Sunday, June 21, 2015

ምርኮን ተካፈለች

ዲቮሽን 285/07 ሰኞ፣ ሰኔ 15/07
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)
ምርኮን ተካፈለች
በቤትም የምትኖር ምርኮን ተካፈለች። መዝ 68፡ 12
ከእግዚአብሔር ጋር በሚኖረን ሕብረት፡ አንዳንዴ መልካም የምንላቸው ጊዜያት፣ አንዳንዴም ከባድ የምንላቸው ወቅቶች ይኖራሉ። አንዳንዴ በበረከት ላይ በረከት እየተደራረበልን ለመቁጠር ያስቸግረናል፣ አንዳንዴም በፍጹም ማጣት እና መራቆት ውስጥ እናልፋለን። አንዳንዴ በምስጋናና በዝማሬ ስንጥለቀለቅ አንዳንዴም በልቅሶና በፍርሃት፣ እንሰጥማለን።
አንዳንዴ ደግሞ፣ በእምነት ስንሞላ አንዳንዴም ደግሞ በጥርጣሬና በስጋት እንዋጣለን። አንዳንዴ ደግሞ በሞገስ ስንወጣ፣ አንዳንዴ ደግሞ በውርደት አንገታችንን እንደፋለን።
ሞላም ጎደለ ግን ዋናው ነገሩ፣ ስንችል እየዘመርን፣ ሲያቅተን እያለቀስን፣ ሲሆንልን በብርታት፣ ሳይሆንልን በድካም፣ ሲደላን እየበረርን፣ ሳይደላን በእንብርክካችን ሆነን፣ በጌታ ቤት፣ በመንፈሱ አፀድ ውስጥ መገኘትን የመሰለ ትልቅ ቁምነገር የለም።
ምክንያቱም፣ አንድ ቀን፣ ጌታ ልጆቹን ሊያስብ በሚመጣበት ቀን፣ ምርኮ ተካፋዮች መሆናችን የማይቀር እውነት ነው። ጌታ በእርግጥ፣ ወደ እያንዳንዳችን ነገር መምጣቱ አይቀርም። ዛሬ ላይ፣ ይህ ነገር እውነት ባይመስለንም፣ በእርግጥ ጌታ መምጣቱ አይቀሬ ነው። ያኔ ግን፣ በቤቱ መገኘት ይሁንልን።
ጌታ ልጆቹን ሊጎበኝ ሲመጣ እንዳያጣን፣ በቤቱም የተገኙት ምርኮ ሲካፈሉ፣ እኛ በደጅ እንዳንቀር፣ የበረከት ዝናብ መውረዱንም በዝና ብቻ ሰሚዎች ሆነን፣ ተካፋዮች ሳንሆን ግን እንዳንቀር፣ በምንም ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ብንሆን፣ በቤቱ ውስጥ እንገኝ።
አባት ሆይ፣ ሁሉን ታደርግ ዘንድ ቻይ ነህና፣ ዛሬ፣ የተፍገመገምነውን ሁሉ፣ በክንፎችህ ጥላ ውስጥ ሸሽገን። ሰምተህኛልና አመሰግንሃለሁ።
ትምሕርቱ ጠቅሞዎታል? እንግዲያውስ፣ እባክዎ ላይክ፣ ሼር
እና ኮሜንት ያድርጉ፤ ጌታ ይባርክዎ።

ዲቮሽን ይቋረጥ ወይስ ይቀጥል? A) ይቋረጥ B) ይቀጥል

ማስታወቂያ፣

ዲቮሽን ይቋረጥ ወይስ ይቀጥል?
A) ጠቃሚ ስላልሆነ ይቋረጥ
B) ጠቃሚ ስለሆነ ይቀጥል

መረጥሁ!!!

ዲቮሽን 284/07 እሁድ፣ ሰኔ 14/07
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)

መረጥሁ!!!

በእግዚአብሔር ቤት እጣል ዘንድ መረጥሁ። መዝ 84፡ 10

መቼም በዚህ ምድር ላይ ያለ ነገር ሁሉ አላፊ ነው። ወይ እኛ እናልፋለን፣ ወይም ያ የጓጓንለት ነገር ያልፋል፣ በመጨረሻም ሰማይና እና ምድር እንኳን ያልፋሉ። ብቻ ምናለፋችሁ፣ በዚህ ምድር ላይ ቋሚ የሆነ አንዳችም ነገር የለም።

ስለዚህ፣ ዛሬ፣ ለዚህ ምድር ሆይ ሆይታ እና አጓጓል ድንዛዜ፣ ምኞት እና ግርግር ልዩ የሆነ “እምቢ ለእርኩሰት” የሚያሰኝ የጭካኔ መንፈስ እንዲገባብን እኔ እጸልያለሁ።

ዳዊት በኃጥአን ድንኳኖች ከመቀመጥ ይልቅ፣ በእግዚአብሔር ቤት እጣል ዘንድ መረጥሁ፣ ያለው እኮ፣ “ጸሎቴም ባይመለስ፣ የምፈልገውን ዝናና ክብርም ባለገኝ፣ በድህነት በበሽታም ብኖር፣ በማጣት በጉስቁልናም ብመታ፣ በውርደትና በነቀፌታ ብመላለስም፣ የምፈልገውን የአገልግሎት ደረጃና ስልጣን ባላገኝም፣ ያማረኝን ባልለብስና ባልጠጣም፣ አሪፍ መኪናና ቤት ባይኖረኝም፣ ሰዎች የሚገባኝን ከበሬታ ባይሰጡኝም፣ የያዝኩት ሁሉ ከእጄ ቢበተን፣ . . . ሌላ ቦታ ሄጄ፣ ይህን ሁሉ ከማገኝ፣ ከአምላኬ ጋር ተስማምቼ፣ ፈቃዱን ብቻ አድርጌ፣ ደስ የሚያሰኘውን ነገር ብቻ ሆኜለት፣ ህይወቴ ትለፍ” ማለቱ ነው እኮ።

ደግሞስ፣ እውነት እንነጋር ከተባለ ማነው እግዚአብሔርን ተደግፎ፣ አምኖና ተመርኩዞ ከበጎ ነገር ሁሉ የጎደለ! ዳዊት ይህን ሲል እኮ፣ እግዚአብሔርን በደንብ አድርጎ ስለሚያውቀው፣ አንዳችም ነገር እንደማያጣ አውቆም ጭምር ነው።
ወዳጅ መንፈስ ቅዱስ ሆይ፣ ዛሬ አእምሯችንን አይናችንን ልባችንን እጃችንን እግራችንን . . . ሁለንተናችንን ትቆጣጠር ዘንድ በኢየሱስ ስም ጸለይኩ። ሰምተህኛልና ተባረክ። አሜን።

ትምህርቱ ጠቅሞዎታል? እንግዲያውስ እባክዎ ላይክ እና ሼር ኮሜንትም ያድርጉ፤ ጌታ ይባርክዎ።

እየጨመረ የሚሄድ ሕይወት

ዲቮሽን 283/07፥ ቅዳሜ፥ ሰኔ 13/07
(በዶ/ር በቀለ ብርሃኑ)

እየጨመረ የሚሄድ ሕይወት

የጠለቀ መንፈሳዊ ጉዞ ለመጓዝና እየጨመረ የሚሄድ ርካታና እረፍት እንድናይ ካስፈለገ፣ የክርስትና ሕይወት ትጋትን ይጠይቀናል(ዕብ 4:11)፡፡ ትጋታችን በጨመረ ቁጥር፣ የእግዚአብሔር ጸጋ በሕይወታችን እየጨመረ ስለሚሄድ፣ ለመንፈሳዊ ነገር ያለን መሻት እያደገ ይሄዳል፡፡

በእንደዚህ ዓይነት ግሥገሣ ውስጥ ባለማሰለስ ስንገኝ፣ እሱን ለማወቅ ያለን ራብ እየተለቀ ስለሚመጣ፣ እየጨመረ ለሚሄድ ፍለጋ እንጠናከራለን፡፡ ይህንን በእንግሊዝኛው አገላለጽ positive vicious cycle ይሉታል፡፡ ማለትም ትጋቱ የጨመረ መንፈሳዊ ራብን ይወልዳል፤ የጨመረ መንፈሳዊ ራብ ደግሞ ሌላ ከፍ ያለ ትጋትን ይወልዳል - መቸም ኡደቱ ማቆሚያ የለውም እኛ በሥጋዊ አካሄዶች እስካላጠፋነው ድረስ!

እየጨመረ የሚሄድ የክርስትና ሕይወት ብዙ ግብዓቶችን ይፈልጋል፡፡ መልካም የእምነት ውጊያንና ዲያቢሎስን በኃይል ጸንቶ መቃወም ይጠይቃል፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል ሳይታክቱ ማሰላሰልና በፊቱ ጥሩ የሆኑ ጊዜዎችን ማሳለፍ ግድ ይለናል፡፡ ሁኔታዎችንና ሥጋችንን ሳናዳምጥ የሚከፈሉ ዋጋዎችን እንደ ጌታ ፈቃድ መክፈልን ይጠይቀናል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ ሕይወቴን የቀየረና ብዙ ቦታ ደጋግሜ የምጠቅሰውን መርሕ እዚህ ጋ ልጥቀስ፡፡ ሦስት በተሰናሰለ መንገድ የተቀመጡ ድርጊቶች በውጤት ሂደት እንዲህ ተቀምጠዋል፡-

ድርጊት(Action)------->ልማድ(Habit)------->ጠባይ(character)
ይህንን መርሕ ለመግለጽ ጸሎትን እንደ ምሳሌ ልውሰድ፡፡ ጸሎትን ደጋግመን ስናደርገው ወደ ልማድነት ይቀየራል፡፡ በሕይወታችን ልማድ እየሆነ ያለውን ይህንን ተግባር እየጨመርን ደጋግመን ስናደርገው ጠባያችን ወይም መገለጫ ባሕርያችን ይሆናል፡፡ ከዚያማ ውጤቱ እንዲህ ይሆናል፡- መጸለይ እንጂ አለመጸለይ አንችልም፡፡ በፊቱ መሆን እንጂ አለመሆን ያቅተናል - የሚጓጓለት ድንቅ ለውጥ!

የላይኛውን ሐሳብ የሚደግፉና የክርስትና ሕይወት እየተቀጣጠለ፣ እያደገና እየጨመረ የሚሄድ ሕይወት እንደ ሆነ የሚጠቁሙ ብዙ ክፍሎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ሦስቱን ልጥቀስ፡-እስከ እግዚአብሔር ፍጹም ሙላት ደርሳችሁ ትሞሉ ዘንድ (ኤፌሶን 3፡19)፤ በመንፈስ የምትቃጠሉ ሁኑ (ሮሜ 12፡11)መንፈስ ይሙላባችሁ እንጂ በወይን ጠጅ አትስከሩ ይህ ማባከን ነውና/ብዙ የሚያሰክሩ ነገሮች እንዳሉ ልብ ይሏል/(ኤፌሶን 5፡16-20) የእግዚአብሔር ሰው ስሚዝ ዊግልስዎርዝ እንዲህ ብሎ ነበር፡- “በዛሬው ቀን ትላንትና የነበርክበት ቦታ ላይ ከተገኘህ የኋሊት እየሄድክ ነው"
በተሰጠ ማንነት፣ ልባችን መሉ በሙሉ በጌታ ላይ ሆኖ ከላይ በተጠቀሰው ዓይነት ፍለጋ(craving) እና ትጋት ስንቀጥል፣ የጌታ አብሮሆት ከመቸው በሚበልጥ ሁኔታ በሕይወታችን ዕውን ይሆናል፡፡ ከዚህም የተነሣ የምናገኘው የመጀመሪያው በረከት በቃላት ልንገልጸው የማንችለው ሰላም፣ መረጋጋትና ደስታ ይሆናል፡፡ መንፈሳዊ መረዳታችንም እየጨመረ ስለሚሄድ፣ ጌታን በሚገባ እያወቅነው እንመጣለን፡፡ መንፈሳዊ ዓይኖቻችን በጨመረ ሁኔታ እየተከፈቱ ስለሚመጡ፣ ብዙ ረብ የሌላቸውን ነገሮች የመጣል መነሣሣትና አቅም እያገኘን እንመጣለን፡፡

እንደዚህ በጽናት ሳናሰልስ የጌታን ፊት በጨመረ ሁኔታ በፈለግን ቁጥር፣ የእግዚአብሔር ኃይል በውስጣችን እየጨመረ ስለሚሄድ፣ ብዙ ቀንበሮች ከሕይወታችን ይሰበራሉ፡፡ ስለዚህም ከበፊቱ ይልቅ በሕልውናው ውስጥ መቆየት አያስቸግረንም፡፡ ብዙ ሰዓት በፊቱ መሆንም ያለ ጥርጥር ፈቃዳችን ይሆናል፡፡

ቃሉ ተግተው የሚሹኝ ምስጉኖች/የተባረኩ ናቸው(ምሳሌ 8፡34) ይላልና፣ ለሚሹት በታማኝነት የሚገለጠው ጌታ ሕይወታችን ሲጎበኝ የሚመጣው ለውጥ ለሌሎች በረከት ያደርገናልና በጨመረ ሁኔታ ተግተን እንፈልገው!
ጌታ ሆይ እርዳን!!

“አሁን እንዳገኘሁ ወይም አሁን ፍጹም እንደ ሆንሁ አይደለም፣ ነገር ግን ስለ እርሱ በክርስቶስ ኢየሱስ የተያዝሁበትን ያን ደግሞ እይዛለሁ ብዬ እፈጥናለሁ። ወንድሞች ሆይ፣ እኔ ገና እንዳልያዝሁት እቈጥራለሁ፤ ነገር ግን አንድ ነገር አደርጋለሁ፤ በኋላዬ ያለውን እየረሳሁ በፊቴ ያለውን ለመያዝ እዘረጋለሁ” ፊልጵስዩስ 3፡7-13)

ሕብረት እና ስኬት

ዲቮሽን 282/07፥ አርብ፥ ሰኔ 12/07
(በወንድም አበባዬ )

ሕብረት እና ስኬት

" አንዱም አንዱን ቢያሸንፍ ሁለቱ በፊቱ ይቆማሉ፤ በሦስትም የተገመደ ገመድ ፈጥኖ አይበጠስም። "(መጽሐፈ መክብብ 4:12)

ከ ኢየሱስ ጋር አዲስ ግንኙነት በጀመርኩባቸው የመጀመሪያ
ዓመታት የመንፈሳዊ ዕድገት ሶስት መሰረቶች ተብየ
ከተማርኳቸው ነገሮች ውስጥ አንዱ ሕብረት ነበር። ( ሌሎች
ሁለቱ ፀሎት እና የእግዚያብሄር ቃል ናቸው) ድስት በሦስት
ጉልቻ እንደሚቆም አማኝም ያለ እነዚህ ሦስቱ አይቆምም
ሲል መንፈሳዊ አባቴ ያሰተማረኝን አልረሳውም። በቃሉ እና
በፀሎት የበረታን ብንሆንም ከ ሌሎች አማኞች ጋር ጤናማ
ሕብረት ከሌለን ዕድገታች ምልዑ አይሆንም።
ይህ ጊዜ ከመቸውም ጊዜ በላይ ግለኝነት የተንፀባረቀበት
ጊዜ ነው። ግለኝነት እራሱ አንዱ የድህረ ዘመናዊነት
አስተሳሰብ ውጤት ነው። ሰዎች ከራሳቸው እና የራሳቸው
ከሆነው በላይ ለማንም የማይጨነቁ ይመስላል።
ለስኬታቸውም ሆነ ለውድቀታቸው የሌሎች ሚና እዚህ ግባ
የማይባል እንደሆነ የሚስቡ ይመስላል። ይህ ከመፅሐፍ
ቅዱሱ የሕይወት ፍልስምና ጋር ይጋጫል።

ሕብረት የክርስትና ሕይወት አንዱ ቁልፍ ነው። ለመንፈሳዊ
ሕይወታችንም ዕድገት ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ግልፅ ነው።
ከምንም በላይ ግን ከስኬት እና ውጤታማነት ጋር ከፍተኛ
ቁርኝት አለው።

በሕይወታችን እና በአገልግሎታችን እንዲሳካልን ካስፈለገ
ጤናማ ሕብረት ሊኖረን ያስፈልጋል። እኛው በእኛው ለኛው
የሆነ ህይወት እና አግልግሎት የለም። በቤተክርስቲያንም
ሆነ በሌሎች ተቋማት በሚኖረን ተሳትፎ በሕብረት ልናምን
ይገባል። አንደኛው ዘርፍ ከሌላው ጋር በሕብረት ተቀናጅቶ
ካልሰራ ስኬት ላይ አይደረስም። በቤተክርስቲያን ውስጥ ያሉ
የተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች ተናበው እና እርስ በርስ
ተደጋግፈው በሕብረት ሲሰሩ የሚያሰማ ውጤት ይመጣል።
አሁን አንዳንድ ቦታዎች ላይ እንደሚታየው አንዱ የአንዱን ስራ
በሚያንቋሽሽበት እና በሚያፈርስበት ሁኔታ ግን ለውጥ
ሊመጣ አይችልም። "አንድ ሰው አስቦ በአንድ በሬ ስቦ"
እንደሚባለው ማለት ነው።

ወገኖቼ እየተፈታተነን ያለውን ግለኝነት ልናሸንፈው ይገባል።
ለሕይወቴ እና ለስኬቴ ሌላው ወንድሜ ያስፈልገኛል
የሚለውን የቀደመ አስተሳሰብ ልናዳብር ይገባል። በግላችን
ምንም እንኳን ጥቂት ርቀት ልንሄድ የምንችል ቢሆንም የትም
ደረጃ ልንደርስ ግን እንደማንችል ልናምን ይገባል።
አሁን ቤተክርስቲያን ልዩነታቸውን አስፈተው በመቀናናት እና በ
መገፋፋት የሚነካከሱ ሳይሆን በ ጋራና በጤናማ ሕብረት
የሚሰሩ የተናበቡ አገልጋዮችንና ኣና አማኞችን ትፈጋለች።
የራሳቸውን ምኞት አረፋ እየደፈቁ በእኔነት መንፈስ ሕዝቡን
ግራ የሚያጋቡ መንጋውን የሚበትኑ ሳይሆን ቀርበው በፍቅር
የሚያቅፉትን ሰፊ ትክሻ ያላቸው እና በሕብረት የሚያምኑ
መሪዊችን ትፈልጋለች። አሁን አገራችን በራሳቸው የብልፅግና
ምኞት ሰክረው ሁሉን እንደ ማግኔት ወደራሳቸው የሚስቡ
ስግብግቦችን ሳይሆን በጋራ የሚሰሩ እና በሕብረት የሚያስቡ
ዜጎችን ትፈልጋለች።

ጌታ በነገር ሁሉ ማስተዋል ይስጠን!

አትፍራ!

ዲቮሽን 281/07 ሓሙስ ሰኔ 11/07
( ወንድም ጌታሁን ሓለፎም )

አትፍራ!

ዘፍ 15፡1 “ከዚህ ነገር በሗላ የእግዚአብሔር ቃል በራእይ ወደ አብርሃም መጣ እንዲህ ሲል አብርሃም ሆይ አትፍራ እኔ ለአንተ ጋሻህ ነኝ ዋጋህም እጅግ ታላቅ ነው ፡፡”

አባት ለልጁ ሁል ግዜ “አይዞህ እኔ አባትህ በህይወት እስካለሁ ድረስ ምንም ነገር አይገጥምህም ፤ ሁል ጊዜ ከጎንህ ነኝ ፤ በምንም ሁኔታ ውስጥ ብትሆን አትፍራ አትታወክ አትደንግጥ ካንተ ፈጽሞ አልለይህም ” ይለው ነበር ፡፡
ልጅም ከህጻንነቱ ጀምሮ “አይዞህ” የሚለውን እና የሚያበረታውን የአባቱን ድምጽ እየሰማ ስላደገ ፤ በምንም ሁኔታ ውስጥ ቢያልፍ ሳይፈራ እና ሳይደነግጥ በነጻነት ይወጣ እና ይገባ ነበር ፡፡ አንዳንድ ጊዜም ለሚገጥመው አስቸጋሪ ሁኔታ ቃል የገባለት አባቱ አጠገቡ እየተገኘ ይረዳው እና ለችግሩ ይደርስለት ስለነበረ ይበልጥ አባቱ ላይ መደገፍ
ሆነለት ፡፡

ከእለታት ባንዱ ቀን ግን እንዲህ ሆነ ፤ ለወትሮው ከአባቱ ጋር አንድ ላይ ያቁዋርጠው በነበረ ጥቅጥቅ ባለ ጫካ በኩል ብቻውን ማለፍ ግድ ሆነበት ፡፡ ጥቂትም እንደተጓዘ ከሩቅ አንድ የአንበሳ ደጎል እያገሳ ወደ እሱ ሲገሰግስ አየ፥ ብላቴናውም አካባቢውን ሲመለከት ከእሱ በቀር ሌላ ማንም ሰው የለም ፡፡ በልቡ ውስጥ ድንጋጤ እና ፍርሃት ሲሰማው ታውቀው ፡፡

ያንበሳውም ደጎል ይበልጥ እየገሰገሰ ወደሱ መቅረብ ጀመረ ፡፡ ብላቴናውም በፍርሃት ውስጥ እንዳለ በውስጡ የአባቱ ድምጽ አቃጨለበት “አይዞህ እኔ ከአንተ አልለይም ” ብላተናው ግን በዚህች ቅስበት ብዙ ጥያቄ ይመላለስበት ነበር “

ዛሬ ግን አባቴ ለምን ተለየኝ ፤ ለምን እንዲህ ባለ አስፈሪ ወቅት ያውም በዚህ በጫካ ለምን አባቴ ከኔ ተለየ አይዞህ አልለይህም ይለኝ አልነበረም ወይ ? ” እያለ የበለጠ ፍርሃት እና ድንጋጤ ውስጥ ገብቶ ያሰላስል ነበር፡፡

በዚህ መሃል እየገሰገሰ የመጣው አንበሳ ዘሎ እላዩ ላይ ሊከመርበት ሲል ከፍተኛ የፍንዳታ ድምጽ ሲሰማ እና አንበሳው መሬት ላይ ሲደፋ አንድ ሆነ፡፡ የተከሰተው ነገር ምን እንደሆነ ለማረጋገጥ ታላቅ ፍንዳታ ወደተሰማበት ስፍራ ዘውር ብሎ ሲመለከት አባቱን ከነ ጠበንጃው በታላቅ ፈገግታ ሆኖ ቆሞ ሲመለከተው አየ ፡፡

ብላቴናውም እየሮጠ አባቱ ላይ ተጠመጠመ ፡፡ እንዲህም አለው አባቴ አመሰግንህ አለሁ ለመጀመሪያ ጊዜ ዛሬ ከፍተኛ ድንጋጤ እና ፍርሃት ተሰምቶኝ ነበር አንበሳው ይበላኛል ብየ ተስፋም ቆርጨ ነበር እውነት
ነው እንደ ቃልህ ታምነህልኛል አለው ፡፡

ይገርማል በቃሉ የምንፈተንበት ቀን ለካ ይመጣል?

ዛሬስ ስንቶቻችን ነን ከገጠምን ችግር እና መከራ የተነሳ ፤ የነገራችን ፍጻሜ የመጨረሻው መራፍ ላይ የደረስን የመሰለን ? እግዚአብሔር ላንበሳና ለተኩላ አሳልፎ እስኪሰጠን ድረስ ዝም ብሎናል ትቶናል እረስቶናል ያልን ?

ስንቶቻችን ነን ጌታ በተለያየ ወቅት እና ጊዜ በቃሉ በነበያቱና ባገልጋዮቹ ተናግሮን ፤ አልጥላችሁም አልተዋችሁም ብሎን አሁን ግን ከምናልፍበት እና ከተጋረጠብን ፤ፈቀቅ አልል ካለን መከራ የተነሳ ተስፋ የቆረጥን ? እግዚአብሔር ተናግሮን ሲያበቃ ፊቱን ከኔ መልሶአል በአጠገቤ የለም የምንል ስንቶቻችን ነን ?

ወገኖቼ እሱ እግዚአብሔር ነው እና ፤ በሰማይ እና በምድር በባህሩና በጥልቁ የወደደውን የሚያደርግ አምላክ ነው እና፤ እርሱ የትንሳኤ አምላክ እና አባት ነው እና በውነት ጊዜው ይርዘም እንጅ ነገሮች አፍጥጠው ሊወርሱን ፤ ሊያሸንፉን አጠገባችን የተጋረጡ ይምሰለን እንጅ እግዚአብሔር እንደተናገረን እንዲሁ ይሆናል ፡፡

አብርሃም ስለ ልጅ መውለድ ጉዳይ ብዙ ዘመን ጠብቆ ጠብቆ 25 አመት በዘገየበት የተስፋ ቃል ምክኒያት በእግዚአብሔር ፊት እንዲህ አለ“ የቤቴ መጋቢ ደማስቆአዊው ኤሌዘር ሊወርሰኝ ነው ” አብርሃምን ድንገት
ድንጋጤ ጋረደው ፤ ፍርሃት ወረረው ፤ ለካስ ለዚህ ነበር ገና ከጅምሩ ከጧቱ እግዚአብሔር“አይዞህ” ብሎ የተናገረው መጽሓፍ ቅዱሳችን ላይ ወደ 365 ጊዜ የሚሆን በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ አትፍራ የሚል ቃል ተጽፎ እናያለን ፡፡
እግዚአብሔር ለምንድን ነው ይህን ያህል አጠንክሮ “አትፍሩ” እያለ የሚናገረን ?“ በራሴ ጊዜ እመጣለሁ ፤ በራሴ ፈቃድ እና እቅድ እሰራለሁ ስለዚህ ነገር የዘገየ ቢመስልም ቃሌን እፈጽማለሁ እና እስከዚያው አይዟችሁ አትፍሩ ጠብቁ ” እያለን እኮ ነው ፡፡

እኔና እናንተ በተለያየ ችግር እና መከራ ውስጥ ስናልፍ ቀለል ባሉ ጉዳዮች ላይ እየታመነው ብዙ የሆነውን እርዳታ እየተቀበልን ብዙ ዘመን አልፈናል ፡፡ ነገር ግን የጠነከረ ወይም ካሰብነው በላይ ያገጠጠ ችግር ሲገጥመን ፍጹም መታመናችን ይጠፋል ፡፡ ነገር ግን ዛሬም ጌታ አትፍሩ አትደንግጡ እመጣለሁ እያለን ነው ፡፡

አሜን እግዚአብሔር ጋሻችን ነው እና አንፈራም !!!!

ይህንን መልእክት ሼር እና ላይክ በማድረግ ጌታን ያገልግሉ ፡፡ ጌታ ይባርካችሁ

'የውሸት እየኖርን' -- የእውነት እንሞታለን!

ዲቮሽን 280/07፥ ረቡዕ ሰኔ 11/07
(በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)

'የውሸት እየኖርን' -- የእውነት እንሞታለን!

ለዛሬው ዲቮሽን ርዕሴ ያደረግሁት አባባል፥ ታክሲ ውስጥ ተለጥፎ ያየሁት ነው! ይህን አባባል ማን እንደተናገረው የሚገልጽ ምንጭ ባላገኝም፥ ትልቅ አባባል መሆኑን ግን ደፍሬ እናገራለሁ፡፡

አዎ፥ የአንዳንዶቻችን ኑሮ የውሸት፥ የሽንገላ፥ የለበጣና የማስመሰል ኑሮ ነው፡፡ ነገረ ሥራችን ሲታይ፥ ከቤታችን ሌላ፥ ከቤት ውጭ ሌላ ነው፡፡ ከሰው ጋር ስንሆን ሌላ ለብቻችን ስንሆን ሌላ፡፡ የምናስበው ሌላ የምንናገረው ሌላ፡፡ የልባችን ሌላ፥ የከንፈራችን ሌላ! የሆዳችን ሌላ፥ የጥርሳችን ሌላ!

አዎይ የኛ ነገር፥ የኛ ነገርና እኛ ግራ ግብትኛ ነው! እየራበን እንግደረደራለን፥ አያማረን እንገፋለን፡፡ እየወደድን እየፈለግን የሆድ የአንጀታችንን እንሸሽጋለን፡፡ ከውስጥ እያለቀስን ከውጭ እንስቃለን፥ ከውስጥ እየሳቅን ከውጭ እናለቅሳለን፡፡ ውስጣችን ጮቤ እየረገጠ፥ በውጫችን ደረት እንደቃለን፡፡

አቤት የኛ ነገር፥ የኛ ነገርና እኛ፥ ግራ ግብትኛ! ንግግራችን ውስጠ ወይራ፥ ላይ-ላያችን ሌላ፥ ታህ-ታያችን ሌላ! አይጧ በበላች ደዋ፥ አህያ ፈርቶ ዳውላ፡፡ ፍየላችን ወዲህ፥ ቅምዝምዛችን ወዲያ፡፡

የአንዳንዶቻችን ሕይወት 'ፌክ' ይበዛበታል፡፡ ወዳጅ ከወዳጁ ጋር በሚኖረው ግንኙነት ፌክ፥ አንዱ ከሌላው ጋራ በሚኖረው ኅብረት ፌክ፥ በንግድ በገበያው ፌክ፥ በሱቅ በፋብሪካው ፌክ፥ በፖለቲካው መድረክ ፌክ፥ በየሐይማኖት ተቋሙ ፌክ፥ በየትምህርት ተቋሙ፥ በየቤተክርስቲያኑም ሆነ በየቤተክሲያኑ ፌክ፥ በየቦታው ሁሉ ፌክ ሞልቷል፡፡
ይህን ይህን ስናይ፥ "እውነትም "የውሸት እየኖርን" ያለ ይመስላል፡፡ እርግጥ ነው፥ የውሸት እየኖርን የውሸት አይሞትምና፥ የውሸት ብንኖርም የእውነት መሞታችን አይቀሬ ነው፡፡

ወገኖች ሆይ፥ የውሸት መኖር ይቅርብን! የእውነት ኑሮ መኖር ዛሬውኑ እንጀምር!

… ውሸትን አስወግዳችሁ፥ እርስ በርሳችን ብልቶች ሆነናልና እያንዳንዳችሁ ከባልንጀሮቻችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ (ኤፌ 4፡25)