ዲቮሽን
ቁ.29/07 ሐሙስ፣ መስከረም 29/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ
ተስፋሁን ሐጢያ)
መስቀል – ትንሳኤ !
እርሱንና የትንሣኤውን
ኃይል እንዳውቅ፥ በመከራውም እንድካፈል፥ ወደ ሙታንም ትንሣኤ ልደርስ ቢሆንልኝ፥ በሞቱ እንድመስለው እመኛለሁ (ወደ ፊልጵ
3፥10-11)
ጌታን ለመከተል መወሰን
በሕይወት ከሚወሰኑ ከባድ ውሳኔዎች ሁሉ የመጨረሻው ውሳኔ ነው! ‹‹የሰይጣንን መንገድና ስራውን፣ የዓለምን መንገድና ስራዋን
ክጃለሁ፣›› ብለን የገባነው ቃል ከቃሎች ሁሉ የመጨረሻው ቃል ነው! ‹‹የጌታን መንገድ እከተላለሁ፣ መስቀል ከፊቴ ዓለም
ከኋላ፣ ወደኋላ አልመለስም!›› እያልን የዘመርናት ዝማሬ ከዝማሬዎች ሁሉ የመጨረሻዋ ዝማሬ ናት! በውሃ ስንጠመቅ፣ ‹‹እርሱን
በሚመስል ሞት ሞቼ፣ እርሱን በሚመስል ትንሳኤ እነሳለሁ›› ብለን ያወጅነው አዋጅ ከአዋጆች ሁሉ የመጨረሻው አዋጅ ነው!
ክርስትና
የመስቀል–ትንሳኤ ሕይወት ነው! ያለ መስቀል ግን ትንሳኤ የለም! ክርስትና የpain–gain ሕይወት ነው! ክርስትና
የአርብ–እሁድ ሕይወት፣ የስቅለት– ትንሳኤ ሕይወት ነው! ክርስትና የሐዘን–ደስታ፣ የእንባ–እልልታ ነው! ክርስትና
የጉድለት–ሙላት፣ የመከራ–ባርኮት ነው! ክርስትና የረሃብ–ጥጋብ፣ የለቅሶ–ሳቅ፣ የውጊያ–ድል ነው! ክርስትና ክርስቶስን መምሰል
ነው!
በክርስቶስ ሕይወት
ከስቅለት በኋላ ትንሳኤ፣ ከውርደት በኋላ ክብር፣ ከመከራው ኋላ ድል እንደሆነ፣ በክርስቲያኖችም ሕይወት እንዲሁ ይሆናል!
ሐዘናችን በደስታ፣ ለቅሷችን በእልልታ፣ ጉድለታችን በሙላት፣ መከራችን በባርኮት፣ ረሃባችን በጥጋብ፣ ይተካል! ውርደታችን
በክብር፣ ጥላቻ በፍቅር ይተካል! በረሃችን ምንጭ፣ መራራችን ጣፋጭ ይሆናል!
ስለሆነም፣ ከመከራ
በኋላ ድል፣ ከስቅለት በኋላ ትንሣኤ እንዳለ በማወቅ መንፈሳችንን እናነቃቃ! ፈተና ሲያጋጥመን ክርስቶስን እናስብ! የትንሳኤውን
ኃይል እንድናውቅ፥ ከመከራውም እንድንካፈል፥ ቢሆንልንም በሞቱ እንድንመስለው እንጣር!