Saturday, August 8, 2015

"ነበር” አያድንም!!!!!!

ዲቮሽን 333/07፥ እሁድ፥ ነሐሴ 3/07 ዓ/ም 
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)


"ነበር” አያድንም!!!!!!


በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበር። ማቴ፡ 27፡ 54


ከምሬ ነው የምላችሁ፣ አዳኙን ኢየሱስን አለመቀበል ምንኛ ከንቱነት ነው? ምንኛስ አለመታደል ነው? ከዘላለም ሕይወትስ የዘላለም ሞትን መምረጥ ምንኛ አሳዛኝ ነገር ነው? ምንስ አይነትስ ድንዛዜ ነው? ምንስ አይነትስ ፍርጃ ነው? የሐዋርያት ሥራ፡ 1፡11 “ልክ ወደ ሰማይ ሲወጣ እንዳያችሁት በዚሁ ሁኔታ ይመለሳል”፣ እንደተባሉት እንደዋዘኞቹ እንደ ገሊላ ሰዎች መሆንስ ምንኛ ዘግናኝ ነገር ነው? ኧረ ለወሬም አይመች!!!!!


በሞላ ጎደለ ስሌት ኢየሱስን አለመቀበል ምንኛ አስፈሪ ነው? ዛሬ፣ ቀኑ ዛሬ ተብሎ ሲጠራ እባካችሁ መመለስ ይሁንልን? እባካችሁ ኢየሱስ አይለመድም። እባካችሁ ሁሉም ነገር ቀሪ ነው።


ብዙ ስራዎችም ቢኖሩን፣ ወይም ደግሞ ራእዪያችንን ለማሳካት ደፋ ቀና ስንል ብንውልም፣ እባካችሁ ሞት የሚባል ጉዳይ ይጠብቀናል እኮ!!!!! የሙታን ትንሳዔም በእርግጥ አለ።


ኢየሱስም ሲመጣ ለፍርድ እንጅ ዳግመኛ ሊሰቀልልን እንዳልሆነ ለነፍሳችሁ ንገሯት። ያለመታከትም ለሰዎች ንገሩ! እኛም ቀድመን ከሰማነው ወንጌል ሌላ አዲስና ልዩ ወንጌል አንስማ፣ አንቀበል። በሲኦል ውስጥ ሆኖ፣ “በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበር”። ማቴ፡ 27፡ 54 ማለት እኮ ከሞት አያስመልጥም።


ያን ጊዜማ ወደን ሳይሆን ተገደን ማለታችን የት ይቀራል???


እኔ ግን የሚቤዠኝ ሕያው እንደሆነ፣ በመጨረሻም ዘመን በምድር ላይ እንዲቆም፣ ይህ ቁርበቴም ከጠፋ በሁዋላ በዚያን ጊዜ ከሥጋየ ተለይቼ እግዚአብሔርን እንዳይ አውቃለሁ። ኢዮብ 19:26


እነሆ የመዳን ቀን ዛሬ ነው!!!!!!!!!
---------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 33 ቀን ቀርቶታል

እውነት ራሴን እወደዋለሁ?????

ዲቮሽን 332/07፥ ቅዳሜ፥ ነሐሴ 2/07 ዓ/ም 
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)

እውነት ራሴን እወደዋለሁ?????

ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ። ዘሌ 19፡ 18

መንፈስ ቅዱስ ባልንጀራን ስለመውደድ፣ ጠላትን ስለመውደድ፣ ከራሳችን ይልቅ ለሌላው ስለማሰብ አጥብቆ ይመክረናል። እናም የይቅርታንና የፍቅርን ምሳሌ ሲያስተምረን፣ “ባልጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” ይለናል።

ዘንድሮ ግን ብዙዎቻችን፣ እንኳን ሌላውን ልንወድ ራሳችንን እንኳን ጠልተን፣ በገዛ ስጋችን እና ነፍሳችን ላይ ፈርደን፣ እንደምንኖር የታወቀ ነው።

ራሳችንን ብንወድማ ወንድሞቻችንን እየያዝን ፍርድቤት ለፍርድቤት አንጓተትም፣ ራሳችንን ብንወድማ ሰውነታችንን በመጠጥ እና በዝሙት አናቆሽሽም፣ ራሳችንን ብንወድማ የሲኦል ፍርደኞች ለመሆን አንጋፋም፣ ራሳችንን ብንወድማ ሕይወታችንን አደጋ ላይ የሚጥል እንግዳ ትምሕርት እና ሕይወት ውስጥ አንገባም።

ራሳችንን ብንወድማ መንፈሳችንን ከማይጠቅም ነገር እንከለክላለን፣ ራሳችንን ብንወድማ፣ በጸሎት እየተጋን የእግዚአብሔርን ፊት የበለጠ እንፈልጋለን፣ ራሳችንን ብንወድማ ውሸትንና ክፋትን ከጉሮሮአችን እናርቃለን፣ ራሳችንን ብንወድማ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘውን ነገር ብቻ እንፈልጋለን። ራሳችንን ብንወድማ የእግዚአብሔርን ጽድቅና መንግስት እንፈልጋለን።

ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ። መዝ 139:14

አንተ መንፈስ ቅዱስ ሆይ፣ እባክህ አሁን ራሳችንን የምንወድበትን ኃይል ላክልን? ሁሉን ታደርግ ዘንድ በእርግጥ ትችላለህና ተባረክልኝ።