Wednesday, December 10, 2014

የጴንጠቆስጤነት አቡጊዳ(#10) –የነፍሳት ምርኮ!

ዲቮሽን ቁ.90/07     ማክሰኞ፣ ሕዳር 30/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)

የጴንጠቆስጤነት አቡጊዳ(#10) –የነፍሳት ምርኮ!

እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ በሕዝብ ሁሉ ፊት ሞገስ ነበራቸው። ጌታም የሚድኑትን ዕለት ዕለት በእነርሱ ላይ ይጨምር ነበር።(የሐዋ 2፡47)።

ወገኖች ሆይ፣ መንፈስ ቅዱስ በሙላት በሚሠራበት ቦታ ሁሉ አዳዲስ ነፍሳት ይጨመራሉ፡፡ ይህ የታላቁ ተልዕኳችን ቁልፍ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱና ዋናው ነው፡፡ ሺህ ጊዜ ሺህ ሪቫይቫልና ተአምራት ቢኖር፣ እልፍ ጊዜ እልፍ ድንቅና ምልክት ቢኖር፣ ነገር ግን ሰዎች ካልዳኑ ዋጋ የለውም!

ወገኖች ሆይ፣ ጴንጠቆስጤነት ያለ ነፍሳት መዳን፣ ያለ አባላት መጨመር ሊታሰብ አይችልም፡፡ ሺህ ጊዜ ሺህ ስብከት፣ እልፍ ጊዜ እልፍ ትምህርት ቢኖር ነገር ግን ሰዎች ካልዳኑ ምንም ዋጋ የለውም! ነፍሳት የማያድን ስብከት፣ ሕይወት የማያድን ትምህርት የምግብ ፍርፋሪ፣ የእህል ገለባ ነው!

ታውቃላችሁ፣ የጴንጠቆስጤነት አንዱ መገለጫ፣ የነፍሳቶች መዳን፣ የሰዎች መትረፍ ነው! ሰዎች ካላዳንን ታላቁ ተልዕኮ፣ የስማ በለው ወሬ፣ የተረት ተረት ነው!

ታውቃላችሁ፣ ነፍሳት ካላዳንን፣ ታላቁ ተልዕኮ የወረቀት ጽሁፍ፣ ባዶ መፈክር ነው፡፡ ነፍሳት ካላዳንን የውሃ ጥምቀቱ፣ የጌታ እራቱ፣ ደቀመዝሙርነቱ፣ የሰሚ ሰሚ ነው፡፡

ታውቃላችሁ፣ ሺህ ጊዜ ሺህ ልሳን፣ እልፍ ጊዜ እልፍ ትንቢት፣ ነፍሳት ካላዳነ የከንቱ ከንቱ ነው! ሺህ ጊዜ ሺህ ጸጋ፣ እልፍ ጊዜ እልፍ ቅባት ነፍሳት ካላዳነ የከንቱ ከንቱ ነው!

ታውቃላችሁ፣ ሺህ ጊዜ ሺህ ጴንጠቆስጤነት፣ እልፍ ጊዜ እልፍ የእምነት ተከታይነት ነፍሳት ካላዳነ የከንቱ ከንቱ ነው! የኛ ፓስተርነት፣ የኛ ነቢይነት፣ የኛ ሐዋርያነት፣ የኛ ዘማሪነት፣ የኛ ወንጌላዊነት፣ ነፍሳት ካላዳነ የከንቱ ከንቱ ነው! (ተፈጸመ)

-------------------------
6 ማስታወቂያዎች፣

(1) የወንጌላዊው እጮኛ መጽሐፍ፣ እሁድ ታህሳስ 12 ቀን ከቀኑ በ10፡00 ካዛንቺስ በሚገኘው ፔንቴኮስታል ቴኦሎጂካል ኮሌጅ አዳራሽ ይመረቃል፡፡ ሁላችሁም ተጋብዛችኋል፡፡

(2) ከዚህ በፊት ለአምስት የፌስቡክ ተከታታዮቼ ስጦታ እንደምሰጥ ቃል ገብቼ ነበር፡፡ በመሆኑም፣ እነዚህ አምስቱ ከቻሉ በመጽሐፉ ምርቃ ቀን ተገኝተው የዚህን ልብ አንጠልጣይ መጽሐፍ አንዳንድ ነጻ ኮፒ በሕዝብ ፊት እነዲወስዱ እጋብዛለሁ፡፡ የማግይገኙም ቢሆን ተወካይ እንዲልኩ በአክብሮት እጠይቃለሁ፡፡

(3) ከመስከረም 1/2007 ጀምሮ እስከዛሬ ሕዳር 30/2007 ድረስ በነበሩት 90 ቀናት፣ ጌታ ረድቶኝ 90 ዕለታዊ ዲቮሽኖች በፌስቡክና በብሎግ ፖስት በማድረግ አገልግያለሁ፡፡ በቀጣየቹ ሶስት ወራት ደግሞ ከዚህ በተሻለ እንዳገለግላችሁ ምክራችሁና መልካም አስተያየታችሁ እንዳይለየኝ በጌታ ፍቅር እጠይቃለሁ፡፡

(4) ባለፉት ሶስት ወራት ውስጥ የወጡ 90 የዲቮሽን ትምህርቶች በአንድ ላይ ተሰብስበውና በመጽሐፍ ታትመው እንደጌታ ፈቃድ በቅርቡ ለአንባቢያን ይደርሳሉ፡፡ ጌታ የተመሰገነ ይሁን፡፡

(5) በቁጥር 4 በተገለጸው የዲቮሽን መጽሐፍ ላይ የ90 ቀን ዲቮሽኖቹን በየዕለቱ በመከታተልና ላይክና ሼር በማድረግ ተግቶ በማገልገል ብልጫ ላሳዩ ሶስት ሰዎች ይህ መጽሐፍ የሕይወት ዘመን ስጦታ እንዲሆንላቸውና ለስማቸውም ቋሚ መታሰቢያ ሆኖ እንዲታተም ወስኛለሁ፡፡ በመሆኑም፣ የእነዚህን ሰዎች ማንነት በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ይፋ የማደርግ መሆኑን ከወዲሁ አሳውቃለሁ፡፡

(6) ጌታ ቢፈቅድ ለሚቀጥሉትም ጊዜያት ዲቮሽኖቹን በየዕለቱ በመከታተልና ላይክና ሼር በማድረግ ተግቶ በማገልገል ብልጫ ለሚያሳዩ ሌሎች ወገኖችም እንዲሁ የሕይወት ዘመን ስጦታ እንዲሆንላቸውና መጽሐፎቹን በመታሰቢያነት አሳትማለሁ፡፡

ለበለጠ ማብራሪያ በሞባይል +251-911-678158 ይደውሉ፡፡


ጌታ ይባርካችሁ፡፡ ሁላችሁንም እወዳችኋለሁ፡፡

‹‹ስድ›› መሪዎች !

ዲቮሽን .91/07     ረቡዕ፣ ሕዳር 31/07 ..
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)


‹‹ስድ›› መሪዎች !

ሙሴም በጠላቶቻቸው ፊት እንዲነወሩ አሮን ስድ ለቅቋቸዋልና ሕዝቡ ስድ እንደ ተለቀቁ ባየ ጊዜ፥ በሰፈሩ ደጅ ቆሞ። የእግዚአብሔር ወገን የሆነ ወደ እኔ ይምጣ! አለ የሌዊም ልጆች ሁሉ ወደ እርሱ ተሰበሰቡ (ዘጸ 32፡25-26)።

መጽሐፍ ቅዱስ ታላቁ መሪ አሮንን ‹‹ስድ መሪ›› በማለት ይነቅፈዋል፡፡ አያችሁኝ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ አሮንን ‹‹ስድ መሪ›› ለማለት አላፈረም፡፡ እውነቱን ነዋ! አሮን የሠራውን ስድነት የሚገልጽ ሌላ አቻ ቃል አላገኘለትማ!

ወገኖች ሆይ፣ ምን አይነት ጥፋት ቢሆን ነው? ሙሴ ወደ እግዚአብሔር ተራራ በእግዚአብሔር ተጠርቶ ሲወጣ ሕዝቡም፣ መሪውም ያውቃሉ፡፡ ተራራው ሲናወጥ፣ የእቶን ጢስ ከሰማይ ሲወርድ፣ ነጐድጓድና መብረቅ ከባድም ደመና እጅግም የበረታ የቀንደ መለከት ድምጽ በተራራው ላይ ሲነፋ፣ እግዚአብሔር በድምፅ ሲናገር መሪውም ሕዝቡን እያየ ነው፡፡

ወገኖች ሆይ፣ መላው የእግዚአብሔር ሕዝብ እንዲህ ያለ የአማልክትን አምላክ፣ የጌቶችን ጌታ ማምለኩን አቁሞ፣ ከጆሮ ጉትቻ፣ ከእጅ ቀለበቶች ለራሱ የሚሆን ሕይወት አልባ አምላክ ሠራ፡፡ ሕይወት አልባውን አምላክ መቅረጽ ብቻም ሳይሆን ማምለክ አማረው፡፡ ሕዝቡ ተሰብስቦ ለጣኦት አምልኮ የጣዖት አጀንዳ ውይይት ጀመረ፡፡

ወገኖች ሆይ፣ በሕዝበ ውሳኔው ለጣኦት አምልኮ ውሳኔ ተሰጠ፡፡ ድምጽ ተቆጠረ፣ ሕዝቡ አሸነፈ፡፡ የሕዝቡ ጥያቄ ለመሪው ቀረበ – መሪውም ተቀበለ፡፡ ብረት ተቀጥቅጦ፣ አምላክ ተፈጠረ፡፡ ለተፈጠረው አምላክ ስግደት ተጀመረ፡፡

ታውቃላችሁ፣ መጽሐፍ ቅዱሳችን ይህንን እብደት፣ ይህንንም ውርደት ከ‹‹ስድ›› አመራር ውጭ ሌላ ቃላት አልመረጠም፡፡

ታውቃላችሁ፣ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ስድ የሚለቅቁ ስድ መሪዎች አሉ፡፡ የእግዚአብሔር ስም በአሕዛብ መካከል እንዲሰደብ በር የሚከፍቱ በርካታ ስድ መሪዎች አሉ፡፡ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ከእውነት የሚያወጡ፣ ከጽድቅ የሚያስቱ ጣዖት የሚሠሩ ብዙ መሪዎች አሉ፡፡ ጌታን የሚያስረሱ ሐውልት የሚቀርጹ፣ ቀርጸው የሚያሰግዱ ብዙ መሪዎች አሉ፡፡

ታውቃላችሁ፣ ከመስመራቸው ወጥተው፣ ድንበራቸውን ለቅቀው፣ ዓላማቸውን ረስተው፣ አቅጣጫቸውን ስተው፣ የሚመሩትን ሕዝብ አቅጣጫ የሚያስቱ፣ ስድ መሪዎች አሉ፡፡

ታውቃላችሁ፣ ጌታን አሳዝኖ ሕዝብን ለማስደሰት ጎንበስ ቀና የሚሉ ብዙ መሪዎች አሉ፡፡ በሰው ለመወደድ፣ በሕዝብ ለመመረጥ መከራ የሚያዩ ብዙ መሪዎች አሉ፡፡ ሕዝብን ለማስደሰት ከመንገድ የሚወጡ፣ በዓመጻ ገበያ ጽድቅ በኃጢአት፣ እምነትን በክህደት እውነትን በውሸት የሚለውጡ ብዙ መሪዎች አሉ፡፡

ታውቃላችሁ፣ ሕዝብን ለማስደሰት ጌታን የሚያሳዝኑ ብዙ መሪዎች አሉ! ሄሮድስን አስቡ! (የሐዋ 12)። ንጉሡ ሄሮድስ የጌታን ሐዋርያት አንዳንዶቹን አስሮ፣ ሌሎቹን ደብድቦ፣ ያዕቆብን ግን በሰይፍ ገደለ፡፡ ይህን በማድረጉ፣ አይሁድ ደስ ተሰኙ፡፡ ይህን ያየው ንጉሥ ለፋሲካው ዶሮ ጴጥሮስን አሰረው፡፡ ጌታ ግን ወኅኒ ቤቱን ከፍቶ የፋሲካውን ዶሮ ጴጥሮስን አዳነው!

ወገኖች ሆይ፣ ስድ መሪዎች ‹‹እግዚአብሔር ምን ይላል?›› ሳይሆን ‹‹ሕዝቡ ምን ይላል?›› በማለት ይጨነቃሉ፡፡ ስድ መሪዎች ‹‹እግዚአብሔር ምን ይወዳል?›› ሳይሆን ‹‹ሕዝቡ ምን ይወዳል?›› በማለት ይጨነቃሉ፡፡ ስድ መሪዎች ከእግዚአብሔር ይልቅ ሕዝቡን ያስቀድማሉ፡፡ ከእግዚአብሔር ይልቅ ሕዝቡን ይፈራሉ፡፡ ከእግዚአብሔር ይልቅ ሕዝቡን ይመርጣሉ፡፡

ወገኖች፣ ስድ መሪዎች በስድ አመራራቸው የእግዚአብሔርን ሕዝብ መረን ይለቅቃሉ፡፡ ስድ መሪዎች የእግዚአብሔርን ሕዝብ መረን በመልቀቅ ከእውነት ያስታሉ፡፡ ከእውነት አስተው የእግዚአብሔርን ቁጣ ያቀጣጥላሉ፡፡

ታውቃላችሁ፣ ጃን ሲ ማክሴል ‹‹ለማናቸውም ነገሮች ትንሳኤና ውድቀት ምክንያቱ አመራር ነው›› ይላል፡፡ እውነቱን ነው፡፡ መልካም አመራር ሲኖር መልካም ውጤት ይኖራል፣ አመራር ሲከፋ ውጤቱ ይከፋል፡፡ ስለሆነም፣ እግዚአብሔርን የሚፈሩ፣ ሕዝቡን መረን የማይለቅቁ መሪዎች እንዲነሱ ወደ ጌታ እንጩኽ!

--------------------------------

(ትምህርቱ ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክና ሼር ያድርጉ፣ ወዳጅ ጓደኞችም እንዲያገኙ ያግዙ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!)