Saturday, August 22, 2015

ዘፀአት ሆነልን!!!!!

ዲቮሽን 346/07፥ አርብ፥ ነሐሴ 16/07 ዓ/ም 
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)

ዘፀአት ሆነልን!!!!!

ልክ አራት መቶ ሠላሳው ዓመት በተፈጸመ ዕለት የእግዚአብሔር ሰራዊት ሁሉ ግብፅን ለቆ ወጣ። ዘፀ 12፡41
እፎይ፣ ነፃነታችን እኮ እውነት አይመስልም አይደል? ግን ሆነ።
እስከዛሬም የቆየነው የአምላካችን ልክ፣ ማንነት፣ ወርድና ስፋት፣ ለምድር ሁሉ መታወቅ ስላለበት፣ እንዲሁም የጠላቶቻችን በኩሮች ሁሉ መቀሰፍ ስላለባቸው ነው። እንጂ ግብፅን በዝብዘን እንደምንወጣማ የታወቀ ጉዳይ እኮ ነው!!! (ዘፀ 3፡22)።
ታዲያ፣ ዛሬ ዘፀአት ሆነልን!!
ያ፣ እግዚአብሔርን አላውቅም፣ እስራኤልንም አለቅም እያለ ሲፎክር የነበረው፣ ፈርዖናችን (እያንዳንችን እኮ ስንት ዓይነት ፈርዖንና ሠራዊቱ ሲገዛን ኖሯል! ዝርዝሩን እናንተ ሙሉበት) የኤልሻዳዩ ሰዓት ሲደርስ፣ እናንተ እስራኤላውያን ከሕዝቤ መካከል ውጡ! በጠየቃችሁት መሠረት እግዚአብሔርን አምልኩ ብሎ ጭራሽ ሸኘን እኮ!
ድሮስ፣ የእኛ ጌታ በኩር በኩሩን እያነቀ ቋ፣ ቋ፣ ቋ፣ ሲጥ ሲያደርግበት ወዶ ነው የሚለቀን! እኛም ዘመናችንን ሁሉ እግዚአብሔርን እናመልካለን። ልጆቻችን፣ የልጅ ልጆቻችንም ሁሉ ሲጠይቁን፣ “ከባርነት ምድር ከግብፅ እግዚአብሔር በሐያል ክንዱ አወጣን። ፈርዖን እኛን አለቅም ብሎ ልቡን ባደነደነ ጊዜ፣ ከሰው ጀምሮ እስከ እንስሳ ድረስ በኩር ሆኖ በግብፅ የተወለደውን ሁሉ እግዚአብሔር ገደለው።” እያልን እንመሰክራለን!!!
ዐይኖቼ የባልንጦቼን ውድቀት አዩ፣ ጆሮዎቼም የክፉ ጠላቶቼን ድቀት ሰሙ። መዝ 92:11
---------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 20 ቀን ቀርቶታል

በማትረፍረፍ የታወቀ!!!!

ዲቮሽን 345/07፥ አርብ፥ ነሐሴ 15/07 ዓ/ም 
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)

በማትረፍረፍ የታወቀ!!!!

ፊትህን አያለሁ ብዬ አላሰብሁም ነበር። እነሆም እግዚአብሔር ዘርህን ደግሞ አሳየኝ። ዘፍጥ 48፡ 11
የእኛ እግዚአብሔር በማትረፍረፍ የታወቀ ነው። የተትረፈረፈ ሰላም፣ የተትረፈረፈ ይቅርታና ምህረት፣ የተትረፈረፈ ባለጸግነት እና ሕይወት የሚገኘው በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ብቻ ነው።
ያዕቆብ፣ ስለ ሞተ ልጁ ሲያለቅስ ዓመታት ተቆጠሩ። ያ ብላቴናው ዮሴፍ ባይን ባይኑ እየሄደበት ብዙ ተክዟል። እንዲያው በቀበርኩት፣ ሬሳውን እንኩዋን ባየሁት እያለ! እንዲያው የልጄን ቀን በሰጠኝ እያለ ያዕቆብ ሲያለቅስ፣ ማስደነቅ የሚያውቀው የእኛ እግዚአብሔር ግን፣ በራሱ ሰዓት እና ጊዜ ከች አለ።
ያውም ዮሴፍ ሲመጣ መለመላውን ሆኖ አይደለም። ለተራበች ምድር ብቸኛ ተስፋ ሆኖ!!!! የልጁን ዓይን ብቻ ለማየት ምንም የተስፋ ጭላንጭል ያልነበረው ያዕቆብ፣ ዕልፍ ብሎ፣ የዮሴፍንም ልጆች አየ: ኤፍሬምና ምናሴን!!!!!!! እሥራኤል አያት ሆነ እኮ ነው እያልኩዋችሁ ያለሁት!!!!! እረ አለ ገና!!!!
ያዕቆብ የልጁን ሬሳ እንኩዋን ቢያገኝ ደስታው ወደር አልነበረውም። ደመ-ከልብ ሆኖ የቀረ መስሎት እኮ ነው በሀዘን ሲብሰለሰል የኖረው!!!! ወይም ደግሞ አካሉ ጎድሎ፣ ወይ ጎስቁሎ ቢመጣለት፣ እጅግ ይደሰት ነበር።
ሆኖም ግን.....
ዮሴፍ ባለፀጋ፣ ሀገረ ገዥ ሆኖ፣ አግብቶ ወልዶ፣ ተትረፍርፎ መጣ።
እግዚአብሔር ነዋ!!!!!!!
አንድ ሲጠየቅ አሥር እጥፍ አድርጎ በመስጠት የታወቀ የእኛ እግዚአብሔር ብቻ ነው። ኦ መንፈስ ቅዱስ ሆይ፣ እንዴት ግሩም ነህ!!!!!
እንግዲህ በእኛ እንደሚሠራው ኃይል መጠን ከምንለምነው ወይም ከምናስበው ሁሉ ይልቅ እጅግ አብልጦ ሊያደርግ ለሚቻለው (ኤፌ 3: 20) ለእግዚአብሔር አምልኮ እና ስግደት፣ ክብር ይገባዋል።
---------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 21 ቀን ቀርቶታል

ዮሴፍ በሕይወት አለ!!!!!!!

ዲቮሽን 344/07፥ ሐሙስ፥ ነሐሴ 14/07 ዓ/ም
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)

ዮሴፍ በሕይወት አለ!!!!!!!

ዮሴፍ የላከለትን ሠረገላዎች ሲያይ የአባታቸው የያዕቆብ መንፈስ ታደሰ። ከዚያም እስራኤል፣ “ልጄ ዮሴፍ በሕይወት አለ፣ ከመሞቴ በፊት ሂጄ ልየው”አለ። ዘፍ 45፡28

በጣም የምትፈልጉት ነገር ሞቷል ብሎ ጠላት መርዶ የነገራችሁ ምንድን ነው? ለመሞቱም ጠላት ምልክት በደም ነክሮ ያረጋገጠላችሁ ነገር ምንድነው? እናንተም ጌታ የተናገረኝ ነገር እንዴት ሳይሆን ቀረ እያላችሁ በስብራት ትኖራላችሁ አይደል? ነገሩ ትዝ ሲላችሁ ስታለቅሱ ስንት ዓመት ሆናችሁ ይሆን?

የሰማነው መርዶ ባለማረጋገጫ ስለሆነ፣ ይህማ የልጄ እጀ ጠባብ ነው፤ ክፉ አውሬ በልቶታል በእርግጥም ዮሴፍ ተበጫጭቆአል፣ እያልን ስንት ዓመታት አለፉ! ጠላትም ስብራታችንን እያየ ሲዘባነንብን፣ ብዙ ዓመታት ተቆጠሩ አይደል? በመጨረሻም፣ በሐዘን እንደተኮራመትን ወደ መቃብር እንወርዳለን ብለን ደመደምን አይደል! ስንት ውሸትን በማስረጃ እያስደገፈ ሲያስደንግጣችሁ እና ሲያባንናችሁ ኖረ አይደል!

አሁን አንገት የመድፊያው ጊዜ የጠላት እንጅ የእኛማ አይደለም! አሁን ጠላት ከነዘርማንዝሩ ለቅሶ ይቀመጥ፣ ምክንያቱም የተቀበረው የጠላት ልጅ እንጅ የእኛ ዮሴፍማ በሕይወት አለ። ዮሴፋችን በሕይወት አለ።

ዛሬ እግዚአብሔርን እንዲህ እንለዋለን፣
---------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 22 ቀን ቀርቶታል

ሮኆቦት ሆነልን!!!!!

ዲቮሽን 343/07፥ ረቡዕ፥ ነሐሴ 13/07 ዓ/ም 
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)

ሮኆቦት ሆነልን!!!!!

አሁን እግዚአብሔር ሰፊ ቦታ ሰጥቶናል፤ እኛም በምድር ላይ እንበዛለን። ዘፍጥረት 26፡22
ካንድ ቦታ ወደሌላው ስትፈናቀሉ፣ ካንድ ሥፍራ ወደ ሌላው ስትሔዱ፣ የያዛችሁት ሁሉ ብትን ብሎ ሲጠፋ ታለቅሳላቸሁ አይደል? የጀመራችሁት ነገር ዳር ሊደርስ ሲል ሲጨናገፍ፣ እናንተም ስታለቅሱ፣ ጠላትም ስታለቅሱለት፣ ዳዊት ጋ እንደፎከረው፣ “በእግዚአብሔር ተማምኖአል፣ እንግዲህ እርሱ ያድነው፣ ደስ የተሰኘበትን እስኪ ይታደገው” መዝ 22፡8 እያለ ይፎክርባችኋል አይደል? አይ ጠላት ሞኙ! ትንቢት እያወጣብን መሆኑን መች አወቀ! አላወቀም እንጅ እያንዳንዷ የእንባ ዘለላችን የጸሎት መስዋዕት ናት!
ብናለቅስስ? እናልቅሳ? ያለቀስነው እኮ ወደ አባታችን ነው። የተከራከርነው እኮ ከአባታችን ጋር ነው። ከንፈር መጦ ዝም ወደማይለው አባታችን እሪ ኡኡኡ ድረስልን ብለን ብናለቅስስ? እናለቅሳለን! ጠላት ምናገባው? እኛ ያለቀስነው፣ ባሕሩን ከፍሎ ወደሚያሻግረን አምላካችን! እኛ ያለቀስነው በምድረበዳ እንደ መንጋ ወደሚመራን አምላካችን! እኛ የምናለቅሰው ዐለቱን በምድረበዳ ሰንጥቆ እንደ ባሕር የበዛ ውሃ ወደሚያጠጣን አምላካችን፣ ምንጭ ከቋጥኝ አፍልቆ ውሃን እንደ ወንዝ ወደሚያወርደው አባታችን!
አሃ! አይ ጠላት! አልቃሻ እያለ ዝም ሊያሰኘን እኮ ነው! ነጭናጫ እያለ ሊወርሰን እኮ ነው! ሞኝ! እኛስ አንገኝም። ኤሴቅንም ጠላት ይውሰድ፣ ስጥናንም ለራሱ ያድርገው! እኛን የሚመጥነን ሮኆቦት ብቻ ነው። ምክንያቱም ብዙ ስለሆንን፣ ትንንሽ ነገር አ-ይ-መ-ጥ-ነ-ን-ም።
ወደ ሰፊ ስፍራም አወጣኝ፣ ደስ ተሰኝቶብኛልና አዳነኝ። መዝ 18፡19
-----
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 23 ቀን ቀርቶታል

ጌታ ነዋ!!!!!!

ዲቮሽን 342/07፥ ማክሰኞ፥ ነሐሴ 12/07 ዓ/ም 
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)

ጌታ ነዋ!!!!!!

ስለዚህ እንደሞተ ሰው ከሚቆጠር ከዚህ ከአንድ ሰው፣ እንደ ሰማይ ከዋክብት የበዛና እንደ ባህር ዳር አሸዋ ተቆጥሮ የማያልቅ ዘር ተገኘ። ዕብ 11፡12

የአብርሐም የአንድ ልጅ ጥያቄ ለዘመናት ከእግዚአብሔር ጋር ሲያጨቃጭቀው ቆይቷል። አይ እግዚአብሔር! እንዴት ድንቅ ነው! ዔሊኤዘር ይወርሰኛል እያለ ሲፈራ የነበረው አብርሐም፣ የትውልድ ሁሉ አባት ለመሆን በቃ። ተረት አይመስልም? ግን እውነት ነው!

እግዚአብሔር እንዲህ ነዋ! እግዚአብሔርን ምንም ነገር አያስፈራውም። ሳይንስ አያስፈራውም፣ እድሜ አያስፈራውም፣ መልክዓምድራዊ አቀማመጥ አያስፈራውም፣ ሞት አያስፈራውም፣ መንግስታት አያስፈሩትም፣ ..እሱ ግን ሥራውን በራሱ ጊዜ ይሠራል! ከለመንነውም ከጠየቅነውም በላይ ማድረግ ይችላል።

ታዲያ ዛሬ በሰውም በእናንተም ዓይን የሞተው ነገር ምንድን ነው? የተቀበረውስ አልአዛር የትኛው ነው? እግዚአብሔር እልፍ ያለ ነገር በእያንዳንዳችን ሕይወት ላይ አይቷል። መንፈስቅዱስን ዝም ብላችሁ አመስግኑት። እወድሐለሁ በሉት።

አምላክ ሆይ፣ ለእኔ ያለህ ሐሳብ እንዴት ክቡር ነው። ቁጥራቸውስ እንደምን በዛ! ብቆጥራቸው ከአሸዋ ይልቅ ይበዛሉ። መዝ 139፡17
---------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 24 ቀን ቀርቶታል