Thursday, July 30, 2015

ይጨምርልን !

ዲቮሽን 323/07 ፤ ሓሙስ ሓምሌ 23 /07
( ወንድም ጌታሁን ሓለፎም )


ይጨምርልን !


“ ምህረት እና ሰላም ፍቅርም ይብዛላችሁ ” ይሁዳ 1፡- 2


አሜን ይብዛልን !


መቼስ ሁላችንም እንደምንመሰክረው እና እንደምንረዳው ፡- ወደ ጌታ ዘውር ካልንበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ ከእግዚአብሔር ከሆነልን አስደናቂ በረከቶች ውስጥ አንዳንዶቹን እንቁጠር ብለን ብንል ፤ የተትረፈረፉልን ሰላም ምህረትና ፍቅር ከብዙዎቹ ጥቂቶቹ ሆነው እናገኛቸዋለን ፡፡



እንደበግ የምንቅበዘበዝ ፤እረፍት አጥተን የምንባዝን ነበርን ፤ ነገር ግን ጌታ ወደ ሂወታችን ሲገባ ታላቅ ሰላም እና ምረጋጋትን ተቀበልን ፤ በነጻነት መግባት መውጣት ሆነልን ፤ መሲሁ ወደ ልባችን እልፍኝ ሰላምን ይዞ መጣ !



በመስቀል ላይ ስለ ሰው ልጆች ኃጢያት እራሱን አሳልፎ በሰጠው በክርስቶስ ኢየሱስ በኩል ታላቅ የሆነውን የእግዚአብሔርን ፍቅር አየን !



ታዲያ ሓዋርያው ያቆብ እንደሚለን እነኝህ ከግዚአብሔር የተሰጡን ስጦታዎች ዋጋቸው ታላቅ ነው እና ፤ በየእለቱ የሚበዙ የሚያድጉ የሚጨምሩ ይሁኑ እንጅ በነገሮች እና በሁኔታዎች የተነሳ የሚከስሙና የሚጫጩ መሆን የለባቸውም ፤ ተመልሰን ወደ ፍርሃት ፤ ተመልሰን ወደድንጋጤ ተመልሰን ወደ ኃጢያት እስራት ፤ ተመልሰን ወደብዝበዛ እና ሽንፈት መግባት አይገባንም ፤ይልቁንም የሚበዙ የሚጨምሩ እና የሚያድጉ ይሁኑ !




እውነት ነው ይህ ከጌታ የተሰጠን በረከት በየእለቱ የሚበዛ እና የሚጨምር መሆን ይገባዋል ፤ በነጻ ከእግዚአብሔር የተቀበልነው ነገር ግን እጅግ ውድ ስጦታ ! የማይከፈልበት ያልተለፋበት ነጻ በረከት! አዎ ብር ወርቅ የማይገዛው ውድ ስጦታ !



ስለዚህም ፡- በወንድሞች መካከል ሰላም ይሁን !

ለቤተክርስቲያን ፤ ለምድራችን ፤ ለአለም ሰላም ይሁን ! 



ለሰው ልጆች በሙሉ ከእግዚአብሔር ምህረት እና ሰላም ፍቅር ይሁን ! መጭው ዘመናችን “ ምህረት፤ሰላም እና ፍቅር ” የሚበዛበት ወደ ጌታ ነፍሳት የሚጨመርበት በነገር ሁሉ የምናድግበት ዘመን ይሁን !


------------
እለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ሊጠናቀቅ 43 ቀናቶች ቀርተውታል !

ማነው የሚለየን?????????????

ዲቮሽን 322/07፥ ረቡዕ፥ ሐምሌ 22/07 ዓ/ም
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)

ማነው የሚለየን?????????????

ከክርስቶስ ፍቅር የሚለየን ማነው? ሮሜ 8፡35

በዚህ ምርጫ እና እድል በበዛበት ዓለም፣ መጀመሪያ የያዝነውን የክርስቶስን ፍቅር ይዞ መቆየት ትግል ሆኖብናል። ያንን፣ በእንባና በልቅሶ የምንወደውን ኢየሱስን፣ አሁን በበርካታ ነገሮች ለውጠነዋል።

በድፍረት እናገራለሁ፡ ኢየሱስን በዓለምና በውስጧ ባሉት ነገሮች ተክተነዋል። በፋሽን ተክተነዋል፣ በምቾት ተክተነዋል፣ በድሎት ተክተነዋል። በዝና፣ በእኔ አውቃለሁ ባይነት ተክተነዋል፣ በእውቀታችንም ተክተነዋል፣ በመኪናችን፣ በቤታችን፣ በትዳራችን፣ በቆንጆ ባሎቻችንና ሚስቶቻችን፣ በዘናጭ ልጆቻችን ተክተነዋል፣ በውጭ ሐገር ጉዞዎቻችን ተክተነዋል፣ በዲግሪና በማስተርሳችን፣ በፒኤችዲያችንንና በፕሮፌሰርነታችን ተክተነዋል።

ደግሜ እላለሁ፡ ያንን የሚወደንን፣ ያንን ምስጢረኛችንን ኢየሱስ፣ ያንን የምድረበዳችን ኢየሱስን፣ ያ በተዘጋው ቤታችን የመጣውን ኢየሱሰን፣ ያ የዘላለም ወዳጃችንን ኢየሱስን፣ በሞራል ትምህርት ለውጠነዋል፣ በሳይኮሎጂ ነክ ትምህርት ለውጠነዋል።

ወገኖቼ፣ እኛ እኮ ከኢየሱስ ጋር ብዙ ምስጢር ያለን ሰዎች ነን። ያልተቻለውን ችሎልን፣ ያ የሚከረፋውን እና የሚሸተውን ቁስላችንን ያጠበልንን ኢየሱስን፣ ያ ክፋታችንን እና ሞታችንን ሁሉ ወደ ህይወት የቀየረልንን ኢየሱስን፣ ያ ማንም ወዳጅ እና ሰው ሲጠላን ያልጠላንን ኢየሱስን ለምን ዛሬ ቸለል ቸለል አልነው?

ጳውሎስ፡ ከክርስቶስ ፍቅር የሚለየን ማነው? ችግር ነው ወይስ ስቃይ፣ ወይስ ስደት፣ ወይስ ረሀብ፣ ወይስ ዕራቁትነት፣ ወይስ አደጋ ወይስ ሰይፍ? ሮሜ 8፡35 እንደሚላቸው ሳይሆን፣ ዛሬ እኔ እንዲህ እላችኋለሁ፡ ከክርስቶስ ፍቅር የሚለየን ማነው? ጥጋብ ወይስ ምቾት፣ ወይስ የተንጣለለ ማረፊያ ቤት፣ ወይስ የሚቀያየሩ ልብሶች፣ ወይስ መንግሥታት ያስጠበቁልን ደህንነታችን?
እላችኋለሁ፤ ማንም አይለየን!!!! ማ----ን-----ም!!!!!!

አባት እግዚአብሔር ሆይ፣ ላንተ የሚሳንህ ነገር የለምና፣ እለምንሃለሁ ወደ ቀደመው ፍቅራችን እና የዋህነታችን መልሰን። በእርግጥ ታደርገዋለህና ተባረክልኝ።
--------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 44 ቀን ቀርቶታል