Sunday, July 5, 2015

ሁሉ – ለማነጽ ይሁን !

ዲቮሽን 298/07፥ እሁድ፥ ሰኔ 28/07 ዓ/ም
(በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)

ሁሉ – ለማነጽ ይሁን !

እንግዲህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ምንድር ነው? (ምን እንበል?) በምትሰበሰቡበት ጊዜ … ሁሉ ለማነጽ ይሁን(1 ቆሮ 14፡26)።

በብዙ ምክንያቶች ስብሰባ እናደርጋለን፡፡ በቤተሰብ ጉዳይ ላይ ለመነጋገር – ለመመካከር፣ በቤተክርስቲያን ጉዳይ ላይ ለመነጋገር – ለመመካከር፣ በቤተእምነት ጉዳይ ላይ ለመነጋገር – ለመመካከር፣ በሀገር ጉዳይ ላይ ለመነጋገር – ለመመካከር፣ ልዩ ልዩ ዓይነት ስብሰባ እናደርጋለን፣ በተለያዩ ጉባዔዎች ላይ እንቀመጣለን፡፡

ወገኖች ሆይ፣ የአጥቢያ ቤተክርስቲያን ውስጥ የሽማግሌዎች ስብሰባ፣ የዲያቆናት ስብሰባ፣ የኮሚቴ ስብሰባ፣ የጸሎት ኅብረት ስብሰባ፣ የመዘምራን ስብስባ፣ የቤት ለቤት ኅብረት ስብሰባ፣ የወጣቶች ስብሰባ፣ የባለትዳሮች ስብሰባ፣ ሌሎችም ከሕጻናት እስከ ዐዋቂ ብዙ ዓይነት ስብሰባዎች እናደርጋለን፡፡

ወገኖች ሆይ፣ ማናቸውም ዓይነት ስብሰባ ይሁን፣ ብቻ በምንሰበሰብበት ጊዜ አንድ መሠረታዊ መርህ መጠበቁን እናስተውል – ሁሉ ለማነጽ ይሁን! በቃለጉባኤያችን ሁሉ፣ በውይይት ጊዜያችን ሁሉ፣ በድምጸ ውሳኔያችን ሁሉ፣ በአቋም መግለጫችን ሁሉ … ይህ መርህ መጠበቁን እናስተውል – ሁሉ ለማነጽ ይሁን!

ወገኖች ሆይ፣ ስንሰብክ–ስናስተምር፣ ስንጽፍ–ስናሳትም፣ ስንነግድ–ስናተርፍ፣ ስናወራ–ስንሰማ፣ ስንወርድ–ስንወጣ … ይህ መርህ መጠበቁን እናስተውል – ሁሉ ለማነጽ ይሁን!

 ------------------

ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6 ቀን 2007 ላይ ይጠናቀቃል፡፡ በዚህ ዓመት ብቻ ዲቮሽኑን የሚከታተሉ ከ15000 በላይ ሰዎች ከመላው ዓለም ማፍራት ተችሏል፡፡ ዲቮሽኖቹ፣ ሰዎች ወደጌታ እንዲመጡ፣ በርካታዎቹም ከውድቀታቸው እንዲነሱና ከስብራታቸው እንዲጠገኑ፣ በርካታዎቹም እንዲታነጹ …ምክንያት ሆነዋል፡፡ ክብሩን ሁሉ ጌታ ይውሰድ፡፡
እነዚህን ዲቮሽኖች ሰብስቦ በአንድ መጽሐፍ ላይ ለማሳተምና መስከረም 2008 ዓ.ም. ላይ ለአንባቢዎች ለማድረስ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡
በሀገራችን ታሪክ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነውንና አንድም ቀን ሳይቋረጥ ዓመቱን ሙሉ ለአንባቢዎች ይቀርብ የነበረውን፥ እንዲሁም በርካታ ነጻ አስተያየቶች ሲሰጡበትና በርካታ ቅዱሳን ሲጸልዩለት የቆዩትን ይህን የጥሞና መጽሐፍ ሁሉም የዲቮሽኑ ተከታታዮችና ሌሎችም ሊያገኙት ይገባል የሚል ራዕይ ተይዟል፡፡
ይህን ታሪካዊ መጽሐፍ፣ የማሳተሚያ ወጭ በገንዘብ ለመደገፍ የምትፈልጉ፣ ወይም ገፆች በመግዛት በመጽሐፉ ላይ የድርጅታችሁንና የአገልግሎታችሁን ዓላማዎች ለአንባቢያን ማስተዋወቅ የምትፈልጉ፣ ምርቶቻችሁንና ማናቸውንም አገልግሎታችሁን በማስታወቂያ ማስተላለፍ
የምትፈልጉ በሀገር ውስጥና ውጭ የምትገኙ ወገኖች ሁሉ ባሉን ውስን ገጾች ውስጥ ቦታ አስቀድሞ በመያዝ ራዕዩን መደገፍ ትችላላችሁ፡፡
ሁሉም የዲቮሽኑ ተገልጋይ የነበራችሁ አነሰ በዛ ሳትሉ በዲቮሽኑ የተባረካችሁ መሆኑን የሚያሳይ የፍቅራችሁን ስጦታ ልታበረክቱ ትችላላችሁ፡፡ ለዚህ ጥሪ የምትመልሱት የፍቅራችሁ ምላሽ፥ ለቀጣዩና ጌታ በልቤ ያስቀመጠውን ለየት ያለ አገልግሎት ወደእናንተ ይዤ እንድመጣ የበለጠ የሚያነሳሳኝ መሆኑንም አትርሱ፡፡ ዓመቱን ሙሉ በዲቮሽኑ ስትባረኩበት ነበር፥ አሁን ደግሞ እኔን ለመባረክ ተራውና ዕድሉ ወደእናንተ ቀርቧልና ተጠቀሙበት፡፡ ጌታ ይባርካችሁ፡፡
ለተጨማሪ መረጃ፣ በሞባይል 0911-678-158 መደወል ይቻላል፡፡ ዓመቱን ሙሉ አብራችሁን ለነበራችሁ ወገኖች ሁሉ ከፍ ያለ ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡ በዲቮሽኑ መቆም ልባችሁ ለሚያዝንብን ወገኖች ደግሞ ከፍ ያለ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡ ጌታ ይባርካችሁ፡፡ የናንተው አገልጋይ፥ ፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ

ማንን ያገኝ ይሆን!

ዲቮሽን 297/07፥ ቅዳሜ፥ ሰኔ 27/07 ዓ/ም
(በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)

ማንን ያገኝ ይሆን!

የጌታንም ድምፅ። ማንን እልካለሁ? ማንስ ይሄድልናል? ሲል ሰማሁ። እኔም። እነሆኝ፥ እኔን ላከኝ አልሁ (ኢሳ 6:8)::

በትናንትናው ዲቮሽን ላይ፥ ንጉሡ ዖዝያን ከፍ ከፍ ካለ በኋላ ልቡ እንደታበየና በእግዚአብሔርም ላይ ስንፍና እንደሠራ፥ በዚህም ምክንያት እግዚአብሔር በለምጽ እንደቀሰፈው፥ እስከሚሞትም ድረስ በኳራንታይን (የተገለለ ቤት) ውስጥ ተዘግቶበት የውርደት ሞት መሞቱን ተመልክተናል፡፡

ዛሬ ደግሞ፥ ንጉሡ ዖዝያን በሞተበት ዓመት እግዚአብሔርን በረጅምና ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ተቀምጦ፥ የልብሱም ዘርፍ መቅደሱን ሞልቶት ለነቢዩ ኢሳይያስ ሲገለጥለትና "የምልከው ሰው እፈልጋለሁ" ሲል እንሰማለን ።

ወገኖች ሆይ፥ የእግዚአብሔር ነገር፥ የቤቱ አሠራር ይገርማል! አንዱን ያነሳል ሌላኛውን ይጥላል! ትዕቢተኛውን አዋርዶ የተዋረደውን ያከብራል! የአንዱን ሹመት ሽሮ ሌላኛውን ይሾማል!

ወገኖች ሆይ፥ ጌታ ሁልጊዜ ሰው እንደፈለገ ነው! እንደ ፈቃዱና እንደ ልቡ ሐሳብ ወጥቶ የሚገባ ሰው እንደፈለገ ነው! የእግዚአብሔር አፍ ሆኖ፥ መልዕክተኛ ሊሆንየተዘጋጀ ሰው እንደገለገ ነው!

ወገኖች ሆይ፥ ጌታ ሰው ሲፈልግ በሕልምና ራዕይ በማናቸውም መንገድ ለሰው ልጆች ሁሉ ሊገለጥ ይችላል፡፡ ነገር ግን ወገኖች፥ ጌታ ሰው ሲፈልግ "እሺ" የሚልና "አለሁልህ" ባይ ሰው በጣም ይፈለጋል! ለተገለጠ ራዕይ እሺ የሚልና የተዘጋጀ ሰው ሊቀባ ይችላል፡፡

ወገኖች ሆይ፥ የሠራዊት ጌታ ነቢይ እንደፈለገ ነው! የመንግሥቱን ሥርዓት ለሰው ልጆች ሁሉ በድፍረት ሊናገር በእውነት የቆረጠ - በነፍስ በሥጋና በመንፈሱ ሁሉ የተወራረደ እንደፈለገ ነው! ዛሬ ጌታ መጥቶ፥ የሚቀባውንና የሚልከውን ሰው ሲፈልግ ብናገኝ፥ "እነሆኝ አምላኬ፥ እኔ አለሁልህ፥ እኔን ቀባኝና፥ እኔን ላከኝ" ብለን እንመልስ ይሆን? ጥሪው ዛሬ ቢሆን፥ ጥሪው አሁን ቢሆን - ጌታ እሺ የሚለውን ማንን ያገኝ ይሆን?