ዲቮሽን ቁ.177/07፣ አርብ፥ የካቲት 27/07 ዓ.ም.
(በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)
ንጥቀት!
ጌታ ራሱ በትእዛዝ በመላእክትም አለቃ ድምፅ በእግዚአብሔርም
መለከት ከሰማይ ይወርዳልና፥ በክርስቶስም የሞቱ አስቀድመው ይነሣሉ፤ ከዚያም በኋላ እኛ ሕያዋን ሆነን የምንቀረው፥ ጌታን በአየር
ለመቀበል ከእነርሱ ጋር በደመና እንነጠቃለን፤ እንዲሁም ሁልጊዜ ከጌታ ጋር እንሆናለን (1 ተሰ 16-17)።
በትናንትናው ዕለት ልጆቼ ወደ ትምህርት ቤት ከመሄዳቸው በፊት፣
በሞባይሌ ላይ ‹‹ለፍት ቢሃይንድ›› ፊልም እያዩ መሆናቸውን ነግረውኝ፣ እኔም አብሬያቸው እንዳይ ጠሩኝ፡፡ ፊልሙ ስለንጥቀት እውነታ
የሚያሳይ መሳጭ ታሪክ የያዘ ክሊፕ ነው፡፡ ፊልሙ በንጥቀት ጊዜ አብረው ከነበሩ ሰዎች መካከል አንዳንዶች ሲነጠቁ ሌሎች ሲቀሩ የሚሆነውን
ክስተት ያሳያል፡፡
ለምሣሌ በአውሮፕላን እየበረሩ ካሉ ሰዎች መካከል አንዳንዶች
የለበሱን ልብስ ጥለው ሲሰወሩና ሌሎች ግን ሲቀሩ፣ ከሕጻናት ሆስፒታሎች ሕጻናት የተጠቀለሉበትን ጨርቆች ጥለው ሲሰወሩ፣ ፓይሌቱ
ሲሰወር፣ የመሳሰሉ ክስተቶችን ያሳያል፡፡ አጠገባቸው ተቀምጬ እነዚህን የመሳሰሉ ክስተቶች ለደቂቃዎች ያህል ካየሁ በኋላ ብዙም ትኩረት
አልነበረኝምና ወደዕለቱ ተግባሬ ፊቴን አዙሬ ተነሣሁ፡፡
ማታ ወደቤቴ ስመለስ፣ መብራት ጠፍቶ ስለነበር ልጆቼ ሞባይሌን
የመንጠቅ ያህል ተቀብለውኝ የጠዋቱን ‹‹ለፍት ቢሃይንድ›› ክሊፕ ማየት ጀመሩ፡፡ እኔንም ጋበዙኝ፡፡ በዚህን ጊዜ ግን ልቤ ተነካ፡፡
ስለንጥቀትም ማሰላሰል ጀመርሁ፡፡ ከዚህም የተነሣ የዛሬውን ዲቮሽን ለመጻፍ ተነሳሳሁ፡፡
ወገኖች ሆይ፣ የክርስቶስ ዳግመኛ ምጽአት የእውነተኛ አማኞች
ተስፋ ነው፡፡ ያ የምንጠብቀው፣ ያ የምንጓጓለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ
በታላቅ የእግዚአብሔር መለከት ነጎድጓድ፣ በመላእክት አለቃ ድምፅ፣ በቅዱሳን መላዕክትና ሰማዕታት ታጅቦ ከሰማይ ሲወርድ ለመመልከት
የምንጓጓለት ተስፋችን ነው!
ጌታችን ሲመጣ፣ በጌታ ሆነው የሞቱ ቅዱሳን ትንሣኤ አግኝተው
መቃብር ፈንቅለው ሲወጡ፣ የማይሞትና የማይበሰብሰውን አዲስ አካል ለብሰው ጌታን በአየር ለመገናኘት ሲነጠቁ፣ እነርሱን ተከትለን
እኛም በሕይወት ያለን የሚበሰብሰው ሰውነታችን በማይበሰብሰው አካል በቅጽበት ተለውጦ በአየር ላይ ጌታን ለመቀበል ስንነጠቅ ለመመልከት
የምንጓጓለት ተስፋችን ነው!
ጌታ የእርሱ የሆኑትን ለመቀበል በደመና ሲመጣ፣ የእርሱ ያልሆኑቱ
አይነጠቁም፡፡ በንጥቀት ጊዜ፣ ከአዳም ጀምሮ የሞቱ ቅዱሳ ትንሣኤ አግኝተው መቃብር እየፈነቀሉ ተነስተው ጌታን ለመቀበል በአየር
ሲነጠቁ፣ ቅዱሳን ያልሆኑት ከሞት አይነሡም፡፡ በሕይወት ካሉና የጌታ የሆኑቱ እውነተኛ አማኞች በቅጽበት ዓይን ተለውጠው በአየር
ሲነጠቁ፣ እውነተኛ ያልሆኑ የስም ብቻ አማኞች ሳይነጠቁ ይቀራሉ፡፡
ከአዳም ጀምሮ ያሉ ቅዱሳን ሁሉ ከጌታ ጋር በደመና ላይ ለሰባት
ዓመታት ሲነግሱ፣ በምድር የሚቀሩት ግን ለሰባት ዓመታት በታላቅ መከራ ይሰቃያሉ፡፡ ቅዱሳን ሁሉ በሰባቱ ዓመታት በደመና ላይ ቆይታ
እንደየአገልግሎታቸው አክሊል ሲቀበሉ፣ በምድር የሚቀሩት ዋይ ዋይ ይላሉ፡፡ በአውሬውና ዘንዶው በሐሰተኛው ነቢይ የተዘጋጀውን የሞት
ጽዋ ለመጠጣት ይገደዳሉ፡፡
ጌታችን ሲመጣ ሳይነጠቁ በሚቀሩ የምድር ወገኖች ላይ ሰማያት
የአሲድና የእሳት ዝናብ ያዘንባሉ፡፡ ምድር በእሳተ ገሞራ፣ በነውጥና መንቀጥቀጥ፣ በጎርፍና ውሃ መጥለቅለቅ፣ በረሃብና ጥማት፣ ይህ
ነው የማይባል መከራና ስቃይ ለመቀበል ይገደዳሉ፡፡
ወገኖች ሆይ፣ ጌታችን ሲመጣ በደመና ለመቀበልና ለመነጠቅ ተዘጋጅተናልን?
መለከት ሲነፋ፣ ድምጹን ሰምተው የሞቱ ቅዱሳን ከመቃብር ሲወጡ፣ በትንሣኤ አካል ጌታን ለመቀበል በአየር ሲነጠቁ፣ እነርሱን ተከትለን
በአየር ለመነጠቅ ራሳችንን እያዘጋጀን ነውን?
ወገኖች ሆይ፣ ጌታን ለመቀበል በቅድስናና በጽድቅ እየተመላለስን
ነውን ወይስ፣ እንደምድር ወገኖች፣ ምድራዊ ሥራ እያከናወንን? ጌታችን ሲመጣ ሳይነጠቁ የሚቀሩት የምድር ወገኖች ዋይ ዋይ ይላሉና፣
ጌታችን ሲመጣ ሳንነጠቅ እንዳንቀር በየዕለቱ ጥንቃቄ እናድርግ፡፡
ወገኖች ሆይ፣ ለምድራዊ ነገር ወዲያ ወዲህ ስንሯሯጥ ጌታችን ሲመጣ ሳንነጠቅ
ቀርተን በአውሬውና ዘንዶው በሰይጣንና በመላዕክቱን የመከራ ስቃይ የሞትንም ጽዋ እንዳንጠጣ ለባልዋ እንደታጨች ሙሽራ፣ በቅድስናና
በጽድቅ ልንመላለስ ይገባል!
--------------------------------
(ትምህርቱ ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክ ያድርጉ፣ ጌታ
ይባርክዎ!)
(1) ኤግል የሬዲዮ አገልግሎት በአማርኛ ቋንቋ
መጀመሬን በደስታ አሳውቃለሁ፡፡ በየትኛውም ዓለም የሚገኙ አማርኛ አድማጮች
http://zenoradio.com/en/listeners/ET/Eagle+Amharic+Radio/
በመጫን ሊያዳምጡ ይችላሉ፡፡ አሜሪካና ካናዳ የሚኖሩ በነጻ ስልክ (605) 562 4274 ማዳመጥ ይችላሉ፡፡
(2) ዲቮሽኖቹን በብሎግ ለመከታተል የሚከተለውን ሊንክ ይጫኑ፡፡
https://draft.blogger.com/blogger.g?blogID=7832170107481561272#allposts
(3) ዲቮሽኖቹን በፌስቡክ ለመከታተል የሚከተለውን ሊንክ ይጫኑ፡፡ https://www.facebook.com/tesfahun.hatia