ዲቮሽን ቁ.41/07 ማክሰኞ፣ ጥቅምት
11/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)
እየተሠራን
ነው!
የእግዚአብሔር እርሻ ናችሁ፤ የእግዚአብሔር ሕንፃ ናችሁ…. (1ቆሮ 3፡9)።
ስለ እርሻ አስበው ያውቃሉ? ስለ ሕንጻስ ልብ ብለው ያውቃሉ? ከእህል
በረንዳ ገብተው ጤፉን፣ ስንዴውን ሩዙን፣ አተር ባቄላውን …ሲመለከቱ ምን ይታሰብዎት ይሆን! ከአትክልትና ፍሬፍሬ ሱቆች ውስጥ
ሙዙን ብርቱካኑን፣ ወይንና ሎሚውን… ቆስጣና ጎመኑን፣ ካሮትና ሽንኩርቱን … ሲመለከቱ ምን ያስቡ ይሆን?
ስለሕንጻ አስበው ያውቃሉ? ከቀላል እስከ ባለኮከብ ሕንጻዎች ሲመለከቱ ምን
ይታሰብዎ ይሆን! ዲዛይናቸውን፣ ውበታቸውን፣ ቀለማቸውንና ምስህባቸውን ሲመለከቱ ምን ያስባሉ?
ታውቃላችሁ፣ እነዚያ ለዓይን የሚያምሩና ለመብልም የሚጣፍጡ አትክልቶችና
ፍሬፍሬዎች ከእርሻ የተገኙ ውጤቶች ናቸው፡፡ አትክልቶችና ፍሬፍሬዎች እንደዚህ ለዓይን የሚያምሩት፣ ለመብልም የሚጣፍጡት ብዙ ስለተደከመባቸው
ነው!
ታውቃላችሁ፣ እርሻው ለሥራ ሲዘጋጅ፣ እላዩ ላይ ያሉ ቆሻሻ ነገሮች፣
በቅለው የነበሩ አረሞች፣ የወዳደቁ ገለባዎች… ተሰብስበው ይቃጠላሉ!
ታውቃላችሁ፣ እርሻው ለሥራ ሲዘጋጅ፣ አላስፈላጊ ሐረጎች ይመነጠራሉ!
አላስፈላጊ ዛፎች ይቆረጣሉ! አላስፈላጊ ቅርንጫፎች ይገረዛሉ! አላስፈላጊ ቡቃያዎች ይወገዳሉ!
ወገኖች ሆይ፣ እርሻው ለአዝመራ ሲዘጋጅ ደግሞ መሬቱ ይሰነጠቃል፣ የተሰነጠቀው ይገለበጣል፣ የተገለበጠው ይከሰከሳል፣ የተከሰከሰው ደግሞ ይጎለጎላል! ከዚያ በኋላ ምርጥ ዘር ይዘራበታል! የበቀለው ይታረማል፣ ሲደርስም
ይቆረጣል! እህሉ ሲደርስ ይታጨዳል፣ የታጨደው ይወቃል፣ የተወቃው ይበጠራል፣ የተበጠረው ለገበያ ይቀርባል!
ወገኖች ሆይ፣ በኪነሕንጻ ጥበባቸውና በውበታቸው የምናደንቃቸው ሕንጻዎች
ሲሰሩ አካባቢው በጣም ያስጠላል! የተቆለለው አፈር፣ የተከመረው ድንጋይ፣ እዚህና እዚያ ተጥሎ የሚታየው ብረት፣ ሚስማር፣ ሽቦ…
ሲታይ ለዓይን ያስጠላል! ሕንጻዎች ሲሰሩ ብዙ ጊዜ ከሰው እይታ በሸራ እንዲከለሉ የሚደረጉት ለዚህ ነው! ሕንጻ ሲሰራ ለእይታ
አስቀያሚ ነው! ጭቃው፣ አቧራው፣ ኳኳታው …አይመችም! ተሠርቶ ሲያልቅ ግን ሰዎች ቆመው በአድናቆት ይመለከቱታል፣ ያወሩለታል፣
ከአጠገቡ ቆመው ፎቶ ይነሡበታል፣ ፖስትካርድ ይለዋወጡበታል !
ወዳጄ ሆይ፣ እግዚአብሔር እየሠራን ነው! የእርሱ እርሻና ሕንፃ ነንና እየሠራን
ነው! እንደ መልካም እርሻ ፍሬያማ እንድንሆን እየሠራን ነው! እንደተዋበ ሕንጻ ለብዙዎች ማረፊያ እንድሆን እየተሠራን ነው! እንደ
መልካም እርሻ እየኮተኮተን፣ እየጎለጎለን፣ እየገረዘንና እያረመን ለፍሬ እያዘጋጀን ነው! ስለሆነም እግዚአብሔር ሲሠራን እርሱ
በሚፈልገው መልኩ ተሠርተን እንድወጣ እንድታዘዝ ጌታ ይርዳን!
-------------------------
(ይህን
ዕለታዊ
ዲቮሽን
ላይክና ሼር ያድርጉ፣ ወዳጅ ጓደኞችዎም
እንዲያገኙ
ያግዙ፡፡
ይህን አገልግሎት ለመደገፍና የእምነት ዘራችሁን ለመዝራት (Tesfahun Hatia
Daka, Commercial Bank of Ethiopia, Andinet Branch; A/C 1000036318949; Swift Code: CBETETAA) መላክ ትችላላችሁ፡፡ ለዘሪ ዘርን የሚሰጥ ጌታ ዘራችሁን ይባርክልኝ!)