Saturday, August 1, 2015

እግዚአብሔር ብቻውን!!!!!

ዲቮሽን 325/07፥ ቅዳሜ፥ ሐምሌ 25/07 ዓ/ም
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)

እግዚአብሔር ብቻውን!!!!!

እግዚአብሔር ብቻ መራው፣ ምንም ባዕድ አምላክ አብሮት አልነበረም። ዘዳግም 32፡12

ያዕቆብ በበረሐ ሲንከራተት፣ ያች የመከረችው እማዬ እንኳን አጠገቡ የለችም። የገዛ ዘመዱ ላባ፣ እንደዚያ አሥር ጊዜ ሲጫወትበት ማን አጠገቡ ነበር? ማ--ን----ም! ያዕቆብን የመራው፣ አትፍራ እያለ ያበረታው፣ የባረከው፣ ያበለጸገው እኮ አንድ እግዚአብሔር ብቻ ነው። ራሱ ያዕቆብ እኮ ይመሰክራል፣ ዮርዳኖስን ስሻገር በእጄ ከነበረው በስተቀር ምንም አልነበረኝም፣ አሁን ግን ይኸው ሰራዊት ሆኛለሁ! (ዘፍ 32፡10) እያለ ይመሰክራል።

በመንገደችን ሁሉ፣ ከስኬታችን ጀርባ፣ ከዛሬው ማንነታችን ጀርባ ያለው አንድ እግዚአብሔር ብቻ ነው።

አስተውላችሁ እንደሆነ እኮ፣ ቃል ብቻ ስላለን ነው በሕይወት ያለነው፣ የበዛነው፣ የተትረፈረፍነው። ጠላት ለእኛ ጉድጓድ ሳይቆፍር ቀርቶ መሰላችሁ? ጠላት ባሪያው ሊያደርገን፣ ሊያርደን፣ ሊሰርቀን፣ ሊያጠፋን እኮ፣ ዙሪያችንን እንደሚያጓራ አንበሳ እየጮኸ ሲያስፈራራን ነበር። ግን፣ የእኛ መሪ እግዚብሔር ከለከለው።

አንዴ በበሽታ፣ አንዴ በሟርት፣ አንዴ በድግምት፣ አንዴ በማጣት፣ አንዴ ሕብረታችንን በመበተን፣ አንዴ መላ ሕይወታችንን በማወክ፣ አንዴ ባዕድ አማልክትን እንድናመልክ በማድረግ፣ እረ ስንቱ! ሊጫወትብን እኮ አካሔዱን እየቀያየረ ፈትኖናል።

ለእኛ ግን መሪያችን፣ አንድ እግዚአብሔር ነው። አዳኛችን አንድ እግዚአብሔር ነው።

ስለዚህ፣ ቃሉ እንደሚለን፣ "አምርረህ በተነሣህ ጊዜ ግን፣ ቀንበሩን ከጫንቃህ ላይ ወዲያ ትጥላለህ" እንዳለ (ዘፍ 27፡40)፣ አምርረን ተነስተናል።

ጠላት ይህን ይወቅ!!!!! ሰይጣን ይስማ፣ ሁሉም ይስማ፣ የሚመለከተው ሁሉ ይስማ!!!! መሪያችንን እግዚአብሔርን ብቻ እናመልካለን!!! ሳይኮሎጂ አናመልክም፣ ፊሎሶፊ አናመልክም! ዓለምንና በውስጧ ያለውን አናመልክም!!!!!! 666ን አናመልክም!!!!! ይህ ግልጽ አቋማችን ነው!!!!!!!!!!!

እግዚአብሔር ብቻውን መሪ ነው!!!!!!!!!!
--------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 41 ቀን ቀርቶታል

ባያድነንስ??? እሰይ! አያድነና!!!!!

ዲቮሽን 324/07፥ አርብ፥ ሐምሌ 24/07 ዓ/ም
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)

ባያድነንስ??? እሰይ! አያድነና!!!!!

ነገር ግን ንጉሥ ሆይ፣ ባያድነንም እንኳ አማልክትህን እንደማናገለግል፣ ላቆምኸውም የወርቅ ምስል እንደማንሰግድ ዕወቅ። ዳን 3፡18

እነአናንያ፣ ሚሳኤልና አዛርያ ያ የሚንበለበለው የእቶኑ እሳት ምንም ሳይመስላቸው፣ ልክ የመዋኛ ገንዳ ውስጥ የመግባትና የመዝናናት ያህል የቀለለባቸው የዘላለም ጉዳይ ስለገባቸው ነው።

ወገኖቼ አነግራችኋለሁ፣ የዘላለም ሕይወት የሚባል ነገር አለ። አንዳንዴ የት ጋ ነው ብኩርናችንን የጣልነው ብላችሁ አስባችሁ ታውቃችሁ? ነገሩ የመጣው እኮ ቀስ በቀስ ነው። ሰዎች መጥተው፣ ጌታ ምን አደረገልሽ/ምን አደረገልህ? ሲሉን እኛም የራሱ ፋንታ ብለን፣ "ጌታን ጌታን" ማለቴ ምን ጠቀመኝ ብለን አይደል እንዴ ከዓለም የአኗኗር ዘይቤ ጋር የተመሳሰልነው? በቤተክርስትያናችን ውስጥ እንግዳ ትምሕርቶች ሲጀመሩ፣ የዘመን ፍጻሜ ደወል እየተደወለ መሆኑን መች አስተዋልን? ትምህርታቸው እንደማይሽር ቁስል ይሠራጫል፣ 2ጢሞ 2፡17 የተባሉት መምህራንን ፓ! ፓ! ፓ! እያልን እያጨበጨብን፣ እልል እያልን እኛም የነሱ ደቀመዝሙሮች መሆናችንን መች ልብ አልን?

እግዚአብሔር ባያድነንስ? ከበሽታችን ባይፈውሰንስ? ባል/ሚስት/ልጅ ባይሰጠንስ? ሥራ፣ ገንዘብ፣ መኪና፣ ቤት፣ ባይሰጠንስ? በቃ በምድር ላይ ባይሳካልንስ? በቃ!!! ከሞት የሚቀር አለ እንዴ!? ማነው በዝናው፣ በሥልጣኑ፣ በሐብቱ ልክ በምድር ላይ ጸንቶ የኖረ? ማንም የለም። በዚች ህይወት ብቻ ክርስቶስን ተስፋ ያደረግን ከሆነ ከሰው ይልቅ ምስኪኖች ነን ያለው ጳውሎስ፣ 1 ቆሮ 15፡ 19 የዘላለም ነገር ስለገባው ነው።

ወዳጄ ሆይ፣ መልሰን እኛም እንመለሳለን፤ ማረን፣ ይቅር በለን። ሰምተህኛልና ተባረክልኝ ኢየሱስ።
--------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 42 ቀን ቀርቶታል