Monday, August 10, 2015

ሙሉ በሙሉ አዲስ /Brand New/!!!!!

ዲቮሽን 335/07፥ ማክሰኞ፥ ነሐሴ 5/07 ዓ/ም 
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)


ሙሉ በሙሉ አዲስ /Brand New/!!!!!


ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል። 2ኛ ቆሮ 5፡17


በቤተክርስትያን ውስጥ እያለን፣ የእግዚአብሔርን ቃል እያወቅን፣ በዚያ በገባን እና በተረዳነው ልክ እንዳንመላለስ ብዙ እንቅፋቶች አሉብን። አንዱና ዋናው ዓእምሮአችን ነው። ይህ ዓእምሮአችን የማያስታውሰው ነገር ስለሌለ፣ በተለይ ክፉ ክፉ ገጠመኞቻችንን ከትቦ ስለሚያስቀር፣ የሕይወት እርምጃችን በመንፈስ ሳይሆን በስጋ እንዲሆን ይጫነዋል።


ለዚህም ነው፣ “እኔ እንዲህ ሆኜ የቀረሁት የሙት ልጅ ስለሆንኩ ነው፣ ቤተሰቤ በመጥፎ አስተዳደግ ስላሳደገኝ ነው፣ እናቴ ወይም አባቴ ጥቃት ስላደረሱብኝ ነው፣ በቂ የቀለም ትምህርት ስላላገኘሁ ነው፣ እልም ያለች ገጠር ውስጥ ስላደግሁ፣ ወይም በፈረንጅ አገር ስለኖርኩ ወ ዘ ተ ... እንላለን።


ተመልሰን ወደ ኃጢአት ስንገባም፣ ክርስቶስን ደስ የሚያሰኘውን ሕይወት መኖር ያቃተኝ፣ እንዲህ እና እንዲያ ስለሆንኩ ነው፣ እንዲህ ባይሆን ኖሮ እንዲህ አይሆንብኝም ነበር.... የሚሉ ልብን የሚያዝሉ ነገሮች ከአፋችን እናወጣለን። የምንናገረው ነገር እውነትነት ሊኖረውም ላይኖረውም ይችላል።


ሰይጣንም ይችን የኛን ደካማ ተፈጥሮ እንደ መልካም አጋጣሚ እየተጠቀመ፣ እስረኞች አድርጎን ሊኖር ይፈልጋል። ሞኙን ይፈልግ!!!!!


ዛሬ ሰይጣንን ከነ ሰበባ ሰበቡ ቻው ቻው እንለዋለን። አእምሮን ሁሉ ከአሁን ሰዓት ጀምሮ ለክርስቶስ እንማርካለን።
እኔ የኢየሱስን ምልክት በሥጋዬ ተሸክሜአለሁና፣ ከእንግዲህ ወዲህ ማንም አያስቸግረኝ። ገላትያ 6፡17 እናንተስ ወገኖቼ?


---------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 31 ቀን ቀርቶታል

አትገረም!!!!!!!!

ዲቮሽን 334/07፥ ሰኞ፥ ነሐሴ 4/07 ዓ/ም 
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)


አትገረም!!!!!!!!

ዳግመኛ መወለድ አለባችሁ ስላልሁህ አትገረም። ዮሐ 3፡7

ሰዎች ከከባድ አደጋ ሲተርፉ፣ ወይም ከጦርነት ልጆቻቸው ተርፈው ሲመለሱ፣ ከአስደንጋጭ ሁኔታዎች ሲያመልጡ ወ.ዘ.ተ ..... “ዛሬ ዳግም እንደ ተወለድኩ እቆጥረዋለሁ” ይላሉ።

መቼም ብዙው ሰው እኮ፣ ዳግም በምድር ላይ እንደ ህጻን የመኖር እድል ቢሰጠው፣ የኖረው ህይወቱን መድገም የሚፈልግ ሰው ኢምንት ነው። አብዛኞቻን ብዙ ስህተቶቻንን አስተካክለን፣ መኖር ነው የምፈልገው። ከህይወት ምእራፎቻችን ልናስታውሳቸው የማንፈልጋቸው ክፍሎች ስላሉን፣ ያንን እያጠፋን መልካሙን ብቻ እያዳበረን መቀጠል እንፈልጋለን።

ታዲያ ሰዎች ዳግም እንደማይወለዱ እያወቁ፣ ለምን “ዛሬ ዳግም እንደ ተወለድኩ እቆጥረዋለሁ” ይላሉ?
መልሱ ምንም ሰምና ወርቅ የለውም፣ ምንም ዓይነት ቅኔም የለውም። ነፍሳቸው የዳግም መወለድን ጥቅም ስለምታወቀው ያንን እየመሰከረችላቸው ነው።

ምናልባት ዛሬስ በቤተክርስትያናችን ውስጥ፣ ዳግም ያልተወለድን ሰዎች እንኖር ይሆን? ኢየሱስስ ለኒቆዲሞስ፣ “ዳግመኛ መወለድ አለባችሁ ስላልሁህ አትገረም” የሚለው ምን ማለት ፈልጎ ነው?
መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን። ኤፌ 2:10

---------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 32 ቀን ቀርቶታል