Monday, August 10, 2015

ሙሉ በሙሉ አዲስ /Brand New/!!!!!

ዲቮሽን 335/07፥ ማክሰኞ፥ ነሐሴ 5/07 ዓ/ም 
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)


ሙሉ በሙሉ አዲስ /Brand New/!!!!!


ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል። 2ኛ ቆሮ 5፡17


በቤተክርስትያን ውስጥ እያለን፣ የእግዚአብሔርን ቃል እያወቅን፣ በዚያ በገባን እና በተረዳነው ልክ እንዳንመላለስ ብዙ እንቅፋቶች አሉብን። አንዱና ዋናው ዓእምሮአችን ነው። ይህ ዓእምሮአችን የማያስታውሰው ነገር ስለሌለ፣ በተለይ ክፉ ክፉ ገጠመኞቻችንን ከትቦ ስለሚያስቀር፣ የሕይወት እርምጃችን በመንፈስ ሳይሆን በስጋ እንዲሆን ይጫነዋል።


ለዚህም ነው፣ “እኔ እንዲህ ሆኜ የቀረሁት የሙት ልጅ ስለሆንኩ ነው፣ ቤተሰቤ በመጥፎ አስተዳደግ ስላሳደገኝ ነው፣ እናቴ ወይም አባቴ ጥቃት ስላደረሱብኝ ነው፣ በቂ የቀለም ትምህርት ስላላገኘሁ ነው፣ እልም ያለች ገጠር ውስጥ ስላደግሁ፣ ወይም በፈረንጅ አገር ስለኖርኩ ወ ዘ ተ ... እንላለን።


ተመልሰን ወደ ኃጢአት ስንገባም፣ ክርስቶስን ደስ የሚያሰኘውን ሕይወት መኖር ያቃተኝ፣ እንዲህ እና እንዲያ ስለሆንኩ ነው፣ እንዲህ ባይሆን ኖሮ እንዲህ አይሆንብኝም ነበር.... የሚሉ ልብን የሚያዝሉ ነገሮች ከአፋችን እናወጣለን። የምንናገረው ነገር እውነትነት ሊኖረውም ላይኖረውም ይችላል።


ሰይጣንም ይችን የኛን ደካማ ተፈጥሮ እንደ መልካም አጋጣሚ እየተጠቀመ፣ እስረኞች አድርጎን ሊኖር ይፈልጋል። ሞኙን ይፈልግ!!!!!


ዛሬ ሰይጣንን ከነ ሰበባ ሰበቡ ቻው ቻው እንለዋለን። አእምሮን ሁሉ ከአሁን ሰዓት ጀምሮ ለክርስቶስ እንማርካለን።
እኔ የኢየሱስን ምልክት በሥጋዬ ተሸክሜአለሁና፣ ከእንግዲህ ወዲህ ማንም አያስቸግረኝ። ገላትያ 6፡17 እናንተስ ወገኖቼ?


---------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 31 ቀን ቀርቶታል

No comments:

Post a Comment