Wednesday, August 26, 2015

ከድንቢጥ እንበልጣለን!!!!!

ዲቮሽን 351/07፥ ሐሙስ፥ ነሐሴ 21/07 ዓ/ም 
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)
ከድንቢጥ እንበልጣለን!!!!!
አትፍሩ፣ ከብዙ ድንቢጦች እናንተ ትበልጣላችሁ። ማቴ 10፡31
እግዚአብሔር ሁልጊዜ እየተጨነቅን ግራ ብናጋባው እኮ ነው፣ ቢያንስ ቢያንስ ከድንቢጥ ትበልጣላችሁ ያለን። ከአንበሳም፣ ከዝኆንም፣ ከነብርም አላወዳደረን እኮ! የምሕረቱ ልክ አልገባን ሲል፣ እንዲያው ስናሳዝነው፣ አንጀቱን ስንበላው ጊዜ፣ ቢጨንቀው እኮ ነው፣ አይ ልጆቼ፣ ቢጠፋ ቢጠፋ፣ ከድንቢጥ ትበልጣላችሁ ያለን!
እንዲያው ዋጋችሁ አታውቁትም? በደም መገዛታችሁን አታውቁትምን? በመስቀል ላይ የተሰቃየሁት ለማን ሆነና፣ መቼም ለድንቢጥ አይደለም እያለን እኮ ነው!
የሚስብ ውበት ወይም ግርማ ያልነበረኝ፣ ሰዎች እንዲወዱኝም የሚያደርግ መልክ ያልነበረኝ፣ በሰዎች የተናቅሁና የተጠላሁ፣ የሕማም ሰውና ስቃይ ያልተለየው የተባልኩ፣ ሰዎች ፊታቸውን ያዞሩብኝ፣ በእግዚእሔር እንደተመታ፣ እንደተቀሰፈ፣ እንደ ተሠቃየም የተቆጠርኩት፣ የተጨነቅሁት የተሰቃየሁት፣ እንደ ጠቦት ለዕርድ የተነዳሁት፣ አሟሟቴ ከክፉዎች ጋር የሆነ፣ ለማን ይመስላችኋል ሲለን እኮ ነው፣ አትፍሩ፣ ከብዙ ድንቢጦች እናንተ ትበልጣላችሁ፣ ብሎ እንደገና የሚያባብለን።
እኛ እምናመልከው እኮ፣ ከመቅደስ የሚበልጠውን፣ ከዮናስ የሚበልጠውን፣ ከሰሎሞንም የሚበልጠውን.... ኢየሱስን ነው!!!!
እግዚአብሔር እረኛዬ ነው፣ የሚያሳጣኝም የለም። መዝ 23:1
---------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 15 ቀን ቀርቶታል

No comments:

Post a Comment