ዲቮሽን ቁ.56/07 ረቡዕ፣ ጥቅምት
26/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)
ዲያስፖራ (#1) – የቤት ሠራተኞች!
ከሶርያውያንም አገር አደጋ ጣዮች ወጥተው ነበር፥
ከእስራኤልም ምድር ታናሽ ብላቴና ሴት ማርከው ነበር፤ የንዕማንንም ሚስት ታገለግል ነበር። እመቤትዋንም። ጌታዬ በሰማርያ ካለው
ከነቢዩ ፊት ቢደርስ ኖሮ ከለምጹ በፈወሰው ነበር አለቻት(2ነገ 5፡1-4)።
በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሐበሾች በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ተበትነው
ይገኛሉ፡፡ በስደት፣ በሥራ፣ በሕጋዊ ነዋሪነት በሚኖሩባቸው በእነዚህ አገሮች በአጠቃላይ በሐበሻነታቸው፣ በተለይም በየእምነታቸው
አቅጣጫ ይቀራረባሉ፡፡ የወንጌል አማኞችም በያሉበት አካባቢ እየተፈላለጉና ምኩራብ እየሠሩ መንፈሳዊ ኅብረት ያደርጋሉ፡፡ ይህ
የሚደገፍ ልማድ ነው!
ይሁንና ይህ ልማድ ሊፈተሹ የሚገባቸው በርካታ ጎኖች
አሉት፡፡ ከእነዚህም መካከል በምንኖርባቸው አገሮች ለሚገኙ ሌሎች ሰዎች ወንጌል የመስበክ ልማዳችን ደካማ ነው፡፡ ነብር
ዝንጉርጉርነቱን እንደማይለቀው ሁሉ ሐበሾችም በየሄዱበት ሀገሮች ሁሉ ከራሳቸው ወገን ጋር ብቻ የመፈላለግና ኅብረት የማድረግ
ጠባይ አይለቃቸውም፡፡ አንዳንዴም፣ በሀገራችን ያለው በቋንቋና በብሔረሰብ መካከል የሚታየው የመጠላላት መርገም ተከትሏቸው
ይሄዳል፡፡
ሐበሾች የሚኖሩባቸውን ሀገሮች ቋንቋ ጠንቅቀው ቢያውቁም፣
የሚኖሩበትን ሕዝብና ባህል አሳምረው ቢለምዱም ‹‹ዘመድ ከዘመዱ›› እንዲባል፣ ምርጫቸው ሐበሻዊ ነው! በአጠገባቸው ሺህ ጊዜ
ሺህ ፓስታ እስፓጌቲ፣ እልፍ ጊዜ እልፍ ራይስና ቻፓቲ ቢኖር ምርጫቸው ከርቀት የሚገኘው እንጀራና ዳጣ፣ ሽሮና ምጥሚጣ ነው!
ወገኖች ሆይ፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ ዲፓስፖራ እንማር! በጦር ምርኮኝነት ተወስዳ በሶርያ ጦር ሠራዊት አለቃ ለሆነው ለለምጻሙ ንዕማን በቤት ሠራተኝነት ታገለግል የነበረው ታናሽ ብላቴና(2ነገ 5)፣ የግብጹ ፈሪኦን የዘበኞች አለቃ ለሆነው ጲጥፋራ በቤት ሠራተኝነት ያገለግል የነበረው ዮሴፍ(ዘፍ 39)፣ እና የፋርስ ንጉሥ የአርጤክሲስ ቀዳማዊ ወይን ጠጅ አሳላፊ የነበረው ነህሚያ…ዲፓስፖራ የቤት ሠራተኞች ናቸው፡፡
ወገኖች ሆይ፣ እነዚህ ዲፓስፖራ
የቤት ሠራተኞች በሚሠሩባቸው
ቤቶች ውስጥ የሚያስገርሙ ነገሮች ማከናወናቸውን እናውቃለን፡፡ የንዕማን ሠራተኛ
በእስራኤል ምድር ከለምጽ የሚፈውስ ነቢይ የመኖሩን ወንጌል ለእመቤትዋ ሰብካለች፡፡ በስብከቱ መሠረትም ንዕማን ወደ እስራኤል
ምድር ሄዶ ከለምጹ ተፈወሰ፡፡
ይህ ታላቅ ባለሥልጣን በዚህች ታናሽ ብላቴና የወንጌል ስብከት ተለውጦ ከእስራኤል ዘንድ በቀር
በምድር ሁሉ አምላክ አለመኖሩን መስክሮ፣ ከእንግዲህ ወዲህ ከእግዚአብሔር በቀር ለሌሎች አማልክት የሚቃጠል መሥዋዕት ወይም ሌላ
መሥዋዕት ላለማቅረብ ወሰነ፡፡ የመስገጃውን አፈር እንኳ ከእስራኤል ምድር ጭኖ በመጣው አፈር ቀይሮ እስራኤልን አምላክ ማምለኩን
እናውቃለን፡፡
ወገኖች ሆይ፣ የቤት ሠራኞቹ ዮሴፍ እና
ነህሚያ የሠሩትን እናውቃለን፡፡ እግዚአብሔር ከዮሴፍና ከነህሚያ ጋር በመኖሩ የሚሠሩትን
ሥራ እንዳከናወነላቸው፣ የእጆቻቸው ሥራ ሁሉ እንደተባረከ እናውቃለን፡፡ እነዚህ የቤት ሠራተኞች ከራሳቸው ተርፈው ለእግዚአብሔር
ሕዝብ በረከት እንደሆኑ እናውቃለን፡፡
ወገኖች ሆይ፣ በትምህርት፣ በስደት፣ በሥራ፣ በነዋሪነትም ይሁን በሌሎች ሁኔታዎች በዲያስፖራነት በቤት
ሠራተኝነት እየሠራን ሊሆን ይችላል፡፡ የንዕማን የቤት ሠራተኛን እናስብ! ስለ ጌታችንና መድኃኒታችን ስለ
ኢየሱስ ክርስቶስ ለምናገለግላቸው ቤተሰቦች ልንመሰክር እንችላለን፡፡ አዳኝነቱን፣ ፈዋሽነቱን፣ ጌትነቱን ፍቅሩንና ምሕረቱን ልንመሰክር
እንችላለን፡፡
ወገኖች ሆይ፣ ዮሴፍንና ነህሚያን እናስብ! በምናገለግልበት ቤት ፈሪሃ እግዚአብሔርን በማሳየት፣ የተሰጠንን ሥራ በታማኝነትና
በትጋት በማከናወን፣ በምናገለግለው ቤተሰብ ውስጥ በእጅ ንጽህናና በቅድስና በመመላለስ ወንጌልን ልንመሰክር እንችላለን፡፡
-------------------------
(ይህን
ዕለታዊ
ዲቮሽን
ላይክና ሼር ያድርጉ፣ ወዳጅ ጓደኞችዎም
እንዲያገኙ
ያግዙ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!)