Monday, November 17, 2014

ፍሬ ያለባቸው!

ዲቮሽን ቁ.68/07     ሰኞ፣ ሕዳር 8/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)


ፍሬ ያለባቸው!  

ዛፍ በፍሬው ይታወቃል፡፡ መልካም ዛፍ መልካም ፍሬ ያፈራል፤ ከመጥፎ ዛፍ ግን መልካም ፍሬ አይጠበቅም (ማቴ 12፡33)

ወዳጄ ሆይ፣ ፍሬ ባለባቸው ዛፎችና ፍሬ በሌለባቸው ዛፎች መካከል ያለውን ልዩነት አስተውለው ያውቃሉ? ፍሬ ያለባቸው ዛፎች ራሳቸውን ዝቅ ያደርጋሉ! ብዙ ፍሬ ያለባቸው ራሳቸውን ብዙ ዝቅ ያደርጋሉ! ፍሬ የሌለባቸው ዛፎች ራሳቸውን ከፍ ያደርጋሉ!

ወዳጄ ሆይ፣ ጌታ ኢየሱስን ያስቡ! የቃል እውቀቱን፣ የማስተማር ብቃቱን፣ ግርማና ሞገሱን፣ ዝና አድናቆቱን፣ ክብሩን ታላቅነቱን ያስቡ! በውሃ ላይ መሄዱን፣ የሞተን ማስነሳቱን፣ ድንቁን ተአምራቱን አስቡ!

ወዳጄ ሆይ፣ የዚህ ታላቅ ጌታ፣ ታላቅ አገልግሎት ራሱን ዝቅ እንዳያደርግ አልከለከለውም! ከማዕረጉ ወርዶ እግር እንዳያጥብ አላስቸገረውም! የዝናው ከፍታ፣ የእውቀቱ ችሎታ አላስኮፈሰውም!

ወዳጄ ሆይ፣ ከጌታ የሆነ ፍሬ ሲበዛልን ራሳችን ዝቅ ይላል! ከጌታ የሆነ እውቀት ሲበዛልን ራሳችን ዝቅ ይላል! ጸጋ ሲበዛልን ራሳችን ዝቅ ይላል! መንፈሳዊነታችን ራስን ዝቅ በማድረግ ተገልጦ ይታያል! እውነተኛነታችን በዚህ ይፈተናል! የአገልግሎት ኩራት፣ የደረጃ ትምክህት፣ የልሂቀት ትዕቢት አጋንንታዊ ነው! ስብከት ዝማሬያችን፣ ጸሎት አምልኳችን ራስን ከፍ ለማድረግ የሚጥር የፍሬ ቢስነት አንዱ ምልክት ነው!

-------------------------

(እባክዎ፣ ይህን ዕለታዊ ዲቮሽን ላይክ ያድርጉ፣ ወዳጅ ጓደኞችዎም እንዲያገኙ ያግዙ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!)