲቮሽን 258/07 ማክሰኞ፣ ግንቦት 18/07
(
በእህት ማርታ ሲሳይነህ)

መካሪዬ!!!!!

የመከረኝ እግዚአብሔርን እባርካለሁ መዝ 167

በህይወት ጉዞ ላይ በሚያጋጥሙን ውጣ ውረዶች እና በእለት እለት እንቅስቃሴያችን ላይ ምን ማድረግ እንዳለብን ግራ የሚያጋቡን ሁኔታዎች ይኖራሉ። አንዳንድ ጊዜ፣ ለኛ ጥሩ የሚመስለንና በእግዚአብሔር ዓይን ግን መልካም ያልሆነን ውሳኔ ለመወሰን ልንገደድ እንችላለን። ሁኔታዎች ሲጠሙብንና ሲከብዱብን በፊታችን ያገኘነውን ነገር ይዘን ልንሔድ እንችላለን። ወይም ደግሞ፣ አንደበታችንን ልናስትና እግዚአብሔርን ልናማርር እንችላለን። ወይም ደግሞ መውጫ ከሌለው አስጨናቂ ጉድጓድ ውስጥም ልንገባ እንችላለን። አንዳንዴ ከባድ ሁኔታዎች እና ድንጋጤዎች ሲከቡን የተለያዩ ዓይነት መላ ምቶችን እንሰነዝራለን።

በዚህ ወቅት ግን ቆም ብለን እግዚአብሔርን ልናስብ ይገባል። እግዚአብሔር ምን ይለኛል? እግዚአብሔር በዚህ ሁኔታ ላይ ያለው ሐሳብ ምንድነው? እግዚአብሔር ምን ብሎኛል? እና የመሣሠሉትን ጥያቄዎች በማንሳት ወደ መጽሐፍ ቅዱሳችን እና ወደ ጸሎት መመለስ አለብን። ያን ጊዜ፣ ትክክለኛ እና እንከን የሌለው ምክር፣ አዋጭ እና ዘላቂ የሆነ መፍትሔ ከመንፈስ ቅዱስ እናገኛለን።

ለዚህም ነው ዳዊት ሲናገር፡የሚመከረኝ እግዚአብሔርን እባርካለሁ፤ በሌሊት እንኳን ልቤ ቀናውን ያመላክተኛል መዝ 16 7 ሲል የሚናገረው።

በሌሊቶቻችን ላይ፣ በጨለማዎቻችን ላይ፣ በድንግዝግዞቻችን ላይ፣ እግዚአብሔር ምንም ሳይደነግጥና የኛም ጨለማና ድንግዝግዝ ሳያስፈራው፣ ተራራ የሆነብን ነገር ሳያስበረግገው፣ ትክክለኛውን ምክር ይመክረናል። በእግዚአብሔር ምክር ውስጥ ደግሞ የዘላለም እቅዱ፣ ቸርነቱና ፍቅሩ አለ፤ እግዚአብሔር በምክር ግሩም ነውና!

አባት ሆይ፣ ከስሜታዊነት የተነሳ ድንገተኛ ምክርን ከጠላት እንዳንሰማ እስከዛሬ ድረስ ጠብቀህናልና ተባረክ። ለቀሪው ዘመናችንም የጠላታችን ምክር በኢየሱስ ውድ ስም ከንቱ ይሁንና፣ ያንተ ምክር በልባችን ላይ ተደላድሎ ይቀመጥ። መንፈስ ቅዱስ ሆይ፣ ስትመክረን፣ ስታስተምረን የምናደምጥበትን መንፈሳዊ ጆሮዎቻችን ዛሬ ይከፈቱ። ሰምተህኛልና ተባረክ፤ በኢየሱስ ስም አሜን።

ትምህርቱ ጠቅሞዎታል? እንግዲያውስ እባክዎ ላይክና ሼር ያድርጉ፣ ጌታ ይባርክዎ።

የማይነቀፍ ንግግር



ዲቮሽን 259/07 ረቡዕ፣ ግንቦት 19/07
(
በወ/ም አበባዬ ቢተው)


የማይነቀፍ ንግግር

".....የማይነቀፍ ንግግርን ግለጥ።" (ወደ ቲቶ 2:8)

የምናመልከው እና የምንከተለው ኢየሱስ እውነት እና እውነተኛ ነው። (ዮሐ 146) የተናገራቸው እና አሁንም የሚናገራቸው ቃላት እውነት ናቸው።(ዮሐ 1717)

እኛ ክርስቲያኖች ደግሞ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ስንሆን የእርሱ ልብ ያለን እና እርሱን ልንመስል የተገባን ነን።( 1ቆሮ 216 111)

ስለዚህ ልክ የጌታችን ንግግር እና ቃላት ነቀፋ የማይገኝባቸው እንደሆኑ ሁሉ የእኛም እንዲሁ መሆን አለበት። ሰዎችን የማያንፅ እና የማይጠቅም ክፉ ንግግር ከእኛ በማንኛውም መንገድ ሊወጣ አይገባም። በሐሜት እና አሉባልታ ተጠምደን ራሳችንን ስናሳድፍ እና የሌሎችን ሕሊና ስናቆሽሽ ልንገኝ አይገባም።

ለሻይ ቡና ስንቀመጥ፡ እንደ ፌስ ቡክ ያሉ ማህበራዊ ድህረ ገፆችን ስንጠቀም፡ ሌሎችን ስናገለግል የምንናገረው ንግግር የማይነቀፍ መሆኑን እናረጋግጥ! ስለ ቤተ ክርስቲያን፡ ፖለቲካ፡ እና ግለሰቦች ባላየነው እና ባልገባን ነገር እየገባን የምንናገረውን እና አስረግጠን የምናስረዳውን ነገር (1 ጢሞ 17) ከሐሜት እና አሉባልታ የፀዳ የማነቀፍ መሆኑን እናረጋግጥ! ተጨባጭነት የሌላቸው ከንቱ ንግግሮቸ እንዳይሆኑ እንፍራ። የክርስትና ስነ ምግባር ግድ ይለናልና።

ንግግራችን አማኞችን ተጠራጣሪ፡ የዋሆችን ክፉ፡ ቅኖችን ጠማማ፡ ሰላማዊዎችን፡ አመፀኛ፡ ቸር እና ሩህሩሆችን፡ ጨካኛ እንዳያደርግ እንፍራ! የክርስቶስ ፍቅር ግድ ይለናልና!

ሐሜት፡ አሉባልታ፡ እና ነቀፋ ያለባቸው ንግግሮች መንፈሳዊ ንፅህናችንን ከማሳደፍ በላይ መንፈስ ቅዱስ በእኛ እንዳይሰራ ይከለክላል እና እንጠንቀቅ! (ኤፌ 429-30)

ጌታ ማስተዋል ይጨምርልን! " ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፥ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ።" (ወደ ኤፌሶን ሰዎች 4:29)
ትምህርቱ ጠቅሞዎታል? እንግዲያውስ እባክዎ ላይክና ሼር ያድርጉ፣ ጌታ ይባርክዎ።