Friday, October 3, 2014

ባለ ራዕይ አይሞትም!


ዲቮሽን .8/2007 ሐሙስ፥ መስከረም 8/2007 ..
(
በፓ/ ተስፋሁን ሐጢያ)


አንዱም ለአንዱ እንዲህ አለው፥ ባለ ሕልም ይኸው መጣ፡፡ አሁንም እንግደለውና በአንድ ጉድጓድ ውስጥ እንጣለውከሕልሞቹም የሚሆነውን እናያለን (ዘፍ 3720)

ጠላታችን ዲያብሎስ ባለ ራዕዮችን ለማጥፋት ዘወትር እንደጣረ ነው፡፡ በነፍሳቸው ላይ በመሸመቅ፥ ጉድጓድ በመቆፈር፥ ልዩ ልዩ መሰናክሎች በማስቀመጥ፥ ክፉ ነገሮችን ሁሉ በማድረግ እቅዱ እንደሚሳካለት ተስፋ ያደርጋል፡፡

ነገር ግን ጠላታችን ሁሌም እንዳፈረና እንደተዋረደ ነው! እግዚአብሔር ሕዝቡን አይጥልምና እቅዶቹ ሁሉ እየከሸፉበት ውርደት እንደተከናነበ ነው፡፡ ጠላት በባለራዕዮች ላይ የሚያስበው ክፉ ምኞት ሁሉ ወዳልተጠበቀ የምስራች እንደተቀየሩበት ነው፡፡ ሞትን ሲያቅድ ወደ ሕይወት ይበወዝበታል፡፡ የውርደት ቅዠቱ ወደ ክብር ይለወጥበታል፡፡ የባርነት እቅዱ ወደ ዙፋን ይቸኩልበታል፡፡ ረሀብ በጥጋብ፥ ለቅሶ በዝማሬ፥ ሐዘን በደስታ ይተካበታል!

ባለራዕይ አይሞትም! የሞት ድግስ ቢደገስበት፥ ነጋሪት ቢጎሰምበት፥ እምቢልታ ቢነፋበትባለራዕይ አይሞትም! ጠላት በባለራዕይ ላይ ከበሮ ቢደልቅ፥ ጸናጽል ቢያንሿሿ፥ ዋሽንት ቢነፋ፥ በገና ቢደረድር፥ ጥሩንባ ቢነፋ፥ ፉከራ ቢያበዛ፥ ጉራውን ቢነዛባለራዕይ አይሞትም፥ አይጠፋምም!!

ጠላት ባለራዕዮችን ከምድር ላይ ሊያጠፋ የሚፈልግበት ምክንያቱ ለምን ይመስላችኋል? አንድ ሺህ አንድ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ጥቂቶቹን ላንሳ፡፡ ባለራዕዮች ከጠፉ ራዕይ ይጠፋል፡፡ ራዕይ ከጠፋ ደግሞ ሕዝብ መረን ይሆናል፡፡ ባለራዕዮች ከምድር ላይ ከጠፉ ምድር ራሷ በቀላሉ ትጠፋለታለች! ይህ እንዳይሆን ባለራዕይ እይጠፋም፥ አይሞትምም!!

(ይህን ዕለታዊ ዲቮሽን ላይክ ያድርጉ፥ ለወዳጅ ጓደኞችዎም ያስተላልፉ)

ወቅታዊ የምሪት ቃል (ካይሮስ-ሬማ)!


ዲቮሽን .7/2007 ረቡዕ፥ መስከረም 7/2007 ..
(
በፓ/ ተስፋሁን ሐጢያ)


አቤቱ ሌሊቱን ሁሉ አድረን ስንደክም ምንም አልያዝንም፥ ነገር ግን በቃልህ መረቦቹን እጥላለሁ፡፡ ይህንም ባደረጉ ጊዜ እጅግ ብዙ ዓሳ ያዙ፥ መረቦቻቸውም ተቀደዱ (ሉቃ 55-6)

ከጌታ ደቀመዛሙርት መካከል እነ ስምዓን ጴጥሮስ፥ ወንድሙም እንድሪያስ፥ የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና ወንድሙ ዮሐንስ የአሳ ማስገር ስራ ልሂቃን (ኤክስፐርቶች) ነበሩ፡፡ ሌሎቹም በገሊላ ባህር አካባቢ ተወልደው ያደጉ ጥሩ የስራ ልምድ ያላቸው ነበሩ፡፡

ነገር ግን ሌሊቱን ሙሉ አንድም ዓሳ ሳያገኙ አነጉ፡፡ ድካማቸው ከባድ ነበር፡፡ ወይ ከእንቅልፋቸው ወይ ከዓሳቸው ሳይሆኑ በኪሳራ ያደሩ አጥማጆችን ነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያገኛቸው፡፡

ሌሊቱን ሲለፉ ባደሩበት በዚያው ባህር ላይ "መረባችሁን ጣሉ" ሲላቸው፥ እንደ ባለአዕምሮና በሙያውም ላይ እውቀትና ልዩ ችሎታ እንዳላቸው ሰዎች "አይ፥ እኛ እናውቃለን፥ አይሆንም፡፡" በማለት መቃወም ይችሉ ነበር፡፡

ነገር ግን ተናጋሪው ጌታ ነውና የራሳቸውን ሰዋዊ "ሎጂክ" ትተው፥ ለጌታ ወቅታዊ የምሪት ቃል ታዘዙ፡፡ የእነርሱ እውቀትና ልምድ ይህንን መንገድ እንዲከተሉ ባይፈቅድም፥ የሰሙት ቃል ሞኝነት ቢመስልም፥ ነገር ግን ጌታ ቃል ተናግሯልና እንዳላቸው አደረጉ፡፡ ሌሊቱን ሙሉ ሲያለፋቸው ያደረው ባህር ታዲያ ጌታ ቃል ተናግሯልና ታዘዘ፡፡ የዓሳ ክምርም ተፋ! መረባቸው እስኪቀደድ ድረስና የሌሎች ሰዎችን እርዳታ እስኪጠይቁ ድረስ የአሳ ምርት ተትረፈረፈ፡፡

ታውቃላችሁ፥ ወቅታዊ የምሪት ቃል ከድካም ያድነናል፡፡ እውቀታችን፥ ልምዳችን፥ ሎጂካችንሁሉ ሊሰጠን የማይችለውን በረከት ያጎናጽፈናል፡፡

መንፈሳዊ ሰው በራሱ ችሎታ ከመደገፍ ይልቅ በጌታ የምሪት ቃል መደገፍ የተሻለ መሆኑን ያውቃል፡፡ "ልፋ ያለው አንድ እንጨት ያስራል" እንዲሉ፥ የጌታን ወቅታዊ ምሪት ከመቀበል ይልቅ በራስ ችሎታ መደገፍ ከትርፉ ድካሙ ያመዝናል፡፡ ይህ እንዳይሆን፥ ድምጹን መስማት ይሁንልን፡፡

መንፈሳዊ ሰው ወቅታዊ መለኮታዊ የምሪት ቃል (ካይሮስ-ሬማ) ያስፈልገዋል! ከእግዚአብሔር የሆነ ወቅታዊ ቃል ከብዙ ድካምና ኪሳራ ያድናል፡፡ እግዚአብሔር ሕያው መሆኑን ካመንን፥ ጊዜ የማይለውጠው አምላክ መሆኑን ካመንን፥ መንፈስ ቅዱስ ዛሬም ስራ ላይ መሆኑን ካመንን፥ ወቅታዊ ምሪት ሊሰጠን እንደሚችል ደግሞ ማመን ይገባናል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና ዛሬ እስከ ለዘላለምም ያው ነው፡፡

(ይህን ዕለታዊ ዲቮሽን ላይክ ያድርጉ፥ ለወዳጅ ጓደኞችዎም ያስተላልፉ)