Saturday, August 15, 2015

ጨዋታችን ተቀየረ!!!!!

ዲቮሽን 339/07፥ ቅዳሜ፥ ነሐሴ 9/07 ዓ/ም
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)
ጨዋታችን ተቀየረ!!!!!
ያዕቆብም ደግሞ ጉዞውን ቀጠለ፣ የእግዚአብሔርም መላእክት ተገናኙት። ዘፍ 32፡1
መቼም ሰውና ሰው ሲገናኝ እና ሰውና መልአክ ሲገናኝ ጨዋታው አንድ አይነት አይሆንም። ከአጎቴ ላባ ቤት እኮ ባዶ እጃችንን አልወጣንም፤ መሰለን እንጂ።
ብዙ ነገር በዝብዘን፣ ማርከን፣ ተትረፍርፈን ወጣን። አሁን ጠረናችን መላእክትን መሳብ ጀመረ። አሁን እንቅፋት የሚሆኑ ሰዎች ሳይሆኑ፣ አሁን መላእክትን በአካል ማየት ጀመርን። መዓዛችን ተቀየራ!!!!
አጎቴ ላባ ከመሔዱ አፍታም ሳይቆዩ የመላእክት መምጣት አይገርማችሁም!! በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ሁሉ ስላንተ ያዛቸዋልና። መዝ 91:11 This is entirely a divine design.
በመንገድ ስንሔድ አሳዳጅ አይደለም ያኘነው-መላእክትን ነው። ምን ምን አሏችሁ? ምን ምን አጫወቷችሁ? ምን ምስጢር ነገሯችሁ? ምን መልእክት አመጡላችሁ? ጉድ ነው መቼም! እንዴት ታድለናል! መላእክቱን ስለእኛ የሚያዝ እግዚአብሔር ይባረክ!!!!! አሜን!!!!!
አሁን እናት አይመክረን አባት፣ እህት አይመክረን ወንድም፣ አጎታችን ላባ አያስፈራራን፣ ያ ሊገድለን ቀን ቀጠሮ ይዞ የነበረው ወንድማችን ዔሳው ጦር አይሰብቅብን። መላእክትን አግኝተናላ!!!!
እራሳቸው መላእክት ተልከው መጡልን---- በአካል አየናቸው!!!! ታድለን!!!! እፎይ!!!!!!!
በቃ ተለወጥን! እንዴት ግሩም ነገር ነው! ገና ከእናታችን ማህፀን ሳንወጣ እኮ ነው ትንቢት የተጀመረው። ጉዞ ወደ ቃልኪዳናችን........... ደስ ሲል!
ታዲያ እንዳትዘናጉ፣ ከአጎቴ ላባ ጋር ተሳስመን እንደተለያየነው ሁሉ ከወንድሜ ዔሳው ጋርም እንዲሁ አድርጉ። እሽ??? አደራችሁን፣ ምንም መዳበል የሚባል ኑሮ የለም!!!!!!
እዛው በሩቁ፣ እሽ??? አደራ!!! አጎቴ ላባ ወደ አገሩ እንደተመለሰው ሁሉ፣ ወንድሜ ዔሳውም ወደ አገሩ በሰላም ይመለስ። ደባል አንፈልግም!!!! እንደገና ጭቅጭቅ ውስጥማ አንገባም!!!! ስንት ስራ የሚጠብቀን ሰዎች እኮ ነን!
ከዚያም ዲያብሎስ ትቶት ሄደ፣ መላእክትም አገለገሉት። ማቴ 3:11
---------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 27 ቀን ቀርቶታል

አጎቴ ላባ ስሞኝ ተመለሰ!!!

ዲቮሽን 338/07፥ አርብ፥ ነሐሴ 8/07 ዓ/ም
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)
አጎቴ ላባ ስሞኝ ተመለሰ!!!
በማግስቱም ላባ የልጅ ልጆቹን እንዲሁም ሴቶች ልጆቹን ስሞ መረቃቸው፤ ከዚያም ወደ አገሩ ተመለሰ። ዘፍ 31፡55
ያዕቆብ ለአጎቱ ለላባ በታማኝነት ሲገዛለት ኖረ። ላባም ሳያስበው አሪፍ ባሪያ አገኘ። “አንተማ የዐጥንቴ ፍላጭ የሥጋዬ ቁራጭ ነህ” እያለ፣ እያሞካሸው ለዓመታት ገዛው። ዘፍጥረት 13፡14
በኋላ በስተመጨረሻ ግን እግዚአብሔር በቃ ሲል፣ ያዕቆብ ኮበለለ። ለካስ ለገዥዎችም ገዥ አለ!!!!
ላባስ ከእንግዲህ ምን ስልጣን አለው!? ትንሽ ማንኮሻኮሽ መፍጠሩ ግን አልቀረም። አንዴ ሳትሰናበቱኝ ምነው? እያለ (አዛኝ ቅቤ አንጓች!!!!)፣ አንዴ አምላኮቼን ሰርቃችኋል እያለ (ጉድ ነው መቼም የሚሰረቅ አምላክ!!!!)፣ አንዴ ከፈለኩኝ ልጎዳህ እችላለሁ እያለ (አይሞክረውም ነበር፣ ድሮስ አዝኖለት ነው!!!!!) እንደ እብድ አስር ነገር ሲለፈልፍ ቆየና፣ ሀቁን አፈረጠው። "አምላካችሁ ያዕቆብን ደግም ክፉም እንዳትናገረው ብሎ አስጠነቀቀኝ" ብሎ እውነቱን ተናገረ!!!!! እሰይ የእኛ እግዚአብሄር!!!!
ከዚያም የልጅ ልጆቹን እንዲሁም ሴቶች ልጆቹን ስሞ መረቃቸው፤ ከዚያም ወደ አገሩ ተመለሰ። ዘፍ 31፡55።
ሲችል እያስፈራራ እያንገራገረ፣ ሳይችል እያባበለ፣ ሲገዛው የኖረውን ላባ፣ ያዕቆብ ለዘላለም ተገላገለው!!!!!!
ከዚያስ? ከዚያማ፣ ያዕቆብ ጉዞውን ቀጠለ። (32:1) እሰይ!!!!!!!!
ቁርስና ምሳ እየሰጡ ዘላለም ሊገዙን የወደዱ አጎቶቻችን ላባዎች ምንም ምርጫ ስለሌላቸው፣ ትእዛዝ ከሰማይ ስለወጣባቸው፣ ሲፈልጉ መርቀውን ሲፈልጉ ረግመውን ዛሬ ሔዱ። መሸሸጊያ ይሆኑናል፣ ያልናቸው አጎቶቻችን ላባዎች፣ መማጸኛ ይሆኑናል ብለን ሲገዙን የኖሩት ሁሉ፣ ዛሬ እየሳሙን ወደ አገራቸው ተመለሱ።
ዛሬ፣ ለዘመናት እንደ ላባ አጎት የሆኑባችሁ ሁሉ፣ ለዘላለም ሔደዋል።
አጎቴ ላባ ስሞኝ ተመለሰ!!! (Uncle Laba kissed me & departed from me FOREVER & returned to his place)
ያልኩት ገብቷችኋል? ከዚያስ?፣ ከዚያማ እንደ ያዕቆብ ጉዞአችንን ቀጠልና!!! ጉዞ እግዚአብሔር ወደ አየልን……..
ነገርን ሁሉ በጊዜው ውብ አድርጎ ሰራው። መክ 3:11
ማን?
ኢ-----የ-----ሱ-----ስ።
---------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 28 ቀን ቀርቶታል

ኃያላን ወደቁ!!!!

ዲቮሽን 337/07፥ ሐሙስ፥ ነሐሴ 7/07 ዓ/ም
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)
ኃያላን ወደቁ!!!!
ኃያላን እንዴት ወደቁ!? 2ኛ ሳሙ 1፤19
ስለጀግንነታቸው ምናልባት ሌሎች ሰዎች ከሚያውቋቸው በበለጠ፣ ሌሎች ወታደሮችና አብረዋቸው የሚኖሩ ሠራዊቶቻቸው ከሚያውቋቸው በላይ፣ ዳዊት ሳኦልንና ዮናታንን ይበልጥ ያውቃቸዋል። ሐያልነታቸው እስከምን እንደሆነ ከሌሎች እስራኤላውያን በተሻለ ዳዊት ልቅም እድርጎ ይገባዋል። እንዲያ ሲያርበደብዱት፣ በረሐ ለበረሐ ሲያስለቅሱት፣ ሲያስርቡት እና ሲያስጠሙት፣ ሲያንከራትቱት የነበሩትን እነዚህን ሁለት ሰዎች ዳዊት በደንብ አድርጎ የጀግነታቸውን ልክ ያውቀዋል።
ለካስ ሁሉም ልክ አለውና ጀግናም፣ ይወድቃል!!! ማመን ቢያቅተው ዳዊት እንዲህ አለ፤ ኃያላን እንዴት ወደቁ? 2ኛ ሳሙ 1፤19
እኛስ አሁን እያርበደበዱን፣ እያስደነገጡን፣ እያሳቀቁን ያሉ ስንት ጀግና የሆኑ፣ ሀጢያቶች፣ ልማዶች፣ ወጎች፣ እውቀቶች የሉም ብላችሁ ነው? መቼስ እንደ አቅም አቅማችን እኮ ብዙ ዓይነት ኃያላን፣ ሲያስጨንቁን እና ሲያሳድዱን አልኖሩም ብላችሁ ነው? አንዴ ኃጢአት ሲጀግንብን፣ አንዴ በሽታ ሲጀግንብን፣ አንዴ ሞት ሲጀግንብን፣ አንዴ ችግር ሲጀግንብን አልኖረም ብላችሁ ነው?
ግን ለኃያላንም የገዙበት ጊዜ በቃቸውና፣ ወደቁ። በቃ ወደቁ።።።።።።።። ምንም ማድረግ አይቻልም፡ ወ----ደ-----ቁ።።።።።። የኃያላን ሁሉ ኃያል ኢየሱስ መጣባቸዋ!!!
እግዚአብሔር የጽዮንን ምርኮ በመለሰ ጊዜ ሕልም እንጅ እውን አልመሰለንም ነበር። በዚያን ጊዜ አፋችን በሣቅ፣ አንደበታችንም በእልልታ ተሞላ። በዚያን ጊዜም በህዝቦች መካከል እግዚአብሔር ታላቅ ነገር አደረገላቸው ተባለ። እግዚአብሔር ታላቅ ነገር አደረገልን፤ እኛም ደስ አለን። መዝ 126: 1 አ---ሜ----ን።
---------ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 29 ቀን ቀርቶታል

ምድረበዳየን ወደድኩት!!!!

ዲቮሽን 336/07፥ ረቡዕ፥ ነሐሴ 6/07 ዓ/ም
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)
ምድረበዳየን ወደድኩት!!!!
ከሕዝብ ግርግር አወጣኸኝ፣ የሕዝቦች መሪ አድርገህ አስቀመጥኸኝ። መዝ 18፡43
በመከራ እያለፋችሁ ይሆን?
እግዚአብሔር ለእኛም ሆነ ለሰው ደስ የማይሉ የሕይወት መንገዶቻችንን እንዴት አድርጎ እንደሆነ ሳይታወቅ፣ ወደ መልካም ይለውጠዋል።
ድቅድቁን ጭለማ፣ ምንም ተስፋ የማይታይበት መንገዳችንን እግዚአብሔር ለሹመት ያደርገዋል።
ለካስ እኛ እያለቀስን፣ ለካስ እኛ እየከፋን የንግሥና ትምሕርት ቤት ገብተን ነው። ለዚያ እኮ ነው እግዚአብሔር ዝም የሚለው። ነገ የሚያደርግልልንን ስላየ፣ አይ ልጆቼ ያዘጋጀሁላችሁን ብታውቁ እኮ ያሁኑ ጨለማ እንደ ንጋት ፀሐይ ይሆንላችሁ ነበር እያለ፣ የእኛ ኢየሱስ ዝምምም ይላል።
ሰዎች ሲንቁን፣ ሲሰድቡን፣ ስንታመም፣ ስንሳቀቅ፣ ስንሸማቀቅ፣ የሚያጽናና ሲጠፋ፣ ሰው ፍለጋ ስንንከራተት ዓይናችን በእንባ ሲታጠብ---- ምስጢሩ እኮ፡ የንግስና ትምህርት ቤት ገብተን ነው።
እንዴ! እሱ እግዚአብሔር ነዋ! ሕይወታችን በመከራ እየተቀመመ ሙሉ ሰው ሊወጣን እኮ ነው።
እና ዛሬ "እግዚአብሔር ሆይ ምድረበዳየን እወደዋለሁ። ስለምድረበዳየ አመሰግንሃለሁ" ብንለውስ?
ግዴላችሁም፣ እንበል። አስደናቂ ነገር ከፊታችን ስላለ እኮ ነው! ገባችሁ ያልኩዋችሁ? በሁሉም አቅጣጫ ሙሉ ሆነን ልንገለጥ እኮ ነው! ባለሙሉ ስልጣን የክርስቶስ እንደራሴ ልንሆን ነው እኮ!!!
አባብላታለሁ፥ ወደ ምድረ በዳም አመጣታለሁ፥ ለልብዋም እናገራለሁ። ከዚያም የወይን ቦታዋን፥ የተስፋ በርም እንዲሆንላት የአኮርን ሸለቆ እሰጣታለሁ፤ በዚያም ከግብጽ ምድር እንደ ወጣችበት ቀን እንደ ሕፃንነትዋ ወራት ትዘምራለች። ሆሴዕ 2:16
---------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 30 ቀን ቀርቶታል