ዲቮሽን 340/07፥ እሁድ፥ ነሐሴ 10/07 ዓ/ም
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)
ጵኒኤል ሆነልን!!!
እግዚአብሔርን ፊት ለፊት አየሁት፣ ሰውነቴም ድና ቀረች። ዘፍ፡ 32፤30
እንግዲህ ጨዋታችን ከፍ ብሏል። ወጋችን ተቀይሯል። አሁን ዋናውን አገኘን። እነ ሎጥን ተለማምጠን ስናስወግድ፣ እነ ላባን እግሬ አውጭኝ ብለን ስናመልጥ፣ እነ ዔሳውን እዛው በሩቁ ብለን ስናርቃቸው፣ ቋንቋችን ሁሉ ተቀየረ። አልፈን ተርፈን ከእግዚአብሔር ጋር እኩል ማውራት ጀመርን። እረ መታገልም ጀመርን። ሪስሊንግ ነገር ሞካከርን!!!!
በሰው ልማድ ቀረ፣ የሚለው ቃል አሉታዊ ነው። እከሌ እንዴት ሆነ? ሲባል፣ ታሞ ቀረ፣ ወይም ድሃ ሆኖ ቀረ፣ ጎስቁሎ ቀረ። ሳይሆንለት ቀረ። ወ.ዘ.ተ. ነው የሚባለው።
አሁን ግን እኛ ድነን ቀረን። ቡቱቱ ኮልኮሌያችን ጋር መጓተት ስናቆም፣ በቃ እግዚአብሔርን ፊት ለፊት አገኘነው። እሱም ቁርጠኛ መሆናችንን ፈተነን፤ የወዳጅ ትግል ታገለን።
እውነት ወስናችሁ ከሎጥ ተለያችሁ? ከላባስ የምር ኮበለላችሁ? ዔሳውንስ ሸኛችሁት፣ አለና እንግዲያማ፣ አሁን ሌላ ስም ይውጣላችሁ ብሎ፡ እስራኤል ተባልን።
አሁን ጠላት ቢፈልገን መታወቂያችን ስለተቀየረ ጎረቤትን ሁሉ አይታችኋል ቢባሉ፣ አንገኝም። ምክንያቱም የጥንቱ ስማችን ተቀየረ። በድሮ ስማችን አገር ቢታሰስ የለንም፣ አንገኝም። ስም ከሰማይ ወጥቶልናል። ናፍቆታችንን አገኘነውና በሁሉም አቅጣጫ ድነን ቀረን። ጵኒኤል ሆነልን!!!!!
ሁልጊዜ እግዚአብሔርን በፊቴ አየዋለሁ፤ በቀኜ ነውና አልታወክም። ስለዚህ ልቤን ደስ አለው። ምላሴም ሐሤት አደረገች። ሥጋዬም ያለ ሥጋት ዐርፎ ይቀመጣል። መዝ 16፡8-9
---------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 26 ቀን ቀርቶታል
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 26 ቀን ቀርቶታል
No comments:
Post a Comment