Monday, February 2, 2015

ለአካላዊና – መንፈሳዊ ፈውስ!

ዲቮሽን .145/07     ሰኞጥር 25/07 ..
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)


ለአካላዊና – መንፈሳዊ ፈውስ!

እርስ በርሳችሁ በኃጢአታችሁ ተናዘዙ። ትፈወሱም ዘንድ እያንዳንዱ ስለ ሌላው ይጸልይ፤ የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች (ያዕ 5፡16)።

በኃጢአትና በሕመም መካከል ከፍተኛ ዝምድና አለ፡፡ አንዳንድ ሕመሞች የእግዚአብሔር ሥራ በእነርሱ እንዲገለጥባቸው ካልሆኑ በስተቀር(ዮሐ 9፡1-3)፣ ሕመም ሁሉ የኃጢአት ውጤት ነው፡፡ ከኃጢአት የተነሳ ለሚመጣ ማንኛውም ሕመም ፈውስ ለመቀበል ቅድመ ሁኔታው ንስሐ  መግባት ነው(ያዕ 5፡16)። በሕክምና ተቋምም ሆነ በጸሎት ፈውስ የሚመጣው ከላይ ከእግዚአብሔር  ነው፡፡

ታውቃላችሁ፣ ጌታችን ኢየሱስ በአልጋ የተኛ ሽባ ወደ እርሱ ሲያመጡ፣ እምነታቸውን አይቶ ሽባውን ‹‹አንተ ልጅ፥ አይዞህ፥ ኃጢአትህ ተሰረየችልህ›› ነው ያለው (ማቴ 9፡2)።

ታውቃላችሁ፣ አካላዊ ፈውስ ከመንፈሳዊ ተሐድሶ ጋር የተገናኘ ነው! ሰው ሥጋ፣ ነፍስና መንፈስ አለውና፣ አካላዊ ፈውስ ከመንፈሳዊ ተሐድሶ ጋር የተቆራኘ ነው! አንዱን ስብዕናችንን ተከትሎ የሚመጣ ነገር በሌላኛው ስብዕናችን ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል! በመንፈሳችን ላይ መንፈሳዊ ተሐድሶ ሲኖር በአካላችን ላይ ፈውስን አስከትሎ ይመጣል!  በአንዱ ስብዕናችን ኃጢአት ስንሠራ፣ ሌላው ማንነታችን በኃጢአት ይበከላል!

ታውቃላችሁ፣ በብሉይ ኪዳን እንደ ፈሳሽ ያሉ፣ በአካልና የቆዳ ላይ የሚወጡ በሽታዎች ሰውን እርኩስ ሆኖ እንዲቆጠር ያደርጉ ነበር፡፡ እነዚህ ችግሮች ያሉበት ሰው ከመንፈሳዊ አገልግሎቶችና ከማህበረሰቡ ጋር የሚኖረው ሕብረት ይቋረጥም ነበር!

ወገኖች ሆይ፣ ኃጢአት ሰውን በቀላሉ የሚያሳስት ኃይል ነው! በእግዚብሔርም ላይ ይሁን በሰው ላይ ኃጢአት ስንሠራ ልናውቅም ላናውቅም እንችላለን፡፡ የድፍረት ኃጢአት እንደምንሠራው ሁሉ ሳናውቀው በስህተት የምንሠራው ኃጢአት አለ፡፡ ስለሆነም፣ ኃጢአት እንደ ሠራን እንኳ ላናስተውል እንችላለን!

ወገኖች ሆይ፣ በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያችን ጌታን እናሳዝናለን፣ የሰው ልጆችንም እናስቀይማለን! በጌታ ላይ ኃጢአት ስንሠራ ለጌታ ተናዝዘን መንፈሳዊ ተሐድሶ መቀበል እንደሚገባ፣ በሰው ላይ ስለሠራነው ኃጢአት በእነርሱ ፊት ተናዝዘን ልንፈወስ ይገባል፡፡

ታውቃላችሁ፣ ዝሙት፥ ርኵሰት፥ መዳራት፥ ጣዖትን ማምለክ፥ ምዋርት፥ ጥል፥ ክርክር፥ ቅንዓት፥ ቁጣ፥ አድመኛነት፥ መለያየት፥ መናፍቅነት፥ ምቀኝነት፥ መግደል፥ ስካር፥ ዘፋኝነት፥ የመሳሰሉት የሥጋ ሥራዎች የሰይጣን 'ሜኑዎች' ናቸው፡፡ እነዚህን ተከትሎ ሕመም ወደ ሰው ሊመጣ ይችላል፡፡ ስለሆነም እርስ በርሳችን እየተናዘዝንና እየተጸላለይን ፈውሳችንን ልንቀበል ይገባል!

ወገኖች ሆይ፣ ኃጢአቱን የሚሰውር አይለማምና፣ ኃጢአታችንን ብንሰውር ምሕረትና ፈውሳችንን መቀበል አንችልም፡፡ በሽታን ደብቆ መድኃኒት የለምና፣ ኃጢአታችንን ደብቀን ምሕረት ፈውሳችንን መቀበል አንችልም!

ወገኖች ሆይ፣ በእግዚአብሔር ላይ የሠራነውን ኃጢአት ለእግዚአብሔር እንናዘዝ! በሰው ላይ የሠራነውን ኃጢአት ለሰዎች እንናዘዝ! እንፈወስም ዘንድ ሳናቋርጥ እርስ በርሳችን እንጸላለይ፡፡ ይህን ስናደርግ መንፈሳዊ ተሐድሷችንና አካላዊ ፈውሳችንን የተረጋገጠ ይሆናል!
-----
ትምህርቱ ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክ ያድርጉ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!

--------------------------------

‹‹የወንጌላዊው እጮኛ›› አዲስ መጽሐፍ፣ በገበያ ላይ ውሏል፡፡ ለተጨማሪ መረጃ በ0911 678158 ወይም 0911 813092 ይደውሉ፡፡