ዲቮሽን
ቁ.161/07፣
ረቡዕ፥
የካቲት
11/07 ዓ.ም.
(በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)
(በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)
የአሁኑ
ሥቃያችን!
ለእኛም ይገለጥ ዘንድ ካለው ክብር ጋር ቢመዛዘን የአሁኑ ዘመን ሥቃይ ምንም
እንዳይደለ አስባለሁ (ሮሜ 8፡18)።
ወገኖች ሆይ፣ ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስን የግል አዳኛችንና መድኃኒታችን አድርገን
ተቀብለን ዳግመኛ የተወለድን አማኞች ሁሉ፣ የእግዚአብሔር ልጆች ነን! ልጆች ከሆንን ወራሾች ደግሞ ነን! ይህም ማለት ከክርስቶስ
ጋር እኩል መብት ያለን የእግዚአብሔር ወራሾች ነን!
ታውቃላችሁ፣ ወራሽነት ጸጋ ሳይሆን መብት ነው! ጌታ ኢየሱስን ተቀብለን
ዳግመኛ ስንወለድ የተወለድነው የእግዚአብሔር ልጆች ሆነን ነው! ይህ የልጅነት መብት የወላጅና ልጅ ግንኙነቱ ካልተበላሸ በስተቀር
በምንም ሁኔታ የማይቀለበስ መብት ነው!
ወገኖች ሆይ፣ ዳግም በመወለዳችን ያገኘነውን የእግዚአብሔር ልጅነት መብት
አናስብ! የልጅነት መብት ከማግኘታችን የተነሣ የተጎናጸፍነውን ከክርስቶስ ጋር አብሮ ወራሽነት
መብት አናስብ! ይህን መብት ከማግኘታችን የተነሣ ወደፊት የሚጠብቀንን ታላቅ ክብር እናስብ!
ወገኖች ሆይ፣ ወደፊት
የሚጠብቀንን ከክርስቶስ ጋር አብሮ የመክበር ታላቅ ነገር ስናስብ ታዲያ፣ ከክርስቶስ ጋር አብሮ መከራ መቀበሉንም እናስብ!
ታውቃላችሁ፣ ከክርስቶስ
ጋር አብሮ ለመክበር፣ ከክርስቶስ ጋር አብሮ መከራ መቀበልን ይጠይቃል! ታውቃላችሁ ወራሽነት ዋጋ ያስከፍላል! ወራሽነት ጸጋ አይደለምና
ሥራ ይጠይቃል! የወራሽነት ክብር ለመጎናጸፍ ከወራሾች ጋራ ሕይወትን መካፈል፣ መከራን መካፈል ይጠይቃል!
ወገኖች ሆይ፣ ከክርስቶስ ጋር አብሮ ለመክበር፣ ከክርስቶስ ጋር አብሮ መከራ መቀበልን ይጠይቃል! መከራችንን
ስናስብ፣ የወደፊቱን ክብራችንን አብሮ ማሰብ ይገባል፡፡ የአሁኑን መከራችንን ከወደፊቱ ክብራችን ጋር ማነጻጸር ይገባል፡፡ ያኔ፣
ለእኛ ይገለጥ ዘንድ ካለው ክብር ጋር ቢመዛዘን የአሁኑ ዘመን ሥቃይ ምንም እንዳይደለ ማረጋገጥ
ይቻላል!
ታውቃላችሁ፣ የፍጥረት ናፍቆት የእግዚአብሔርን ልጆች መገለጥ ይጠባበቃልና፣ ፍጥረት በሞላ እየጠበቀን
ነው! በሰው ልጆች ውድቀት ምክንያት የተጎዳው ፍጥረት፣ የሰው ልጆች ሁሉ ወደቀድሞው ክብር ሲመለሱ ለማየት ፍጥረት ሁሉ በናፍቆት
እየጠበቀን ነው!
ወገኖች ሆይ፣ ክብር እየጠበቀን ስለሆነ፣ የአሁኑ ሥቃያችንን ቻል አድርገነው
በእግዚአብሔር ጸጋ ወደፊት እንገስግስ! የአሁኑ ሥቃያችን ከሚጠብቀን ክብር ጋር ሲነጻጸር እዚህ ግባ የሚባል አይደለምና፣ ይህን
እያሰብን ሩጫችንን በትዕግሥት እንሩጥ! በኃጢአታችን ምክንያት የደረሰብንን ውርደታችንን ያየው ፍጥረት፣ ክብራችንን ለማየት እናፈቀ
ነውና ይህን እያሰብን ሩጫችንን በትዕግሥት እንሩጥ!
ወገኖች ሆይ፣ የእግዚአብሔር ልጆች ከሆንን የእግዚአብሔር ወራሾች ነን! ይህ ወራሽነት ጸጋ
ሳይሆን ሥራ ነውና፣ ከክርስቶስ ጋር አብረን እንድንከበር፣ ከክርስቶስ ጋር አብረን መከራ ለመቀበል መዘጋጀት ያሻል!