Monday, January 12, 2015

የሽማግሎች – ወግ!


ዲቮሽን .124/07     ሰኞጥር 4/07 ..
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)


የሽማግሎች – ወግ!

በዚያን ጊዜ ጻፎችና ፈሪሳውያን ከኢየሩሳሌም ወደ ኢየሱስ ቀረቡና። ደቀ መዛሙርትህ ስለ ምን የሽማግሎችን ወግ ይተላለፋሉ? እንጀራ ሲበሉ እጃቸውን አይታጠቡምና አሉት።
እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ እናንተስ ስለ ወጋችሁ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ስለ ምን ትተላለፋላችሁ?(ማቴ 15፡1-3)

ጻፎችና ፈሪሳውያን ይህን ጥያቄ ለኢየሱስ ክርስቶስ ከማቅረባቸው ቀደም ብሎ፣ የመጥምቁ ዮሐንስን በሰይፍ ተቀልቶ የመሞቱንና በደቀመዛሙርቱም የመቀበሩን ዜና እናነባለን፡፡ ጌታችን ኢየሱስ የዮሐንስን ዜና ሰማዕት ሰምቶ እጅግ ከማዘኑ የተነሳ፣ ብቻውን ወደ ምድረ በዳ በታንኳ ፈቀቅ አለ፡፡ ግን ሕዝቡ ይህን ሰምቶ ነቅሎ ተከተለው፡፡ ያለስንቅ ወደ ምድረ በዳ የወጣው ሕዝብ ተራበ፡፡ ጌታም አዘነላቸውና በጥቂት ዓሳና ዳቦ የሴቶችና የልጆች ቁጥር ሳይጨምረ፣ ከአምስት ሺህ በላይ የሆኑ ወንዶችን አጠገበና ሸኘ፡፡

ወገኖች ሆይ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ አሁንም ለብቻው መሆን ፈለገ፡፡ የዮሐንስ ሞት ሐዘን አልለቀቀውምና ሰው ለብቻው እንዲተወው ፈለገ፡፡ ስለሆነም፣ ደቀመዛሙርቱን ጨምሮ ሁሉም ሰው ከባህር ማዶ እንዲሻገር አሰናብቶ ምሽቱንም ለብቻው ነበረ።  ነገር ግን፣ ደቀመዛሙርቱ በባህር ላይ ሲሄዱ ማዕበል ተነስቶ ሲጨነቁ ሳለ ጌታ በባህሩ ላይ እየተራመደ መጥቶ ማዕበሉን ጸጥ አደረገ፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን፣ ጴጥሮስም ከታንኳይቱ ወርዶ በውኃው ላይ እንዲሄድ አደረገው፡፡ ብዙ ሕመምተኞች ወደ እርሱ ሲመጡ፤ የልብሱንም ጫፍ ሲዳስሱና፣ የዳሰሱትም ሁሉ ሲድኑ ነበር፡፡

ወገኖች ሆይ፣ ለጻፎችና ፈሪሳውያን መንግሥተ ሰማያት መቅረቧን በማብሰር መላውን እስራኤል ወደ ንስሐ ይጠራ የነበረው የመጥምቁ የዮሐንስ በግፍ አንገቱ ተቀልቶ መሞት፣ በዮሐንስ ሞት ምክንያትም ኢየሱስ ክርስቶስ ይሰማው የነበረው ስሜት፣ በኢየሱስ የተደረገው ይህ ሁሉ ድንቅና ተአምራት፣ ፈውስና ምልክት፣ ጉዳያቸው አልነበረም! ጻፎችና ፈሪሳውያን ይጨነቁለት የነበረው አንድ ብርቱ ጉዳይ ብቻ ነበር– እርሱም የሽማግሎች ወግ ነው!

ወገኖች ሆይ፣ የተራበን ከመመገብ፣ የታመመን ከመፈወስ፣ ማዕበልን ከማዘዝ፣ ሰውን በባህር ከማራመድ ይልቅ ጻፎችና ፈሪሳውያን ያስጨንቃቸው የነበረው ብርቱ ጉዳይ የሽማግሎች ወግ ነው! ደቀመዛሙርት ውሃ በሌለበት በምድረ በዳ፣ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ራብተኞችን ሲመግቡ፣ ‹‹ጎሽ!›› ያላሏቸው ጻፎችና ፈሪሳውያን፣ እንጀራ ሲበሉ እጃቸውን ባለመታጠባቸው ሲከስሷቸው እናያለን! የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ሲያፈርሱ ምንም የማይሰማቸው ጻፎችና ፈሪሳውያን ለእጅ መታጠብ ወግ ሲቆረቆሩ እናያለን፡፡

ወዳጄ ሆይ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ለጻፎችና ፈሪሳውያን ክስ የሰጣቸውን ምላሽ እንስማ! እናንተስ ስለ ወጋችሁ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ስለ ምን ትተላለፋላችሁ?
-----
ትምህርቱ ጠቅሞታል? እንግዲያውስ ላይክ ያድርጉ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!
--------------------------------
‹‹የወንጌላዊ እጮኛ›› በሙሉጊዜ አገልጋዮች ላይ የሚያጋጥሙ እውነተኛ ታሪኮች የያዘ በሺዎች የተደነቀ ልብ አንጠልጣይ መጽሐፍ፣ በገበያ ላይ ውሏል፡፡ ለተጨማሪ መረጃ በ0911 678158 ወይም 0911 813092 ይደውሉ፡፡

ጽድቃችን – እንደ ‹‹ሞዴስ››!


ዲቮሽን .123/07     እሁድጥር 3/07 ..
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)


ጽድቃችን – እንደ ‹‹ሞዴስ››!

… ሁላችን እንደ ርኩስ ሰው ሆነናል፥ ጽድቃችንም ሁሉ እንደ መርገም ጨርቅ ነው ሁላችንም እንደ ቅጠል ረግፈናል፥ በደላችንም እንደ ነፋስ ወስዶናል(ኢሳ 64፡6)፡፡

እግዚአብሔር ሰማያትን ቀድዶ ቢወርድና፣ ቢመለከተን እንዴት ያገኘን ይሆን? ከሰማያት ሲወርድ ሰማያት የተንቀጠቀጡለት፣ ተራሮች የጬሱለት፣ ባህር ውቅያኖሱ የተናወጠለት ጌታ እግዚአብሔር ሰማዮችን ቀድዶ ወደእኛ ቢወርድ እንዴት ያየን ይሆን?

ወገኖች ሆይ፣ ሙሽራው ሙሽሪትን ሊወስድ ሲመጣ ሰው ሁሉ ለማየት እንደሚጋፋ፣ ጌታ ሲመጣ ጌታን ለማየት እንጋፋ ይሆን? ሙሽራውን ሙሽሪትን ለማየት እንደምንጠራራው፣ ጌታ ሲመጣ እርሱን ለማየት እንጓጓ ይሆን?

ወገኖች  ሆይ፣ እግዚአብሔር ጻድቅ ነው! እኛ ደግሞ ኃጢአተኞች ነን! የእግዚአብሔር ጽድቅ ፍጹም ሲሆን፣ የእኛ ኃጢአት ደግሞ እንደ ሞዴስ ጨርቅ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ጽድቅ በቃላት ሊገልጡት ከሚችሉት በላይ ፍጹም ሲሆን፣ የእኛ ኃጢአት በእግዚአብሔር ዓይን ሲታይ ደግሞ አስነዋሪነቱ እንደ ሞዴስ ጨርቅ ነው! ሺህ ጊዜ ሺህ ስንጸድቅ ብንውል፣ እንፍ ጊዜ እልፍ እልፍ ስንቀደስ ብንውል፣ በእግዚአብሔር ዓይን ሲታይ ያ ሁሉ ልፋት እንደ ሞዴስ ጨርቅ ነው!

ማንም ሰው በእግዚአብሔር ሊጸድቅ አይችልም! ጽድቃችን ክርስቶስ ነው! ይህንን የክርስቶስን ጽድቅ በንስሐ ተቀብለን፣ በክርስቶስ ኢየሱስ ደም ታጥበን፣ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃንና ቅዱሳን ሆነን ልንገኝ ይገባል!

ወገኖች ሆይ፣ ነቢዩ ኢሳይያስ አገልግሎቱን የጀመረ አካባቢ፣ የሌሎች ሰዎችን ኃጢአት እየተመለከተ፣ ይል ነበር፡፡ ነገር ግን፣ ከምዕራፍ ስድስት በኋላ መልዕክቱ ተቀይሮ፣ ‹‹ወዮልኝ፣ ወዮልኝ!›› ማለት ጀመረ፡፡ ይህም ለውጥ የመጣው፣ በቅድስናው ከፍ ያለ እግዚአብሔር ከፍ ባለ ዙፋኑ ላይ ተቀምጦ ስለታየው ነው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፡፡

ወገኖች ሆይ፣ ነቢዩ ኢሳይያስ በምዕራፍ 6 ላይ የታየው የከንፈሮቹ እርኩሰት ነበር፡፡ ይህን ኃጢአቱን ተናዘዘና ጌታ በደሉን አስወግዶለት፣ ለኃጢአቱም ስርየት ሰጠው፡፡ ከዚያም የእግዚአብሔር መልዕክተኛ ሆኖ ተላከ! ወገኖች ሆይ፣ ኃጢአት የማያቋርጥ ትግል ይጠይቃልና፣ ነቢዩ ኢሳይያስ በምዕራፍ 64 ላይ፣ የእርሱም ሆነ የእስራኤላዊያን ጽድቅ፣ እንደ ሞዴስ ጨርቅ መሆኑን እየመሰከረ በማናዘዝ ላይ ነው!

ወዳጄ ሆይ፣ እግዚአብሔር ሰማያትን ቀድዶ ቢወርድና፣ ቢመለከትዎ እንዴት ባለ ሕይወት ያገኘዎ ይሆን? አለኝ የሚሉት ‹‹ጽድቅ›› እንደ መልካም ሽቱ የሚያውድና ይጣፍጠው ይሆን? ወይስ እንደ ሞዴስ ጨርቅ የሚጸየፈው?
-----
ትምህርቱ ጠቅሞታል? እንግዲያውስ ላይክ ያድርጉ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!
--------------------------------
‹‹የወንጌላዊ እጮኛ›› በሙሉጊዜ አገልጋዮች ላይ የሚያጋጥሙ እውነተኛ ታሪኮች የያዘ በሺዎች የተደነቀ ልብ አንጠልጣይ መጽሐፍ፣ በገበያ ላይ ውሏል፡፡ ለተጨማሪ መረጃ በ0911 678158 ወይም 0911 813092 ይደውሉ፡፡