Saturday, November 15, 2014

የድህነትን ዙፋን (#2)

ዲቮሽን ቁ.67/07     እሁድ፣ ሕዳር 7/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)


የድህነትን  ዙፋን (#2)


ወንድሞች ሆይ፥እግዚአብሔር በመቄዶንያ ላሉ አብያተ ክርስቲያናት የሰጠውን ጸጋ እንድታውቁ እንፈልጋለን፡፡ …እኛ ከጠበቅነው በላይ፣ በመጀመሪያ ራሳቸውን ለጌታ ሰጡ፤ ቀጥለውም በእግዚአብሔር ፈቃድ ራሳቸውን ለእኛ ሰጡ(2 ቆሮ 8፡1-5)

የድህነትን ዙፋን መፈንቀል ከምንችልባቸው ሁለት ሚስጥሮች የመጀመሪያው ራስን ለጌታ መስጠት ነው! ሰው ራሱን አስቀድሞ ለጌታ ከሰጠ ለራሱ የሚሰስተው ከዚህ የሚበልጥ ሌላ ነገር አይኖረውም! ሁለተኛው ሚስጥር ራስን ለሰው መስጠት ነው! ራስን ለሰው ስንሰጥ ለሌሎች አኗኗር እንቆረቆራለን!

መስጠት በውዴታ የሚደረግ መስዋዕት ነው! ጌታ ስጡኝ ሲል፣ የበለጠ በረከት ሊሰጠን ነው! አብዝተን እንድንሰጥ የሚጠይቀን አብዝቶ ሊሰጠን ፈልጎ ነው! እግዚአብሔር አብዝቶ መስጠት ብቻ ሳይሆን፣ የተሻለ ነገር ሊሰጠን ይፈልጋል! እግዚአብሔር የብዛት ብቻ ሳይሆን የጥራት አምላክ ነው! ስለሆነም፣ ያለንን ተቀብሎ የተሻለውን ሊሰጠን ይፈልጋል!

አንድ ጊዜ ስለመስጠት ያነበብሁት ምሳሌ የሚገርም ነው! አባት ለትንሽዬ ሴት ልጁ አርቴፊሻል የአንገት ጌጥ ገዝቶላት ነበር፡፡ ልጅቱም ጌጡን በጣም ትወድደው ነበር፡፡ ጌጡን ከገዛላት ከጥቂት ሳምንታት በኋላ አባት ልጁን ትወድደው እንደሆነ ጠየቃት፡፡ ልጅትም ሕጻናት እንደሚያደርጉት ሁሉ በአባቷ ጉንጮች ላይ ለደቂቃዎች ተጣብቃ እየሳመችው ፍቅሯን ገለጸችለት፡፡

አባትም ቀጠል አድርጎ በጣም ትወድደው ከሆነ ያንን በጣም የምትወድደውን ጌጥ እንድትሰጠው ልጅቱም ደንግጣ ዓይን ዓይኑን እያየች ዝም አለች፡፡ አባት አሁንም ልጁን ጌጠን እንድትሰጠው ጠየቃት፡፡ እርስዋ ግን በጣም ተጨናነቀች፡፡ ጭንቀትዋም ሲበዛ ዓይንዋ እያየ ልትሰጠው ስላልፈገች ፊቷን ዞራ በሐዘን በተሰበረ መንፈስ ጌጡን ከአንገትዋ አውልቃ ለአባትዋ ወረወረችለት፡፡

አባትዋም አርቴፊሻል ጌጡን ዓይኗ እያየ በጣጥሶ ከፊትዋ በተነላት፡፡ ይኼኔም ልጅት ለቅሶዋን አፈነዳችው፡፡ ለቅሶዋ እንዳቧራ አባት እጁን ከኪሱ ከተተና የወርቅ ሀብል አውጥቶ በአንገትዋ አጠለቀላት!

ወገኖች ሆይ፣ አንዳንዴ እኛንም የዚህ ዓይነት ችግር ይፈታተነናል! እግዚአብሔር በእጃችን ያለውን ነገር ተቀብሎ በእጁ ያለውን የከበረ ነገር ሊሰጠን ሲፈልግ ለመወሰን እንጨናነቃለን!
ወገኖች ሆይ፣ ገንዘብ ኃላፊ፣ ጠፊ ነው! ከእናታችን ማህጸን የወጣነው ራቁታችንን፣ ባዶ እጃችንን ነው–ስንሞትም የምንሄደው ሁሉን ጥለን ነው! ብልህነት ይህን ሚስጥር ማወቅ ነው! አስተዋይነት በሚያልፍና በሚጠፋ ገንዘብ የማያልፈውንና የማይጠፋውን መዝገብ በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ማኖር ነው! ብልህነት ለጌታ መስጠት ነው! ለጌታ ስንሰጥ ብልና ዝገት በማያጠፉት፣ ሌቦች ቆፍረው በማይሠርቁት በሰማይ መዝገብ ላይ ሀብትን መሰብሰብ ነው!

ወገኖች ሆይ፣ ብልጽግና ከንቱ፣ ሀብትም ጊዜያዊ ነው! ለዓመታት ደክመን ያፈራነው ጥሪት ከሞትን በኋላ በጥቂት ወራቶች የሚደመሰስ ነው! ይህን እውነት አውቀን እንድንመላለስ፣ እግዚአብሔር ይርዳን! ‹‹አንዱ ቁራሽ አጥቶ ተደፍቶ ሲያድር፣ ግማሻችን ተርፎን ስንደፋ በምድር፣ ከዚህ ጨካኝነት ጌታ ይፈውሰን፣ ሩህሩህ የሆነውን የራሱን ልብ ይስጠን!›› (ተፈጸመ)

-------------------------

(እባክዎ፣ ይህን ዕለታዊ ዲቮሽን ላይክ ያድርጉ፣ ወዳጅ ጓደኞችዎም እንዲያገኙ ያግዙ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!)

የድህነት ዙፋን (#1)

ዲቮሽን ቁ.66/07     ቅዳሜ፣ ሕዳር 6/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)


የድህነት  ዙፋን (#1)


ወንድሞች ሆይ፥እግዚአብሔር በመቄዶንያ ላሉ አብያተ ክርስቲያናት የሰጠውን ጸጋ እንድታውቁ እንፈልጋለን፡፡ …እኛ ከጠበቅነው በላይ፣ በመጀመሪያ ራሳቸውን ለጌታ ሰጡ፤ ቀጥለውም በእግዚአብሔር ፈቃድ ራሳቸውን ለእኛ ሰጡ(2 ቆሮ 8፡1-5)

በየአብያተክርስቲያኖቻችን ድህነት ዙፋኑን ዘርግቶ፣ መንግሥቱን አስፋፍቶ ይገኛል! ከዚህም የተነሳ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ምዕመናን በጨካኙ የድህነት ቅኝ ግዛት ሥር ናቸው! ከድህነት ቀንበር ክብደት የተነሳ ምግብ፣ መጠሊያና ልብስ በመሳሰሉ መሠረተ ፍላጎቶች እጦት ይሰቃያሉ!

እስኪ አጥቢያዎቻችንን እንመልከት! በድህነት ቀንበር ሥር መሆናቸው ግልጽ ነው! እስኪ አገልግሎቶቻችንን ልብ እንበል! የማህበረ ምዕመኖቻችን የመስጠት ባሕል ቁልጭ አድርገው እንደሚያሳዩ የማያከራክር ነው! ድህነታችን ከመስጠት ባህላችን ጋር የተያያዘ ነው!
የአገልጋዮቻችን ጥራትና ብዛት፣ የስብከቶቻችን ዓይነትና ጥልቀት፣ የማምለኪያ ቦታችን ቅርጽና ይዘት፣ የንብረታችን መጠንና ግዝፈት፣ የአስተዳደራችን አመራርና ስልት፣ በአጠቃላይ በአጥቢያዎቻችን ውስጥ ያሉ ነገሮች እንኳ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከመስጠት ባሕላችን ጋር የተቆራኙ ናቸው፡፡

ታውቃላችሁ፣ በአገራችን የመስጠት ወንጌል ስላልተሰበከ የድህነት መንግሥት አልተገረሰሰም! መስጠት ስላልተሰበከ የድህነት ዙፋን አልተገረሰሰም! ከድህነት ቅኝ ግዛት ነጻ አልወጣንም!
ወገኖች ሆይ፣ መስጠት የእግዚአብሔር የሚወረስ ባህል ነው! ይህ የእግዚአብሔር ባህል በአብያተክርስቲያኖቻችን ገና አልተወረሰም! እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ሁሉን ነገር ሰጠ፡፡ የሕይወትን እስትንፋስ፣ የምንተነፍሰውን አየር፣ ውሃና ዝናብን፣ ጨረቃ ጸሐይን፣ ጤናና ሰላምን…የመሳሰሉትን ያለ ዋጋ ሰጠን! አንዲያ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ለኃጢአታችን ሥርየት ሰጠን! ይህም ብቻ አይደለም፣ የጌታ ልብ ዛሬም የሚያስፈልገንን ሁሉ አብዝቶ ሊሰጠን ይፈልጋል!

ታውቃላችሁ፣ እግዚአብሔር ለስጦታው ምላሽ፣ ለፍቅሩ አስታዋሽ የሚሆን የመስጠት ጸጋችን አድጎ ማየት ይሻል! የጌታ ፍላጎት በምንሰጠውና በምንዘራው መጠን የምንቀበለውና የምናጭደው እንዲበዛ ነው!

ወገኖች ሆይ፣ ቀንደኛው የበረከታችን ጠላት የሆነው ዲያብሎስ ክርስቲያኖችን በልዩ ልዩ ሽንገላዎቹ እንዳይሰጡ በትጋት እንደሚሠራ ያውቃሉ? ወገኖች ሆይ፣ ዲያብሎስ በሽንገላው በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አማኞችን ማሳመን እንደቻለስ ያውቃሉ? መከራ–ፈተናን  የኑሮ ሁኔታን በማጋነን፣ በማካበድና አግዝፎ በማሳየትና እንዳይሰጥ በማሳመን ይሸነግላል! በሽንገላውም ብዙዎቹን ያሳምናል! በዚህም አማኞችን ከእግዚአብሔር የበረከት መስመር ውጭ ያደርጋቸዋል!

ወገኖች ሆይ፣ የመቄዶንያ አብያተ ክርስቲያናት ለዲያብሎስ ሽንገላ እጃቸውን አልሰጡም! የደረሰባቸው መከራ ጽኑ ቢሆንም፣ ደስታቸው የላቀ ነበር! ድህነታቸው ብርቱ ቢሆንም ልግስናቸው ግን የበዛ ነበር! ዐቅማቸው ትንሽ ቢሆንም ስጦታቸው ከአቅማቸው በላይ ነበር!

አንዲት ባልቴት ወገቧ ላይ ሀያ ብር ቋጥራ ወደቤተክርስቲያን ሄደች፡፡ ጌታ ከያዘችው ብር ላይ ግማሹን እንድትሰጥ ይናገራታል፡፡ ወዲያውም ዲያብሎስ ይሸነግላት ጀመር፡፡ ‹‹ያለችሽ ብር በቃ ይህቺ ናት፣ ቆጥበሽ ተጠቀሚባት እንጂ ስህተት ሰርተሽ ችግር ላይ እንዳትወድቂ›› እያለ በአእምሮ በኩል ከባድ ሙግት ገጠማት፡፡ ጌታ ረዳትና ሀያውን ብር ሰጠች፡፡

ባልቴቷ ወደቤቷ በመመለስ ላይ ሳለች፣ ዲያብሎስ አገኛትና ያሉባትን ቀዳዳዎች አጉልቶ እያሳያት ‹‹ተሳስተሻል!›› እያለ ብርቱ ሙግት ገጠማት፡፡ እርሷም ለዲያብሎስ እንዲህ ብላ መለሰችለት፣ ‹‹ተወኝ ብያለሁ፣ ቀዳዳዎቹ የራሴ፣ የሰጠሁት ለጌታዬ፣ አንተ ምን ቤት ነህ? ቅናት ይዞህ ነው እንጂ፣ አንተን የኔ ተቆርቋሪ ማን አደረገህ? እንቢ ካልክ፣ የቀረችኝን አስር ብሬን ጨርሼ እንዳልሰጥ!›› በማለት ዲያብሎስን አሳፍረውታል፡፡

ወገኖች ሆይ፣ ዲያብሎስ ከመስጠት የሚገኘውን በረከት እንዳናገኝ በብዙ መንገድ ይሸነግለናል! የድህነታችንን ጥልቀት፣ የችግራችንን ብዛት አግዝፎ እያሳየን እጃችንን ሰብስበን እንድንቀመጥ፣ ሌሎች ሲሰጡ እንድንመለከት ይሸነግለናል! የኑሮን ውድነት፣ የገቢያችንን ማነስ፣ የቤት ኪራይ፣ የልጆች ክፍያ፣ የታክሲ የወር አስቤዛ፣ የዕድር፣ የእቁብ፣ የአክሲዮን ቁጠባ እያሳየ ያስፈራራናል! በዚህም የድህነትን ዙፋን በእኛ ላይ ይጭናል!

ወገኖች ሆይ፣ የድህነትን ዙፋን መፈንቀል የምንችልባቸው ሁለት ሚስጥሮች አሉ፡፡ የመጀመሪያው ራስን ለጌታ መስጠት ነው! ሰው ራሱን አስቀድሞ ለጌታ ከሰጠ ምን ሊያስቀር ይችላል? ነፍስን ከመስጠት በላይ የሚከብድ ምን ነገር ይገኛል?

ወገኖች ሆይ፣ ከገንዘባችን በፊት፣ ከስጦታችን በፊት፣ ራሳችንን ለጌታ እንስጥ! ራሳችንን ለጌታ አስቀድመን ሰጥተን እንደሆነ መባ አስራታችንን፣ በኩራት ስጦታችንን ለጌታ ለመስጠት እጅግ ቀላል ይሆናል! መስጠት ቀላል ሲሆን የድህነት ዙፋን፣ የዙፋኑም ቀንበር፣ የቀንበሩም ክብደት በእግዚአብሔር ጉልበት ከሥር ከመሠረቱ ተነቅሎ ይጣላል!

-------------------------

(እባክዎ፣ ይህን ዕለታዊ ዲቮሽን ላይክ ያድርጉ፣ ወዳጅ ጓደኞችዎም እንዲያገኙ ያግዙ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!)