Sunday, August 30, 2015

ማልጄ እነሳለሁ!!!!

ዲቮሽን 355/07፥ ሰኞ፥ ነሐሴ 25/07 ዓ/ም (በእህት ማርታ ሲሳይነህ) ማልጄ እነሳለሁ!!!! በገናም መሰንቆም ተነሱ፤ እኔም ማልጄ እነሳለሁ። እግዚአብሔር ሆይ በሕዝብ መካከል እዘምርልሃለሁ። መዝ 108፡2 ታዲያ የሰላም እንቅልፍ ለሰጠን ለእግዚአብሔር ማለዳ ደግሞ እንነሳና እናመሰግነዋለን። አዲስ ዝማሬ እኮ ነው ሌሊት በአፋችን የጨመረው! ለፈዋሻችን፣ ለአዳኛችን፣ ነቀፌታችንን ላስወገደው ለእግዚአብሔር! ነፍሳችንን ከወህኒ ላወጣት፣ በተዘጋው ቤታችን ገብቶ ሰላም ለእናንተ ይሁን ብሎ ሰላሙን ላፈሰሰብን፣ መዋረዳችንን ላየው፣ እንባችንን ለዘላለም ላበሰው ለኢየሱስ! አዲስ ዝማሬ!!! ቀስቃሽ ሰው አንፈልግም አሁን! እስራታችን ተበጥሶ፣ ወጥመዱ ተሰብሮ እኛም አምልጠን በዓይናችን ያየን ሰዎች እኮ ነን! ስለዚህ ዛሬ የማንንም ፈቃድም፣ ይሁንታም አንፈልግም፣ ማልደን እንነሳለን! አዲስ መዝሙር፣ አዲስ ምስጋና እናቀርብለታለን! አሁን ለሃጢያት፣ ለእርኩሰት ጊዜ የለንም! አሁን መካኒቱ ሰባት ወልዳለች፣ እያልን ነው የምንዘምረው። ከፍ ከፍ ብሎ ከብሮአልና፣ ለእግዚአብሔር እዘምራለሁ፣ ፈረሱንና ፈረሰኛውን በባህር ውስጥ ጥሎአልና! እያልን እንዘምራለን። አሁን ለልቅሶ ጊዜ የለንም! ይልቅስ ነቀፌታዬን ከሰው መካከል ያስወግድልኝ ዘንድ ጌታ በተመለከተበት ወራት እንዲህ አድርጓልና፣ እያልን እንዘምራለን!!!! ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች፣ መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴት ታደርጋለች፣ የባሪያይቱን ውርደት ተመልክቷልና፣ ብርቱ የሆነ እርሱ በኔ ታላቅ ስራ አድርጎአልና፣ ስሙም ቅዱስ ነው፣ ምሕረቱም ለሚፈሩት እስከ ትውልድ ትውልድ ይኖራል እያልን። እንዘምራለን። ያልጠፋነው ከእግዚአብሔር ምሕረት የተነሳ ነው። ርኅራኄው አያልቅምና፣ ማለዳ ማለዳ አዲስ ነው፣ ታማኝነትህ ብዙ ነው። ሰቆ ኤር 3፡2 --------- ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 11 ቀን ቀርቶታል

No comments:

Post a Comment