Tuesday, August 25, 2015

ተሻገርን!!!

ዲቮሽን 347/07፥ እሁድ፥ ነሐሴ 17/07 ዓ/ም 
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)

ተሻገርን!!!

እነዚህማ በዚያ ስፍራ አይገኙም፤ የዳኑት ብቻ ይሄዳሉ። ኢሳ 35፡5
አይ ጠላት!!! የሞተ መሆኑን ራሱ በራሱ ጊዜ ማስመስከር ፈለገና፣ በሰረገላና በፈረስ ሆኖ ሊያሳድደን ጀመረ አይደል? እኛ፣ በጌታ መንፈስና እና ኃይል እንደምንንቀሳቀስ አላወቀ! የትኛው ቴክኖሎጂ እና ጥበብ ነው፣ ውሃን እንደ ግድግዳ ያቆመ! የትኛው አስማተኛና ጠንቋይ ነው ተከታዮቹን በውሃ ውስጥ ያስኬደው! የትኛው የሉሲፈር ጥበብ ነው በእሳት ውስጥ ጭፍሮቹ ሲያልፉ የታደጋቸው!
እኛማ ድነናል! ጠላት ይስማ! ድ-ነ-ና-ል!!! ኢየሱስ በመስቀል ላይ ኃጢያታችንን በደላችንን መከራችንን ሁሉ ተ-ፈ-ጸ-መ ብሎ አዲስ ሰው አድርጎናል።
ስለዚህ በውሃ ውስጥ እንሄዳለን፣ አንሰጥምም!! በእሳት ውስጥ እናልፋለን አንቃጠልም፣ ነበልባሉም አይፈጀንም!!!!
ለእኛ የተከፈተ መንገድ ለእኛ ብቻ ነው። ጠላትን አይመለከተውም።
አይ ጠላት ሞኙ፣ ደሞ ብሎ ብሎ አባታችን ለእኛ በከፈተው መንገድ ሊሄድ ያምረዋል? ምን ያለው ትእቢተኛ እና ክፉ ነው! ምንስ ያህል አመፀኛ ነው! ለነገሩ አንዴ ለጥፋት ስለተጻፈ፣ መከታተሉ አይቀርም። ምክንያቱም እግዚአብሔር የጠላታችን መታሰቢያው እስከማይገኝ ድረስ ነውና ድምጥማጡን ማጥፋት የሚፈልገው፣ ስለዚህም ዝም ይለዋል።
ዲያብሎስ ከነጭፍሮቹ ሰጠመ፣ እኛ ግን በደረቅ ተሻገርን። የፈርዖን ፈረሶች፣ ሰረገሎችና፣ ፈረሰኞች ተሰብስበው ሰጠሙ፣ እኛን ግን አምላካችን ውሃውን ግራና ቀኝ እንደግድግዳ አድርጎልን በደረቅ ባሕሩን ተሻገርን።
ዐይን ያላየውን፣ ጆሮ ያልሰማውን፣ የሰውም ልብ ያላሰበውን እግዚአብሔር ለሚወዱት አዘጋጅቷል። 1ቆሮ 2፡9
---------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 19 ቀን ቀርቶታል

No comments:

Post a Comment