ዲቮሽን 356/07፥ ማክሰኞ፥ ነሐሴ 26/07 ዓ/ም
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)
አዎን አሸብሽቤአለሁ፣ አሁንም አሸበሽባለሁ!!!!!!!!!
እንዲያውም ከዚህ ይልቅ ራሴን በፊቱ ዝቅ አደርጋለሁ፣ ከዚህም የባሰ የተናቅሁ እሆናለሁ። 2 ሳሙ 6፡21
ዳዊት ነው ለሜልኮል እንዲህ ያላት። እኛስ ስንት ዓይነት ሜልኮሎች ዙሪያችንን ከብበውናል እኮ አላስተዋልንም እንጂ! ልብ ብንል በብዙ አእላፋት ሜልኮሎች ተከበናል።
ገንዘባችን ሜልኮል ነው፣ ፎቃችን መኪናችን ሜልኮል ነው፣ ትምህርታችን ሜልኮል ነው፣ መንግሥታዊ ኃላፊነታችን ሜልኮል ነው፣ ዘመዶቻችን፣ ቤተሰቦቻችን ሜልኮሎች ናቸው፣ ውበት ደምግባታችን ሜልኮል ነው፣ ዝና ከበሬታችን ሜልኮል ነው፣ ጓደኞቻችን ሜልኮል ናቸው፣ አልፎ ተርፎም ልብሳችንም እኮ ሜልኮል ነው፣ (አያድርስ ነው መቼም፣ ለጥቂቶቻችን ደግሞ መንፈሳዊ አገልግሎታችንም ሜልኮል ነው::)
ሰዎችም ቁሶችም አንዳቸውም እኮ ከብዙ ሞቶች አላዳኑንም። ግን እኛ እግዚአብሔርን ላመለክን እነሱ እንቅፋት ይሆኑብናል!!!!! ምቀኞች!!!!!
ስለዚህ ሜልኮሎቻችንን ዛሬ እንዲህ እንላቸዋለን፡ "እናንተ ባለ ብዙ ጫፍ ተራሮች ሆይ፣ እግዚአብሔር ሊኖርበት የመረጠውን ተራራ፣ በእርግጥ እግዚአብሔር ለዘላለም የሚኖርበትን ተራራ ለምን በምቀኝነት ዓይን ታያላችሁ?" መዝ 68:16
እግዚአብሔርን ደግሞ እንዲህ እንለዋለን::
ዋይታዬን ወደ ሽብሸባ ለወጥህልኝ። ማቄን አውልቀህ ፍስሓን አለበስኸኝ። እንግዲህ ነፍሴ ታመስግንህ፣ ዝምም አትበል፣ እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፣ ለዘላለም አመሰግንሀለሁ። መዝ 30:11
---------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 10 ቀን ቀርቶታል
No comments:
Post a Comment