Wednesday, July 22, 2015

አለማመናችንን እርዳ!!!!!!

ዲቮሽን 315/07፥ ረቡዕ፥ ሐምሌ 15/07 ዓ/ም
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)

አለማመናችንን እርዳ!!!!!!

አምናለሁ፣ አለማመኔን እርዳ። ማርቆስ 9፡ 24

የእምነት ነገር በጣም ከባድና ሐሳባዊ ሆኖባችሁ ያውቅ ይሆን? በተለይም በጣም በሚያስፈልጋችሁ ነገር ላይ፣ በጣም በጉጉት በምትጠብቁት ነገር ላይ፣ ጌታ በተደጋጋሚ እየተናገራችሁ ለእናንተ ግን ርቆባችሁ ይሆን? ጌታ ከተናገራችሁ ነገር በተቃራኒው በሕይወታችሁ እየሆነ ይሆን?

ሕይወታችሁን በቅድስና እየመራችሁ፣ ቃሉ እንደሚላችሁ እየተመላለሳችሁ፣ በሥፍራችሁ ሆናችሁ ሳለ፣ ነገሮች ግን እየተበላሹባችሁ ይሆን? እግዚአብሔርን ከመጠበቅ የተነሳም የመዛልና የስፍና ነገርስ ይሰማችሁ ይሆን? “ስለማታምኝ ነው/ ስለማታምን ነው እግዚአብሔር የተናገረሽን/ የተናገረህን ያልመለሰላችሁ” ተብላችሁስ በወገኖች ተመክራችሁ ይሆን?

እንግዲህ ነገሩ ካለማመናችን ከሆነ ለምን ተስማምተን አንጸልይም? እንዲህ በማለት፣ አብ አባት ሆይ፣ እኔ የማውቀው ማመኔን ነው፣ እኔ የማውቀው አንተን ተስፋ ማድረጌን ነው፣ ነፍሴ የምትመሰክርልኝ ኤልሻዳይነትህን ማመኔን ነው። ደግመህ ደጋግመህ በልዩ ልዩ መንገድ የተናገርኸኝ ነገር ያልሆነው ካለማመኔ ይሆንን? ወደጄ ሆይ፣ እባክህ አለማመኔን እርዳ። በድካሜ ላይ ተገለጥ፣ ጥርጣሬየን የመንፈስህ እሳት ይብላውና፣ ዛሬ በአዲስ እምነትና ኃይል ሙላኝ። ባለፈው ዘመኔ ሁሉ እንዳደረከው፣ እለምንሃለሁ፣ በወደድከው፣ ባከበርከው በልጅህ በኢየሱስ ስም እለምንሃለሁ፣ አለማመኔን እርዳ። ወደ ፈቃድህም አስገባኝ። ሰምተህኛልና ተባረክ።
--------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 51 ቀን ቀርቶታል፡፡

አንድም አልጠፋብኝም!!!!

ዲቮሽን 314/07፥ ማክሰኞ፥ ሐምሌ 14/07 ዓ/ም
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)

አንድም አልጠፋብኝም!!!!

ከሰጠኸኝ ከእነዚህ አንድም አልጠፋብኝም። ዮሐ 18፡9

ጌታን ካገኘን ጀምሮ እግዚአብሔር ወደ ሕይወታችን ያመጣቸው እጅግ ዓይነት በርካታ ሰዎች ይኖራሉ። የኛ ሕይወት አመቺም በሆነ መንገድ ይለፍም አይለፍም፣ የኛ ጸሎት ይመለስም አይመለስም፣ ክርስቲያን በመሆናችን ብቻ አምነውን ለእርዳታ ወደ እኛ የመጡ ብዙ ወንዶችና ሴቶች፣ ታናናሾች እና ታላላቆች ይኖራሉ።

ምክራችንን፣ ጸሎታችንን፣ ገንዘባችንን፣ እንክብካቤያችንን፣ ጊዜያችንን .... ፈልገው “እሱ አለ/እሷ አለች” ብለው የፈለጉንን ሰዎች የት አድርሰናቸው ይሆን? የክርስትና ሕይወት አቀበት ሲሆንብን መንገድ ላይ ጥለናቸው ይሆን?
ሲርበን፣ ሲጠማን፣ ስንታረዝ፣ በሕይወታችን ላይ ሰልፍ ሲበዛብን የራሳችሁ ጉዳይ ብለን አባረናቸው ይሆን?

እግዚአብሔርስ እነዚያን ሰዎች ያለነገር ወደ ሕይወታችን ዝምብለው ያመጣቸው ይመስላችኋል? ከፍቷቸው፣ ሆድ-ብሷቸው፣ ማልቀስ አምሯቸው እኛን ከሰው ሁሉ መርጠው የተጠጉንን ሰዎች የት አድርሰናቸው ይሆን?

እግዚአብሔር ሌላ ወገን ሰጣቸው ይሆን? ወይስ የሚያነሳቸው ጠፍቶ ተንከራተው ቀርተው ወይም ሞተው ይሆን? ምናልባት ጌታስ ድንገት ቢጠይቀን፣ እንደ ኢየሱስ፣ “ከሰጠኸኝ ከእነዚህ አንድም አልጠፋብኝም” ዮሐንስ ወንጌል 18፡9 የማለት ኃይል ይኖረን ይሆን? መልሱን ለእያንዳንዳችሁ ልተወው። ዛሬም ሌላ ቀን ነውና፣ ግን ካሁን በኋላ ልብ እንበል።

አባት ሆይ፣ በአንድም በሌላም ምክንያት ወደእኛ ያመጣሀቸውን ሰዎች አባርረናቸው እንደሆነ፣ ወይም በራሳችን ጉዳይ ተጠምደን፣ የነፍሳትን ነገር ችላ ብለን እንደሆነ፣ ወይም ስልካችንን እያጠፋን፣ በመንገድም አይተን እንዳላየን አልፈናቸው እንደሆነ፣ በውጤቱም የእነዚያ ሰዎች ሕይወት ተበላሽቶ እንደሆነ፣ ዛሬ እለምንሀለሁ፣ እኛንም ይቅር በለን፤ እነሱንም ከወደቁበት የሚያነሳውን መንፈስህን ላክላቸው። ሰምተህኛልና ተባረክ።
--------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 52 ቀን ቀርቶታል፡፡

ባለስልጣን!!!!

ዲቮሽን 313/07፥ ሰኞ፥ ሐምሌ 13/07 ዓ/ም
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)

ባለስልጣን!!!!

ስልጣን ከሰማያት እንደሆነ ካወቅህ በኋላ መንግሥትህ ይቆይልሃል። ዳንኤል 4፡27

የመጨረሻው ዘመን አሠራር እጅግ በረቀቀ እና በተወሳሰበ ስልት ሕይወታችን እያመሰ ያለበት ወቅት ላይ ነን። አማኝ ነን ለምንል ለእኛም ቋንቋችንን እየደበላለቀ፣ እርስ በርሳችን ለእግዚአብሔር ቤት ሥራ እንዳንተጋ ያደረገበት ወቅት ነው።

በሚያልፍና በሚጠፋ ነገር ውስጥ ተተብትበን፣ የክርስቶስን ሰላም እንደ ቀላል ያቃላለንበት ወቅት ነው አሁን። አንዳንዴ ራሳችን ለራሳችን ምን ነክቶኝ ነው እንዲህ የሆንኩት? እስክንል ድረስ በማይገባን ሥፍራ፣ የማይመጥነን ስራና አመል እያሳየን፣ ትእግስት እየጎደለን፣ ስንባዛን ራሳችንን እናገኘዋለን።

በቤተክርስትያንም ያለው አሠራር ደስ የሚያሰኘውንም ያህል፣ ልብን የሚያዝል ነገር አለው። አልፎተርፎም እግዚአብሔር አለ ወይስ የለም? በዚህ ጊዜ ምን እየተከናወነ ነው? ለኔስ ሆነ ለቀሪው ቤተሰቤ፣ ለራእየና ለሀገሬ ምን ተስፋ አላት? እያልን በተስፋ መቁረጥ ውስጥ የምንመላለስበት ሰዓት ነው አሁን። አንድ ነገር እነግራችኋለሁ፣ እግዚአብሔር አለ። እየሆነ ያለውንም ነገር ሁሉ ያውቀዋል። የተበላሸ የቤተክርስትያናችንንም ሆነ የሕይወታችንን ክፍል ያውቀዋል። መፍትሔ ፍለጋም ወደቀኝ እና ወደግራ ስንባክንም ያውቀዋል። የጨለማው ገዢ በመጨረሻው ሰዓት ትንቅንቅ ላይ ስለሆነ ራሳችሁን ባልተገባ ቦታ ላይ ብታገኙት አይግረማችሁ።

ስልጣን ያለው በሰማይ ነው። የሰማይና የምድር ፈጣሪ አንድ እግዚአብሔር ይደርስልናል። እኛ ብቻ በድካምም ውስጥ ብንሆን፣ አባት ሆይ እባክህ ዓይኖቼን ክፈት እያልን እንጸልይ። ወደ ቀኝ ወደ ኋላ ማለታችንንም ትተን ወደሰማይ ብቻ እንመልከት። እጅ እንስጥ። መፍትሔ ያለው ከሰማይ ነው። መላ ያለው ከአብ ዘንድ ነው። ከሌላ ከየትም የለም። እኛ ስልጣን ከሰማይ መሆኑን እንወቅ እንጅ፣ እኛ እግዚአብሔርን እንፈልገው እንጠጋጋው እንጅ፣ እንጠጋጋው እንጅ፣ ያን ጊዜ የተዝረከረከው ነገር ሁሉ ቦታ ቦታውን በራሱ ጊዜ ይይዛል።

አባት ሆይ፣ ግሩም መካሪ ስለሆንክልን ተባረክ። ወዳጅ ሆይ ስምህ ለዘላለም ይባረክ። መንፈስቅዱስ ሆይ፣ ባስጨነቁን ላይ በእሳት ስለምትገለጥ ተባረክ። ሰምተህኛልና ተባረክ።
--------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 53 ቀን ቀርቶታል፡፡

አወሩ!!!!!

ዲቮሽን 312/07፥ እሁድ፥ ሐምሌ 12/07 ዓ/ም
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)

አወሩ!!!!!

እግዚአብሔርም ከእነርሱ ጋር ያደረገውን ሁሉ አወሩ። ሐዋ 15፡ 4

በዘመናችን ጌታ ያደረገልን ነገር ብዙ ነው። ጠላቶቹ ስንሆን ወዳጅ አድርጎን፣ ውሸተኛ ስንሆን በልጁ በኢየሱስ እውነት ሸፍኖን፣ በሽተኞች ስንሆን በመገረፉ ቁስል ፈውሶን፣ ከርታቶች ስንሆን በእቅፎቹ ይዞን፣ የማንመች ለሆንነው ለኛ፣ የሚመች ሆኖ፣ ለሚቆረቁረው ማንነታችን የማይቆረቁር ስሙን ሰጥቶን፣ ሌቦች፣ ዘማውያን፣ ተሳዳቢዎች ስንሆን... ተሸክሞን ይኼው አለን።

እስከዛሬ ድረስ፣ እሳከሁኗ ደቂቃ ድረስ፣ ያለነው ጌታ ተጠንቅቆልን ነው። መንገድ የጠፋን ቅብዝብዞች ሆነን እያለ፣ መንገድ ሆኖልን። በምድረበዳው፣ በሐሩር እና በቁሩ፣ በዳገት እና ቁልቁለቱ፣ ሰለቸኝ ደከመኝ ሳይል፣ እዚህ ያረሰን እግዚአብሔር ነው። ጠላት ሊያበራየን ሲመጣ፣ ጌታ ከልክሎልን እስካሁኗ ሰከንድ ድረስ አለን።

ታዲያ ዛሬ ለገጠመን ነገር እንዴት እንዴት ምንም እንዳልተደረገለት ሰው ጨለማ ይውጠናል? ታዲያ ዛሬ ላላንበት ነገር እንዴት ልባችን ይዝላል? በጉልበታችን፣ በእውቀታችን፣ በገንዘባችን አልኖርንም አይደል? ስለዚህ፣ አይዞን፣ አይዟችሁ። ድብርት፣ ተስፋ መቁረጥና፣ አዚም ሲጫጫናችሁ/ ሲጫጫነን እንዲህ አድርጉ። እግዚአብሔር በሕይወታችሁ ላይ ያደረገላችሁን ነገር ተጨዋወቱት።

ብቸኝነት ይዟችሁ፣ የምታካፍሉት ሰው ከሌላችሁ እንኳን፣ ወደ ሰማይ ቀና ብላችሁ አሰላስሉት። አስቡት። ለልቦናችሁ ንገሩት። እርግጠኛ ሆኜ የምነግራችሁ፣ ያ የምሕረት አምላክ አላረጀም፣ አልደከመም፣ አልሰለቸም። በደጅ ነው። በርቱ።
አባት ሆይ፣ ስለሰማህኝ አመሰግንሀለሁ። በእርግጥ ያደረክልን ነገር ብዙ ነውና እሱኑ እንድንጨዋወተው እንድናሰላስለው ስለመከርከን ተባረክ። ሰምተህኛልና ተባረክ።
--------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 54 ቀን ቀርቶታል፡፡

ሰላምን ያደርጋል!!!!!

ዲቮሽን 311/07፥ ቅዳሜ፥ ሐምሌ 11/07 ዓ/ም
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)

ሰላምን ያደርጋል!!!!!

የሰው አካሔድ እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘ እንደሆነ፣ በእርሱና በጠላቶቹ መካከል ስንኳ ሰላምን ያደርጋል። ምሳሌ 16፡7
አንዳንድ ጊዜ በሕይወት መንገድ ላይ በብዙ ጉዳዮች ተጠምደን እንውላለን። በዚህ በማሕበራዊ መስተጋብራችን ውስጥም የተለያዩ ዓይነት ሰዎች ያጋጥሙናል። የሚወዱን፣ የሚጠሉን፣ ሐሳባችንን የሚደግፉ፣ ሐሳባችንን የሚቃወሙ፣ በገንዘም ሆነ በምክር የሚረዱን ወይም ደግሞ ያለንንም ነገር ቢሆን የሚወስዱብን፣ ልባችን የሚያርፋባቸው፣ ወይም በነገር እና በሐሜት ልባችንን የሚያደሙ .... ብቻ እጅግ በርካታ አይነት ሰዎች ይገጥሙናል።

በዚህ ጋጋታ ውስጥም ይህ አመጸኛ ስጋችን አንዳንዴ በስሜታዊነት ጎል ያስገባንና ለሰዎች መጫወቻ እንሆናለን። ጉዳይ ልናስፈጽም ብንል እየተሳደብን፣ መልእክት እናድርስ ብንል እየተቆጣን፣ ብቻ ግራ ያጋባናል-ይህ ስጋችን። ያን ጊዜ፣ ሰዎች እንኳን ሊታገሱን እስከማይችሉ ድረስ ይጸየፉናል፣ ወይም ደግሞ ይጠሙብናል። ክብር ለመንፈስቅዱስ ይሁንና፣ ወጀቡም ማእበሉም ሲያንገላታን አጽናኛችን አይጥለንም፤ ወደ ቃሉ ይመልሰናል።

ከዚያም በሁሉ ሙሉ የሆነው ንጹህ የእግዚአብሔር ቃል ይመክረናል፤ እንዲህ ሲል፣“ የሰው አካሔድ እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘ እንደሆነ፣ በእርሱና በጠላቶቹ መካከል እንኳን ሰላምን ያደርጋል”። ምሳሌ 16፡7

እንዲህ ያለ ነገር ገጥሟችሁ ያውቅ እንደሆነ ግዴላችሁም ወደ ቃሉ ተመለሱ። ጌታ ለዘላለም ስለማይጥለን ከእሱ ጋ እንስማማ፣ ደስ የሚያሰኘውንም እንፈልግ፣ ያን ጊዜ ብልሽትሽቱ የወጣው ማሕበራዊ ሕይወታችን፣ የሥራ ሁኔታችን፣ የጠሉን ሰዎች ሁሉ በስምምነት ከእኛ ጋር መኖርና መስራትን ይፈቅዳሉ።

ባባዬ፣ ደግ ነህና እወድሀለሁ። ደግ ስለሆነው ቃልህም ተባረክልኝ። ቁጥር ስፍር ስለሌለው ምክርህም አመሰግንሀለሁ። ሰምተህኛልና ተባረክ።
--------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 55
ቀን ቀርቶታል፡፡