Saturday, August 22, 2015

ሮኆቦት ሆነልን!!!!!

ዲቮሽን 343/07፥ ረቡዕ፥ ነሐሴ 13/07 ዓ/ም 
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)

ሮኆቦት ሆነልን!!!!!

አሁን እግዚአብሔር ሰፊ ቦታ ሰጥቶናል፤ እኛም በምድር ላይ እንበዛለን። ዘፍጥረት 26፡22
ካንድ ቦታ ወደሌላው ስትፈናቀሉ፣ ካንድ ሥፍራ ወደ ሌላው ስትሔዱ፣ የያዛችሁት ሁሉ ብትን ብሎ ሲጠፋ ታለቅሳላቸሁ አይደል? የጀመራችሁት ነገር ዳር ሊደርስ ሲል ሲጨናገፍ፣ እናንተም ስታለቅሱ፣ ጠላትም ስታለቅሱለት፣ ዳዊት ጋ እንደፎከረው፣ “በእግዚአብሔር ተማምኖአል፣ እንግዲህ እርሱ ያድነው፣ ደስ የተሰኘበትን እስኪ ይታደገው” መዝ 22፡8 እያለ ይፎክርባችኋል አይደል? አይ ጠላት ሞኙ! ትንቢት እያወጣብን መሆኑን መች አወቀ! አላወቀም እንጅ እያንዳንዷ የእንባ ዘለላችን የጸሎት መስዋዕት ናት!
ብናለቅስስ? እናልቅሳ? ያለቀስነው እኮ ወደ አባታችን ነው። የተከራከርነው እኮ ከአባታችን ጋር ነው። ከንፈር መጦ ዝም ወደማይለው አባታችን እሪ ኡኡኡ ድረስልን ብለን ብናለቅስስ? እናለቅሳለን! ጠላት ምናገባው? እኛ ያለቀስነው፣ ባሕሩን ከፍሎ ወደሚያሻግረን አምላካችን! እኛ ያለቀስነው በምድረበዳ እንደ መንጋ ወደሚመራን አምላካችን! እኛ የምናለቅሰው ዐለቱን በምድረበዳ ሰንጥቆ እንደ ባሕር የበዛ ውሃ ወደሚያጠጣን አምላካችን፣ ምንጭ ከቋጥኝ አፍልቆ ውሃን እንደ ወንዝ ወደሚያወርደው አባታችን!
አሃ! አይ ጠላት! አልቃሻ እያለ ዝም ሊያሰኘን እኮ ነው! ነጭናጫ እያለ ሊወርሰን እኮ ነው! ሞኝ! እኛስ አንገኝም። ኤሴቅንም ጠላት ይውሰድ፣ ስጥናንም ለራሱ ያድርገው! እኛን የሚመጥነን ሮኆቦት ብቻ ነው። ምክንያቱም ብዙ ስለሆንን፣ ትንንሽ ነገር አ-ይ-መ-ጥ-ነ-ን-ም።
ወደ ሰፊ ስፍራም አወጣኝ፣ ደስ ተሰኝቶብኛልና አዳነኝ። መዝ 18፡19
-----
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 23 ቀን ቀርቶታል

No comments:

Post a Comment