Monday, July 13, 2015

ቆም ብለህ አስብ!!!!

ዲቮሽን 307/07፥ ማክሰኞ፥ ሐምሌ 7/07 ዓ/ም
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)


ቆም ብለህ አስብ!!!!


ቆም ብለህ የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራ ዐስብ። ኢዮ 37፡ 14

በሕይወታችን ላይ ማዕበል እና ወጀብ ሲበዛ፣ ከቀናነት ይልቅ ጠማማ ነገሮች በከበቡን ጊዜ፣ በድቅድቅ ጭለማና ግራ መጋባት ውስጥ ስንሆን፣ አሰልቺ የሆኑ ነገሮች ሲበዙብን፣ ከንቱ ድግግሞሽ ሕይወት ሲሆንብን፣ ወደ ማን እንሔዳለን? በማያምኑት መሀል ስንከበብ፣ የጨለማው ሥራ የእግዚአብሔርን ብርሐን የደፈነው ሲመስለን፣ በእጃችን የያዝነው ነገር ሁሉ ሲፈርስብን፣ ብቻችንን የሆንን ሲመስለን ወደማን እንሄዳለን? የማንፈልገውን እንጅ የምንፈልገውን ማድረግ ሲሳነን፣ ሥጋችን አርነት ፈልጎ ሲያምጽብን፣ ነፍሳችን የሌለች ሲመስለን ወደማን እንሄዳለን?

በዚህ ጊዜ፣ ማድረግ የሚገባን፣ እስከ ዛሬ ድረስ እግዚአብሔር በእኛም ሆነ በወገኖቻችን ላይ ያደረገውን መልካም ሥራ እያሰብን፣ መጽናናት ነው።

ለዚህም ነው፣ ኤሊሁ፣ ኢዮብን፣ ቆም ብለህ የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራ ዐስብ። ኢዮ 37፡ 14 በማለት የሚመክረው።

የእግዚአብሔር ሥራ ድንቅ ነው፤ በተጠበቀው ጊዜና ሁኔታ ሳይሆን፣ በእኔና በእናንተ እይታ እና እቅድ ሳይሆን፣ ኤልሻዳዩ፣ በራሱ ጊዜ እንደቀድመው ዘመን ሁሉ በእያንዳንዳችን ላይ በእርግጥ በድንቅ ስራው ይመጣል።

አባት ሆይ፣ ከከበበን ነገር ይልቅ፣ ከሆንነውም ነገር ይልቅ፣ ካለንበት ሁኔታም ይልቅ አንተ ድንቅ ነህና፣ ተረጋግተን  በቦታችን ሆነን እንድናስብህ፣ እንድናከብርህ እና አንተን ብቻ እንድንጨዋወትህ ዛሬ ጸጋህ ይደግፈን ሰምተህኛልና ተባረክ።

------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 59 ቀን ቀርቶታል፡፡

የአሕዛብ – አማልክት!

ዲቮሽን 305/07፥ እሁድ፥ ሐምሌ 5/07 ዓ/ም
(በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)


የአሕዛብ – አማልክት!


የአሕዛብ አማልክት ሁሉ አጋንንት ናቸውና እግዚአብሔር ግን ሰማያትን ሠራ (መዝ 95፡6፤1 ዜና 16፡26) ።
ከ20 ዓመታት በፊት ጎረቤቶቼ ጸበል ቅመስ እያሉ በሚጋብዙኝ ሐይማኖታዊ በዓላት ምንም ሳይመስለኝ እሄድ ነበር፡፡ ከአልኮሆል መጠጦች በስተቀር የሚቀርብልኝን ሁሉንም ዓይነት ምግብ ተመግቤ ተጫውቼ ወደቤቴ እመለስ ነበር፡፡ በዚም ሁኔታዬ ጎረቤቶቼ ‹‹የማያካብድ ጴንጤ›› የሚል ቅጽል ሰጥተውኝ እነደነበረ አስታውሳለሁ፡፡ በእኔ ቤት እነዚህ አጋጣሚዎች የበለጠ ከአሕዛብ ጋር ለመቀራረብና ወንጌልን ለማካፈል ዕድል ይሰጣል በሚል ነው፡፡ እስከማስታውሰው ድረስ ግን በእንዲህ መልኩ ልቡ ተለውጦ ጌታን የተቀበለ ሰው ትዝ አይለኝም፡፡


አንድ ጊዜ በሕልሜ ዝንጀሮ ጸበል ቅመስ ብላኝ ከቤቷ ሄድኩ፡፡ ቤቷ ስገባ በየቦታው በስብሰውና ለማየት እንኳ የሚቀፍፉ እጅግ አስቀያሚ የሆነ ጠረን ያላቸው እዳሪዎች እዚህና እዚያ ወዳድቀው ይታያሉ፡፡ የቤቱ ጠረን ሳንባ መተንፈሻ እስኪያቅተው ድረስ የታፈነ ነው፡፡ ይሁንና በይሉኝታ ተይዤ ወደቤቱ ዘልቄ ገባሁና በተዘጋጀልኝ መቀመጫ ላይ ተሸማቅቄ ተቀመጥሁ፡፡ ዙሪያዬ ሁሉ በእዳሪ የተከበበና የተጨማለቀ ስለሆነ እንደልቤ መንቀሳቀስ አልችልም ነበር፡፡


ዝንጀሮዋ እጇ በእዳሪ ቆሻሻ ተበክሎ ሳለ ነገር ግን ምንም ሳይመስላት ምግብ እየተመገበች ለእኔ ደግሞ ቡና ልታፈላልኝ ቡና ትወቅጥ ነበር፡፡ ከደቂቃዎች ቆይታ በኋላ በዓይኖቼ የማየውንና በአፍንጫዬ የማሸትተውን ነገር መቋቋም ስላልቻልኩ ውስጤ ይገለባበጥና ወደላይ ወደላይም ይለኝ ጀመር፡፡ በዚህ የጭንቅ ቅጽበት ከእንልቅፌ ነቃሁ፡፡ ተነስቼ እንኳ በውስጤ የነበረው መረበሽ የእውነትም ይረብሸኝ ቀጠለ፡፡ ከእንቅልፌ ነቅቼ እንኳ ወደዓእምሮዬ እስከምመለስ ድረስ ትንፋሽ አጥሮኝ በኃይል እተነፍስ ነበር፡፡ ላብ በላብም ሆኛለሁ፡፡


ታዲያ ከእንቅልፌ በደንብ ነቅቼ የሆነውን ሁሉ ሳስተውል ያቺ በእውኗ ዓለም ‹‹ጸበል ቅመስ›› የምትባለዋ ነገር፣ በሕልሜ ካየሁት የዝንጀሮ ግብዣ ጋር ተመሣሣይ እንደሆነችና አጋንንታዊ አምልኮ እንዳላት ጌታ አስተማረኝ፡፡ ተዚያች ዕለት ጀምሮ አስተዛሬ ድረስ የትም ዘመድ ቤት፥ የትም ቦታ ቢሆን ‹‹ጸበል ቅመስ›› ግብዣ ድርሽ ብዬ አላውቅም፡፡


ወገኖች ሆይ፣ በዓለማችን ውስጥ ስፍር ቁጥር የሌላቸው የአሕዛብ አማልክት አሉ፡፡ በሰማይ አካላት የተመሰሉ፣ በፀሐይ በጨረቃ የተመሰሉ፣ በቅዱሳን መላዕክትም ጭምር የተመሰሉ ብዙ የአሕዛብ አማልክት አሉ፡፡ እነዚህን አማልክት በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ የዓለማችን አሕዛብ ያመልኳቸዋል፡፡


ወገኖች ሆይ፣ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል – የአሕዛብ አማልክት ሁሉ አጋንንት ናቸው! በምድር ላይ ይሁን፣ ከምድር በታች፣ ወይም በየትኛውም ስፍራ እንዲሁም በሰማይ አካላት ዘንድ የሚገኙ ማናቸውም የአሕዛብ አማልክት ሁሉ አጋንንት ናቸው!


ወገኖች ሆይ፣ በርካታ ሰዎች የክርስትና ስም ይዘው የአምልኮ መልክ ይዘው ነገር ግን አጋንንትን ማምለክ እስካሁን ስላልተዉ፣ ጣዖታትን ማምለክ ዛሬም ሳልተዉ፣ ደግሞም መንፈሳዊ ዕውቀት ስላልበራላቸው በአጋንንት አምልኮ የተጠመዱ እጅግ ብዙ ናቸው፡፡


ወገኖች ሆይ፣ የአሕዛብ አማልክት ሁሉ አጋንንት ናቸውና እኛ አናመልካቸውም፡፡ ልናመልከው የሚገባው በሰማይና በምድር የሚኖሩትንና የሚንቀሳቀሱትን እንዲሁም የማይንቀሳቀሱትንም ሁሉ የፈጠረውን የሠራዊቱን ጌታ ሕያው እግዚአብሔርን ብቻ ነው!


-----------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6 ቀን 2007 ላይ ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 61 ቀናትብቻ ቀርተዋል፡፡

ከፊትህ – አትጣለኝ!



ዲቮሽን 306/07 ሰኞ፥ ሐምሌ 6/07 /
(
በፓ/ ተስፋሁን ሐጢያ)

ከፊትህአትጣለኝ!

ከፊትህ አትጣለኝ፥ ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ ላይ አትውሰድብኝ (መዝ 51:11)፡፡

ወገኖች ሆይ፥ ከተጠቀምናቸው በኋላ በቆሻሻ ገንዳ ውስጥ የምንጥላቸው ልዩ ልዩ ዓይነት ቆሻሻዎች፥ ከተጣሉበት ገንዳ ውስጥ ተለቅመው ወጥተው ወደ ሌላ መልክ ተቀይረው (ሪሳይክል ተደርገው) ጥቅም ላይ እንዲውሉ ይደረጋል፡፡

ታውቃላችሁ፥ ሰው የጣለው ቆሻሻ ዋጋ ያለው ሲሆን፥ ጌታ የጣለው ሰው ምንም ዋጋ የለውም! የሰው ልጅ የጣለው በሰው ልጅ ሲነሳ ጌታ የጣለው ሰው በሰው አይነሳም!

ወገኖች ሆይ፥ መዝሙረኛው፥ "ከፊትህ አትጣለኝ" እያለ የሚማጸነው - ከጌታ ፊት መጣል የሚያስከትለውን አደጋ ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ነው!

ወገኖች ሆይ፥ መዝሙረኛው ሲጸልይ (መዝ 274) "እግዚአብሔርን አንዲት ነገር ለመንሁት እርስዋንም እሻለሁ፤ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት እኖር ዘንድ…" እያለ የሚማጸነውም ከዚህ እውቀቱ ነው!

ወገኖች ሆይ፥ መዝሙረኛው ሲጸልይ፥ "ከፊትህ አትጣለኝ" ብሎ ብቻ አያቆምም - "ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ ላይ አትውሰድብኝ" ብሎም ነው እንጂ!

ታውቃላችሁ፥ ከእግዚአብሔር ፊት አለመጣላችንን የምናረጋግጠው ውስጣችን በሚኖረው በቅዱስ መንፈሱ ነው፡፡ ይኼ ቅዱስ መንፈስ በውስጣችን እንዲኖር ጌታ ያደረገው ልጆቹ "አባ አባት" ብለው መጥራት እንዲችሉ፥ እርሱም "እነሆኝ ልጄ" ብሎ ይመልስ ዘንድ ነው፡፡

ታውቃላችሁ፥ ቅዱስ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኛ ውስጥ ከሌለ፥ የአባትና የልጅ ግንኙነት ተበጠሰ ማለት ነው! ቅዱስ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኛ ውስጥ ከሌለ፥ ከእግዚአብሔር ፊት ተተፋን፥ ተጣልን ማለት ነው! ከእግዚአብሔር የተጣለ ሰው አለቀለት ማለት ነው! ያለቀለት ሰው ደግሞ፥ ወደ ሲዖል ገባ፥ ለዘላለም ጠፋ ማለትም ጭምር ነው!
------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 / ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 60 ቀን ቀርቶታል፡፡