Monday, October 6, 2014

ሞገስ እንዲኖርህ …!


ዲቮሽን ቁ.26/07     ሰኞ፣ መስከረም 26/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)

ሞገስ እንዲኖርህ …!



እግዚአብሔርም የሰው ክፉት በምድር ላይ እንደ በዛየልቡ አሳብ ምኞትም ሁልጊዜ ፈጽሞ ክፉ እንደ ሆነ አየ። እግዚአብሔርም ሰውን በምድር ላይ በመፍጠሩ ተጸጸተ፥ በልቡም አዘነ። እግዚአብሔርም፦ የፈጠርሁትን ሰው ከምድር ላይ አጠፋለሁ፥ ከሰው እስከ እንስሳ እስከ ተንቀሳቃሽም እስከ ሰማይ ወፍም ድረስ ስለ ፈጠርኋቸው ተጸጽቼአለሁና አለ። ኖኅ ግን በእግዚአብሔር ፊት ሞገስን አገኘ። የኖኅ ትውልድ እንዲህ ነው። ኖኅም በትውልዱ ጻድቅ ፍጹምም ሰው ነበረ ኖኅ አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ (ዘፍ 6፡5-9)


እንደ ኖህ ዘመን ሁሉ፣ የትውልዳችን ክፋት በዝቷል! ጠፍቷል! በትውልዱ አናት ላይ ሰይጣን ዙፋን ተክሏል! በቤተክርስቲያን ውስጥም ኃጢአት ምሽግ ሰርቷል! ማግባትና መፍታት፣ የተፋታን ማግባት ተራ ነገር ሆኗል፡፡ ምንዝርነት፣ እርኩሰት፣ ዓለማዊ ምኞት ሲበዛ ተለምዷል፡፡ የአማኝ አላማኝ ልዩነቱ ቀርቷል! ቅድስና ጽድቁ መላ ቅጡ ጠፍቷል! ነገረ ስራችን ውጥንቅጡ ወጥቷል!


የዘመናችን ቤተክርስቲያን ግብረሰዶማዊያንን በተክሊል እያጋባች ነው፡፡ በበርካታ አገልጋዮችና መሪዎች ዘንድ ሳይቀር እግዚአብሔርን መፍራት እንደ ኋላቀርነት እየተቆጠረ ነው፡፡ ሳይጋቡ መዘሞት እየቀለለ ነው፡፡ ስርቆቱ፣ ሙስናው፣ ዝርፊያውና ንጥቂያው እየጨመረ ነው፡፡


እንደ እኛ ዘመን ሁሉ፣ የኖህ ዘመን ትውልድ በኃጢአት የተበከለ ነበር፡፡ የልባቸው ክፋትና የኃጢአታቸው ክርፋት ምድርን አበላሸ፡፡ በዘመኑ ሰዎች ኃጢአት ምክንያት በተፈጥሮ ላይ ሳይቀር ቀውስ ደረሰ፡፡ 


እግዚአብሔር በዘመኑ ከሚኖሩ ሰዎች መካከል ፈልጎ ያገኘው ኖኅን ብቻ ነበር፡፡ ኖህ በትውልዱ መካከል በልዩነት ይመላለስ ነበር፡፡ ከትውልዱ አካሄድ እራሱን ለይቶ፣ ከዘመኑ ሩጫ መንፈሱን ገትቶ ነበር፡፡ ትውልዱ ሲፋንን እርሱ ለጽድቅ ተገዝቶ ነበር፡፡ ሕዝቡ ሲበላ ሲጠጣ፣ ሊዘፍን ሲነሳ፣ ሲያገባ ሲፈታ፣ ኖህ ግን ልዩነት ነበረው፡፡ 


የኖህ ዘመን ትውልድ ጸበሉ ጸዲቁ፣ ፌሽታና ድግሱ፣ ዳንስና ዘፈኑ በምድሩ ላይ ሲበዛ ሰዎች አላወቁም፡፡ ሲበሉ ሲጠጡ፣ ሲያገቡ ሲፈቱ በጊዜ አልነቁም፡፡ የኃጢአት ዳንኪራ፣ የጭፈራና እልልታ ጩኸት በምድሪቱ ሲበዛ ሁሉ ሰላም መስሎ ነበር፡፡ እግዚአብሔር በእነዚህ ሁኔታዎች የማያገባው፣ ቸል ያለ፣ ዝም ያለ፣ መሰላቸው፡፡ ነገር ግን በድንገት የጥፋት ውኃ መጥቶ ሁሉንም ወሰዳቸው! ከኃጢአት ክርፋታቸው ጋር ከምድር ገጽ ላይ ጠርጎ አጠፋቸው! 


ዛሬም የኛ ትውልድ ይኼው መጥቶበታል! በኃጢአታችን ምክንያት ምድር ተበላሽታለች፡፡ ሽብርተኝነቱ፣ የእርስ በርስ ጦርነቱ፣ የደም መፋሰሱ… በየቦታው በዝቷል፡፡ በኃጢአታችን ምክንያት ተፈጥሮ ተቃውሷል፡፡ የአየር ብክለት፣ የእሳተ ገሞራዎች ፍንዳታ፣ የጎርፍ መጥለቅለቅ፣ የአውሮፕላኖች መከስከስ፣ የመርከቦች መስጠም … ይጠቀሳል፡፡ ድርቅና ረሃብ፣ ቀሳፊ ደዌዎችም እየበረከቱ ነው፡፡ 


ይህ ብቻም አያበቃም! አንድ ቀን በድንገት ጌታችን ኢየሱስ በሕያንና በሙታን ሊፈርድ በመላዕክት ታጅቦ በደመና ይመጣል፡፡ የተዉት፣ የካዱት፣ የናቁት ያዩታል! በኖኅ ዘመን እንደሆነው፣ ሰዎች ሲበሉ ሲጠጡ፣ ሲያገቡ ሲጋቡ ሳለ የጥፋት ውኃ ድንገት እንደመጣ፣ ጌታችን በድንገት ይመጣል፡፡ ለያንዳንዱም እንደ ስራው ዋጋውን ይሰጣል! 


የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፣ ምድር እንዳትጠፋ እግዚአብሔርን ፍራ! በትውልድህ መካከል በጽድቅ ተመላለስ! ከትውልድህ መካከል ፈልጎ እንዲያገኝህ፣ በፊቱም ሞገስ እንዲኖርህ፣ አካሄድህን ከእግዚአብሔር ጋር አድርግ!


------------------------
(
ይህን ዕለታዊ ዲቮሽን ላይክ እና ሼር ያድርጉ፣ ወዳጅ ጓደኞችዎም እንዲያገኙ ያግዙ፡፡ ዲቮሽኑ ሳይቋረጥ ዓመቱን ሙሉ እንዲቀጥል በጸሎትዎና ጌታ በልብዎ በሚያስቀምጥ ማናቸውም ነገር ሁሉ ይደግፉ፡፡ ጌታ ይባርክዎ፡፡)

ባይወለዱ ኖሮስ ?

ዲቮሽን ቁ.25/07     እሁድ፣ መስከረም 25/2007 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)

ባይወለዱ ኖሮስ ?

… መጽሐፍ እንደሚል ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሞተ፥ ተቀበረም፥ መጽሐፍም እንደሚል በሦስተኛው ቀን ተነሣ፥ ለኬፋም ታየ በኋላም ለአሥራ ሁለቱ፤ ከዚያም በኋላ ከአምስት መቶ ለሚበዙ ወንድሞች በአንድ ጊዜ ታየ፤ ከእነርሱም የሚበዙቱ እስከ አሁን አሉ አንዳንዶች ግን አንቀላፍተዋል፤ ከዚያም በኋላ ለያዕቆብ ኋላም ለሐዋርያት ሁሉ ታየ፤  ከሁሉም በኋላ እንደ ጭንጋፍ ለምሆን ለእኔ ደግሞ ታየኝ።  እኔ ከሐዋርያት ሁሉ የማንስ ነኝና፥ … ከሁላቸው ይልቅ ግን ደከምሁ፥ ዳሩ ግን ከእኔ ጋር ያለው የእግዚአብሔር ጸጋ ነው እንጂ እኔ አይደለሁም።(1 ቆሮ 15፡3-10)

በሕይወታችን ቆም ብለን ስለራሳችን ራሳችንን ጠይቀን እናውቅ ይሆን? ለምሳሌ እናቴ ባረገዘችን ወቅት በማናቸውም ምክንያት ውርጃ ፈጽማ ቢሆን ኖሮስ፣ ብለው  ወይንም እርስዎ ስለተረገዙ አባትዎ እናትዎን፣ ‹‹እኔ ልጅ አልፈልግም፣ በቃ አውጥተሽ ካልጣልሽ›› ብሎ እናትዎትን አስገድዶ፣ እናትዎትም አማራጭ ስላጡ፣ ሽሉን አውጥታ ጥላው ቢሆን ኖሮስ ብለው አስበው ያውቃሉ? በድህነት፣ ራስን ባመለቻል፣ ወይንም በማናቸውም ምክንያቶች እርስዎ እንዳይወለዱ ተደርጎ ቢሆን ኖሮስ? እስኪ ያስቡት? ከእናትዎት ሆድ በሽልዎ ወጥተው ከቆሻሻ ገንዳ ውስጥ ሲጣሉ፣ ምን ሊያጋጥምዎት እንደሚችል በዓይነ ሕሊናዎ ይሳሉት፡፡ ምን ሊያጋጥምዎት እንደሚችል እስኪ ላፍታ ያስቡት??

ውድ አንባቢዬ፣ ለጽንስ ማቋረጥ አስፈላጊ የሚመስሉ ሌሎች አራት ምክንያቶችንም ላቅርብልዎት፡፡

ምክንያት (1)፣ አንድ ወንጌላዊና ሚስቱ እጅግ በጣም ድሃ የሆነ ኑሮ ይመራሉ፡፡ ሁለቱም 14 ልጆች ወልደዋል፡፡ በዚህ ላይ ሳይዘጋጁበት ሚስትዬው 15ኛ ልጃቸውን ማርገዟን አረጋገጡ፡፡ ባልና ሚስቱ በድህነት እየማቀቁ ናቸው፡፡ ስለሆነም፣ የእነዚህን ባልና ሚስት ድህነት ከግንዛቤ በማስገባትና የዓለም ሕዝብ ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን በማየት ሴትየዋ የተረገዘውን ልጅ በውርጃ ብታስወጣው እንደሚሻል ይመክሩ ይሆናል፡፡

ምክንያት (2)  አባትየው የመተንፈስ ችግር አለበት፡፡ እናት ደግሞ የሳንባ በሽታ አለባት፡፡ ሁለቱም አራት ልጆች ወልደዋል፡፡ የመጀመሪያ ልጃቸው ዓይነስውር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ሞቶባቸዋል፡፡ ሶስተኛው ልጃቸው መስማት የተሳነው ሲሆን አራተኛው የሳንባ በሽተኛ ነው፡፡ እናት በድንገት አምስተኛ ልጃቸውን አረገዘች፡፡ በእነዚህ ከአቅም በላይ በሆኑ ምክንያቶች የተነሳ ውርጃ መፈጸም የተሻለ አማራጭ መሆኑን ይደግፉ ይሆናል፡፡

ምክንያት (3)፣ አንድ ነጭ፣ የአስራ ሶስት ዓመቷን ጥቁር ልጅ አስገድዶ በመድፈሩ ምክንያት አረገዘች፡፡ እርስዎ የዚህች ልጅ ወላጅ ቢሆኑ ውርጃ እንደሚሻል ያስቡ ይሆናል፡፡

ምክንያት (4)፣ አንዲት ወጣት ልጅ ከጋብቻ በፊት አረገዘች፡፡ እጮኛ ነበራት፡፡ ነገር ግን እጮኛዋ የልጁ አባት አይደለም፡፡ ከዚህም የተነሳ እርስዎ ልጅቱ እንድታስወርድ ይመክሩ ይሆናል፡

በ1ኛው ምክንያት ጽንስ ተቋርጦ ቢሆን ኖሮ፣ ታላቁ የ19ኛው ምዕተ ዓመት ወንጌላዊ ጆን ዊስሊ ተገድሎ ነበር ማለት ነው፡፡ በ2ኛው ምክንያት ውርጃ ተፈጽሞ ቢሆን ኖሮ፣ ታላቁ የሙዚቃ ቀማሪው ቤትሆቨን ተገድሎ ነበር ማለት ነው፡፡ በ3ኛው ምክንያት ጽንስ ተቋርጦ ቢሆን ኖሮ፣ ታላቋን ጥቁር ዘማሪ ኤትል ዋተርስን ተገድላ ነበር፡ በ4ኛው ምክንያት ጽንስ ተቋርጦ ቢሆን ኖሮ፣ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገድሎ ነበር ማለት ነው፡፡

ውድ አንባቢ ሆይ፣ ስለሐዋርያ ጳውሎስ ያስቡ፣ ባይወለድ ኖሮ? ጨንግፎ ቢቀር ኖሮ? የጌታ ኢየሱስን ደቀመዛሙርትም ያስቡ፡፡ ባይወለዱ ወይም ጨንግፈው ቢሆን ኖሮ?

ነገስታቶቻችንን እነአጼ ላሊበላን፣ አጼ ቴዎድሮስን፣ አጼ ዮሐንስን፣ አጼ ሚኒሊክን፣ አጼ ኃይለስላሴን ያስቡ፡፡ የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትራችንን መለስ ዜናዊን እንዲሁም ያሁኑን አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን ያስቡ፡፡ እነዚህ ሰዎች እንዳይወለዱ ተፈርዶባቸው ቢሆን ኖሮስ?
እነሼክ አላሙዲንን፣ እነሜትር አስቲስት አፈወርቅ ተክሌን፣ እነአበበ ቢቂላን፣ እነኃይሌ ገብረስላሴን፡ እነደራርቱ ቱሉን ያስቡ፡፡ እነዚህ ሰዎች እንዳይወለዱ ተፈርዶባቸው ቢሆን ኖሮስ? 

ከአገር ወጣ ብለው ባራክ እነ ኦባማን፣ ዴቪድ ካሜሮንን፣ እነ ኔልሰን ማንዴላን፣ እነ ማዘር ቴሬዛን፣ እነ አንድራ ጋንዲን ያስቡ፡፡ እነዚህ ሰዎች እንዳይወለዱ ተፈርዶባቸው ቢሆን ኖሮስ? ከዘማሪዎችም እነዶን ሞይንን፣ እንዳርሊን ዘችን፣ እነተስፋዬ ጋቢሶን፣ እነሊሊን ያስቡ፡፡ እነዚህ ሰዎች እንዳይወለዱ ተፈርዶባቸው ቢሆን ኖሮስ?  

ከእግር ኳሱም ዓለም እነሮናልዶን፣ እነሜሲን አስቡ፣ እነዚህ ሰዎች እንዳይወለዱ ተፈርዶባቸው ቢሆን ኖሮስ? ከሳይንቲስቶች እነቶማስ ኤዲሰን እነኒውተንን አስቡ፣ ከሐኪሞችም፣ ከፋርማሲስቶችም፣ ከአንትሮፖሎጂስቶችም፣ ከአርኪዎሊጂስቶችም …አስቡ፡፡ እነዚህ ሰዎች እንዳይወለዱ ተፈርዶባቸው ቢሆን ኖሮስ?  

ውድ ወዳጄ፣ ጽንስ ማቋረጥ ይቅር! የተጸነሰው ልጅ ምን ሊሆን እንደሚችል አይታወቅም፡፡ ለሰውነቷ ማሞቂያ ጨርቅ ካጠራት ድሃ ሴት ቢሊየነር ሊወለድ ይችላል፡፡ ከዓይነስውሯ ሆድ ዓይናማ፣ ከፈሪዋ ጀግና፣ ከማይሟ ሳይንቲስት …ሊወለድ ይችላል፡፡ ነገ የሚሆነው አይታወቅምና፣ ሰው አፍረን፣ ይሉኝታ ፈርተን፣ በማናቸውም ሁኔታ የተረገዘን ጽንስ አንግደለው! በዚህ ጽንስ ነገ ስማችንን በዓለም የሚያስጠራ፣ ሀገርን የሚያኮራ …ሊሆን ይችላል! ጽንስ ማቋረጥ ይቅር! ነገ የሚሆነው አይታወቅምና ነፍስ ማጨንገፍ ይቅር!

------------------------
(
ይህን ዕለታዊ ዲቮሽን ላይክ እና ሼር ያድርጉ፣ ወዳጅ ጓደኞችዎም እንዲያገኙ ያግዙ፡፡ ዲቮሽኑ ሳይቋረጥ ዓመቱን ሙሉ እንዲቀጥል በጸሎትዎና ጌታ በልብዎ በሚያስቀምጥ ማናቸውም ነገር ሁሉ ይደግፉ፡፡ ጌታ ይባርክዎ፡፡)