Thursday, May 21, 2015

የጴንጤ ፖለቲካ = ፊሊያ + ኮይኖኒያ !



ዲቮሽን 253/07 ሐሙስ፣ ግንቦት 13/07
(
በፓ/ ተስፋሁን ሐጢያ)


የጴንጤ ፖለቲካ = ፊሊያ + ኮይኖኒያ !

ስለፖለቲካ ያለን መረዳት የተለያየ ሊሆን ይችላል፡፡ እኔ ወንጌል ሰባኪ እንጂ የፖለቲካ ሰውም አይደለሁም፡፡ ስለሆነም፣ በዚህ ነጥብ ላይ መከራከር አልፈልግም፡፡ ነገር ግን በግሪኮቹ ፈላስፎች በፕሌቶም ሆነ አርስቶትል ትርጉሞች፣ እንዲሁም በዛሬውም ዘመን በመላው ዓለም እየተሠራበት ያለውን ስለ ‹‹ፖለቲካ›› የተሰጠው ቀላልና ግልጽ ትርጉም፣ ‹‹መልካም ኑሮ›› ማለት መሆኑን እረዳለሁ፡፡ ይህ ‹‹መልካም ኑሮ›› መገለጫው ደግሞ በሰዎች መካከል ያለ የእርስ በርስ ወዳጅነት (ፊሊያ) ሲሆን፣ የወዳጅነት መለኪያው ደግሞ በሰላምና በመቻቻል አብሮ መኖር (ኮይኖኒያ) ነው፡፡

ወገኖች ሆይ፣ የአንድ ሀገር ፖለቲካ ‹‹መልካምነቱ›› ወይም ‹‹ኢ-መልካምነቱ›› የሚፈተሸው የምንወድደው ፓርቲ ስለሆነና ስላልሆነ ሳይሆን፣ በአንድ ሀገር ዜጎች መካከል እኩልነትና ወዳጅነት እንዲሁም በሰላምና በመቻቻል አብሮ ለመኖር በሚያደርገው ጥረት ይመስለኛል፡፡ በቤተክርስቲያን ውስጥም ጉሮሮአችን እስኪሰነጠቅ በየጊዜው እየጮኽን የምንሰብከው እውነት ቃል በቃል ማለት ይቻላል ይኸው ነው!

ወገኖች ሆይ፣ በሰዎች መካከል የወዳጅነት መንፈስ ከጠፋ በሀገሪቱ ውስጥ ጤናማ ፖለቲካ ሊኖር አይችልም፡፡ ጤናማ ፖለቲካ በሌለበት ሀገር ደግሞ ‹‹መልካም ኑሮ›› ማየት ዘበት ይሆናል፡፡ በቤተከርስቲያን ውስጥ ያለውም ይኸው ነው! በሰዎች መካከል የወዳጅነት መንፈስ ከጠፋ ቤተክርስቲያንም አብራ ትፈርሳለች፡፡ ይህ ሲሆን ደግሞ አይተናል፡፡

ወዳጆቼ ሆይ፣ ይህን አስተሳሰቤን ላለመቀበል ‹‹ቤተክርስቲያንን የገሀነም ደጆች አይችሏትም›› ተብሎ ተጽፏልና ቤተክርስቲያን አትፈርስም በማለት አትከራከሩኝ፡፡ በአውሮፓ ሀገሮች ለምዕተ ዓመታት ገናና የነበሩ በርካታ የፈራረሱ ቤተክርስቲያኖችን በሥጋ ዓይኖቼ ተመልክቻለሁና ሌላ ምስክር አልሻም!

ወገኖች ሆይ፣ በመጀመሪያዎቹ ምዕተ ዓመታት በሰሜን አፍሪካና በእስያ በርካታ አብያተክርስቲያናት ነበሩ፡፡ እነዚያ አብያተክርስቲያናት ዛሬ መታሰቢያቸውም ደብዛቸውም ጠፍቷል፡፡ ለዚህም ብዙ ምክንያቶች መጥቀስ ቢቻልም ሁለቱን ብቻ መጥቀስ ይበቃል፡፡ አንደኛው፣ በቤተክርስቲያን ምዕመናን መካከል በልዩ ልዩ አስተምህሮች ምክንያት አለመግባባትና አንዱ ሌላውን ማሳደድ ሲሆን፣ ሁለተኛው፣ የእስልምና እምነት መስፋፋትና ክርስትና እምነትን ከምድር ገጽ የማጥፋት ዋነኛ ተልዕኮ ነው፡፡

ወገኖች ሆይ፣ በብዙዎች ዘንድ ‹‹የክርስትና እምነት በስደት ውስጥ ይጠነክራል›› የሚለው አስተሳሰብ ሥር የሰደደ ነው፡፡ ይህን አስተሳሰብ መቃወም አልፈልግም፡፡ ነገር ግን፣ የክርስትና እምነት እንቅስቃሴ ሰላማዊና የተረጋጋ ፖለቲካዊ አስተዳደር ቢያገኝ የተሻለ ለመስፋፋት ዕድል የማግኘቱ ነገር ደግሞ ክርክር የማያሻው ነው፡፡ ለዚህም ማሳያው እንደ ደቡብና ደቡብ ምዕራብ ያሉ አካባቢዎች ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች ወንጌልን ከዳር እስከዳር ለማድረስ ከ30 ዓመት በላይ አልፈጀም፡፡

በተቃራኒው ደግሞ፣ ወንጌል ወደ ሰሜኑ የአገራችን ክፍል የደረሰው ከአውሮፓውያኑ የተሐድሶ እንቅስቃሴ እኩል በተመሣሣይ ጊዜ ሲሆን፣ ክፍለዘመኑ ሁሉ በየጊዜው ይካሄድ በነበረው ጦርነት ምክንያት በኅብረሰተሰቡ ዘንድ የተረጋጋና ሰላማዊ ለወንጌል ሥራ እንቅስቃሴ ምቹ ምህዳር ሳይፈጠር ቀርቷል፡፡ እንደ ፒተር ሐይሊንግ፣ እነ ሳሙኤል ጉባትና ሌሎቹም በርካታ አውሮፓዊያን የአውሮፓውን የተሐድሶ እንቅስቃሴ እንደወረደ ይዘው ወደ ኢትዮጵያ ለማስተላለፍ ቢመጡም በወቅቱ በነበረው ምህዳር የተነሣ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

ወገኖች ሆይ፣ ዛሬም ቢሆን በኢትዮጵያ ክልሎች ለምሳሌ በአፋር፣ በሶማሌ፣ በአርሲ ባሌና በሰሜኑ አካባቢዎች የወንጌል እንቅስቃሴ ተጠናክሮ ሲሠራ የማይስተዋልበት በጣም ምክንያት ግልጽ ነው፡፡ የተጠናከረ የወንጌል እንቅስቃሴ እንዲኖር የተረጋጋ ሰላምና የፖለቲካ አስተዳደር ያስፈልጋል ብዬ የምከራከርበት ምክንያቱ ይኼ ነው፡፡

ወገኖች ሆይ፣ በእኔ አተያይ፣ ያለፉት የሀገራችን የፖለቲካ ሥርዓቶች፣ አንዱን የኅብረተሰብ ክፍል አለቅጥ ጠቅመው፣ ሌላኛውን የኅብረተሰብ ክፍል ደግሞ አለቅጥ የመጉዳት አካሄድ ነበራቸው፡፡ ይህን እውነታ ለኢትዮጵያዊያን ለማስረዳት የታሪክ ሰነዶችን ማጣቀስ ፌዝ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም እኛ በሀገራችን የነበረውን ሁኔታ ስለምናውቀው አስረጅ አያሻንምና ነው፡፡ ሐሳቤን ለማብራራት ግን ምሣሌ መጥቀስ ይበቃል፡፡

ያለፉት የሀገራችን የፖለቲካ ሥርዓቶች፣ በኢትዮጵያ የነበሩ ብሔር ብሔረሰቦችና ሐይማኖቶች፣ እርስ በእሳቸው እንዲቀባበሉና እንዲከባበሩ ሲደረግ አልነበረም፡፡ አንዱን ተቀብሎ ሌላውን የመግፋት፣ አንዱን የመንግሥት ሌላውን የጫካ አድርጎ የመውሰድ ነገሮ ነበሩ፡፡ ከዚህም የተነሳ በብሔር ብሔረሰቦች መካከል የእርስ በእርስ ጥላቻና አለመቀባበል ነበር፡፡ በሐይማኖት ተቋማት ዘንድም መንግሥታዊ ተቀባይነት ያለው በሌለው ላይ ጡንቻውን ሲያሳርፍ፣ ሲያሳድድና ሲያንገላትታ ነበር፡፡

እንደ ሐይማኖት መሪ፣ ሐሳቤ ተቀባይነት አገኘም አላገኘ እውነታውን በግልጽ ማስቀመጥ ይኖርብኛል፡፡ በሐገራችን የሐይማኖት እኩልነት የተረጋገረጠው፣ የብሔረሰቦች እኩልነት በይፋ የታወጀው በአሁኑ ሥርዓት ነው፡፡ ይህንን እውነት አለመቀበል የሚያመለክተው የአስተሳሰብ ልዩነት መኖሩን ሳይሆን የአስተሳሰብ ችግር መኖሩን ይሆናል፡፡ የአስተሳሰብ ልዩነት ጤናማ ሲሆን፣ የአስተሳሰብ ችግር ግን ጤነኛ አይደለም፡፡

እውቀት እየጨመረ ይሄዳል ብዬ ባምንም፣ ማንም ሰው ስለፖለቲካ ያለው ግንዛቤ ከፖለቲካ ፈጣሪዎቹ ከፕሌቶና አርስቶትል ልቆ መሄድ ችሏል ብዬ ለማመን ይቸግረኛል፡፡ ካለም ይቅረብና እንስማው፡፡ ‹‹ሪፐብሊክ››ን በደንብ ያነበበ ሰው በእውነት ፖለቲካን ከሐይማኖት ለያይቶ ለማስቀመጥ ይቸግረዋል፡፡ የዚህም ምክንያቱ የእውነተኛ ፖለቲካ ዋና ዓላማ በሰዎች መካከል የወዳጅነት፣ የወንድማማችነትና የእኩልነት መብት በማስፈንና ፍትሐዊ ሥርዓቶችን በማስፈን ለሰው ልጆች ሁሉ መልካም ኑሮ እውን ማድረግ ስለሆነ ነው፡፡

ወገኖች ሆይ፣ ይህ  አስተሳሰብ ከመንፈሳዊ አስተምህሮአችን ጋራ በቀጥታ ይያያዛል ብዬ አምናለሁ፡፡ ለዚህም ነው፣ ድምጼን ማሰማት ግዴታ ሲሆንና ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ስንደርስ፣ ዛሬ ብቻም ሳይሆን በተለያዩ ጊዜያት ለፖለቲካ አስተዳደሪዎቹም ሆነ ለአብያተክርስቲያናት መሪዎች መልዕክቴን በድፍረት ከማስተላለፍ የማልቆጠበው!

ከዚህም በፊት ያሰማኋቸውን የወሳኝ ወቅት ድምጾቼን ለማስታወስ ያህል፣ (1ኛ) በምርጫ 97 ወቅት ‹‹አይናማዎች እንዳይገጩን›› በሚል ርዕስ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ፣ (2ኛ) ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሥልጣናቸው ለመልቀቅ መፈለጋቸውን በመገናኛ ብዙሃን ይፋ ባደረጉ ጊዜና በሀገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ ውይይት በሆነ ወቅትም ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትር ሥልጣናቸውን  ቢለቅቁ እንጠቀማለን?›› በሚል ርዕስ በሜታኖያ መጽሔት ላይ፣ ድምጼን አሰምቻለሁ፡፡

መካነኢየሱስ ከኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አብያተክርስቲያናት ኅብረት ለመልቀቅ በተንቀሳቀሰች ጊዜም ‹‹ቄሶቹ መንታ መንገድ ላይ››፣ በሚል ርዕስ በሜታኖያ መጽሔት ላይ፣ የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አብያተክርስቲያናት በነቢያት አገልግሎት ላይ ክርክር በሆነ ጊዜም ሚዛናዊ ያልሆነ አቋም እንዳይወሰድ በተደረጉ ጉባኤዎች ሁሉ ላይ በአካል ተገኝቼ ድምጼን ከማሰማትም አልፎ፣ በዚህ ዲቮሽን መስከረም 11 ቀን 2007 ዓ.ም. ላይም ‹‹ነቢያትን እንውገር፣ አንግደል!›› በሚል ርዕስ ድምጼን አሰምቻለሁ፡፡ ሌሎችም ለወንጌል አገልግሎት በተዘዋወርኩባቸው ክልሎች ሁሉ የተመለከትኳቸውን ነገሮች ልዩ ልዩ ሚዲያዎችን በመጠቀም በጽሁፍና በንግግር ወደ ሕዝብ እንዲደርሱ ከማድረግ ተቆጥቤ አላውቅም፡፡

ወገኖች ሆይ፣ ለእኔ መጋቢነት ማለት በር ዘግቶ መጯጯኽ ብቻ አይደለም፡፡ መጋቢነት የአጥቢያውንና የመላ ሀገሪቱን ሁለንተናዊ ጥቅም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚነኩ ነገሮች ሲያጋጥሙም ሆነ ከማጋጠማቸውም በፊት ድምጹን ማሰማት አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ በተለይም እንደእኔ መንፈሳዊ ጸጋው ነቢይነት የሆነና ጸሐፊ የሆነ መጋቢ፣ የሰው ትችት ፈርቶ አፉን በፕላስተር ቢያስርም የሚሳካለት አይመስለኝም (ደግሞም፣ ራሱን ነቢይ ነኝ አለ ብላችሁ አትውገሩኝ:: አንዳንዶቻችሁ ፓ/ር ሆኖ ፖለቲካ ነክቷልና ፓስተርነቱ ይቅርበት ‹አቶ› ይበቃዋል፣ ያላችሁም እግዜር ይስጥልኝ! እርሱንም አትንፈጉኝ እንጂ ‹አቶ› ለእኔ መቼ አነሰኝ፡፡ ከምንም ከምንም በላይ ‹ወንድም› ብትሉኝ በመካከላችን የተሻለ መቀራረብ እንዲኖር ይረዳናል)፡፡

ከዓመታት በፊት በአንድ የወረዳ ከተማ ውስጥ በተዘጋጀው ኮንፍራንስ ላይ በርካታ የመንግሥት ባለሥልጣናት ተሳትፈው ነበር፡፡ ስለዚህ ግን ምንም ዕውቀት አልነበረኝም፡፡ በስብከት አገልግሎቴ መሀል ላይ የትንቢት ቃል መጣ፡፡ ‹‹በዚህ ከተማ የሚገኙ በሥልጣናቸው በመባለግ ሕዝብን ያስመረሩ ሙሰኞችን ቢሮዎችና ቤቶች በቅርቡ ባዶ አደርጋለሁ›› የሚል፡፡ ይህንን መልዕክት በድፍረት አስተላለፍኩ፡፡ አስደንጋጭ ሁኔታ ነበር፡፡ ግን ጌያ ተናግሯልና፣ ወዲያውም የበላይ የመንግሥት አካል የወረዳውን ባለሥልጣናት ሁሉ በመገምገም በርካቶቹን ከሥልጣናቸው እንዳባረረ ሰምቻለሁ፡፡ ነቢይነት ማለት እንደ ውሻ በበሉበት መጮኽ ሳይሆን እውነትን በድፍረት መናገር ነው!

የ2007 ምርጫ እንዳይረሳ! ሁሉም ክርስቲያኖች በበነቂስ ወጥተው ለሐይማኖት ብዝሃነትና ነጻነት፣ ለሕዝቦች እኩልነትና ወንድማማችነት እንዲሁም ለሰላምና መረጋጋት ቅድሚያ የሚሰጠውን አቅም ያለውን አካል በጸሎት ለይተን በመምረጥ ሕገመንግሥታዊ መብታችንን፣ በተለይም ግራ ጉንጯን ሲመቷት ሌላኛውን ለምታዞረው፣ ሰይፍ ሲያነሱባት፣ ፍቅር ለምትሰጠው፣ ሰያርዷትና ሲሰቅሏት ‹‹የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው›› ለምትለዋና ከሰላምና ፍቅር እንዲሁም ሕጋዊ መስመር ሌላ ምንም አማራጭ የሌላትን ቤተክርስቲያን ለመጠበቅና ለመንከባከብ አቅም ያለውን አካል በጸሎት ለይተን እንምረጥ፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!

የጴንጤዎች ዕድገት - በኢሕአዴግ ዘመነ መንግሥት!

ዲቮሽን 252/07 ረቡዕ፣ ግንቦት 12/07
(በፓ/ ተስፋሁን ሐጢያ)

የጴንጤዎች ዕድገት - በኢሕአዴግ ዘመነ መንግሥት!

ዛሬም የሞኝ ለቅሶዬን ላልቅስ ፍቀዱልኝ - የቤተክርስቲያን ሁለንተናዊ ጥቅም ተቆርቋሪ እንጂ፥ የማንም የፖለቲካ ፓርቲ አባል አይደለሁም፥ የጽሁፌ መልዕክትም የማንንም የእምነት ተቋም የሚወክል አይደለም፡፡

ጴንጤዎች በኢሕአዴግ ዘመነ መንግሥት ያገኘነውን ያህል ጥቅም በየትኛውም የኢትዮጵያ ሥርዐተ ማኅበር አግኝተን አናውቅም! በታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ 1987 . ከወጣው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት፥ የሐይማኖትና የመንግሥት መለያየት (አንቀጽ 11) የሐይማኖት እኩልነት (አንቀጽ 25) የሐይማኖት፥ የእምነትና የአመለካከት ነጻነት (አንቀጽ 27) የሐይማኖት ተቋማት የመደራጀት መብት (አንቀጽ 31) እና ሌሎቹም ለእኛ ከፍተኛ ጥቅም ያላቸው ድንጋጌዎች በግልጽ አስቀምጧል፡፡

እነዚህ ድንጋጌዎች ሳይሸራረፉ ጥቅም ላይ ውለዋል ብለን ባናምንም፥ ነገር ግን ከዚህ በፊት በሀገራችን ይወጡ ከነበሩ "የይስሙላ" ሕገመንግሥቶች ሁሉ ማለት ይቻላል፥ ይህኛው ሕገመንግሥት ለጴንጤዎች ወርቃማ ዕድሎች ማጎናጸፍ የቻለ ሕገመንግሥት ነው!
ይህም ከመሆኑየተነሣ፥ በዝርዝር ለማስቀመጥ የሚበዙ ጥቅሞች አግኝተናል፡፡ ካገኘናቸው ከብዙ ጥቅሞች መካከል ቢያንስ አንዱን ለመጥቀስ ያህል፡- በኢሕአዴግ ዘመነ መንግሥት የታየውን የጴንጤዎቹን ዕድገት መጥቀስ ይበቃል፡፡

እኤአ 1994 እና 2007 የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ መደረጋቸው ይታወቃል፡፡ እኤአ 1994 ቆጠራ ወቅት ከሀገሪቱ የሕዝብ ቁጥር 10.1% የነበረው የጴንጤዎች ቁጥር 2007 ቆጠራ ወቅት ወደ 18.6% ደርሶአል፡፡ ይህ ዕድገት በፐርሰንት ሲሰላ 8.5% ነው፡፡ ይህም ማለት በሀገሪቱ ውስጥ ከሚገኙ ሌሎች ሐይማኖቶች ሁሉ ዕድገት ከስምንት እጥፍ የበለጠ ዕድገት ነው!

ወገኖች ሆይ፥ ጴንጤዎች በከፍተኛ ሁኔታ ማደግ በመቻላቸው ምክንያት እኤአ 1994 የሕዝብ ቆጠራ ወቅት 61.6% በነበረው የሀገሪቱ የክርስትና ተከታዮች የጋራ ቁጥር ላይ 1.2% ዕድገት በመጨመር 2007 ላይ 62.8% እንዲደርስ አስችለዋል፡፡ በዚህም ጴንጤዎች ለሀገሪቱ የክርስትና እምነት ተከታዮች ሁሉ ታሪካዊ ውለታ አድርገዋል፡፡ ከእዚህም በላይ በርካታ ትንታኔዎች መስጠት ይቻል ነበር፡፡ ነገር ግን በዚሁ መተዉ መልካም ነው፡፡

ወገኖች ሆይ፥ ባብዛኛው ጴንጤዎች ስንባል ፖለቲካዊ ገለልተኝነት በእጅጉ የሚያጠቃን የኅብረተሰብ ክፍሎች ነን፡፡ በርካታ ወገኖች የፖለቲካ ነገርን ከዓለማዊነት ጋራ በቀጥታ ያያይዙታል፡፡ የኢትዮጰያ ጴንጤዎች ፖለቲካዊ ፎቢያ(መደንግጽ) አለባቸው! በከፍተኛ የፖለቲካ ማዕረግ ላይ ቢሆኑም፥ ፖለቲከኝነታቸው ለእግዚአብሔር ሕዝብ ከፍተኛ ጥበቃና ከለላ ከመስጠት ያልከለከላቸውን ትንቢተ ዳንኤልን ቢያነብቡም፥ መጽሐፈ አስቴርን ቢያነብቡም፥ መጽሐፈ ነህምያን ቢያነቡም የኢትዮጰያ ጴንጤዎች የፖለቲካ ፎቢያ(መደንግጽ) አለባቸው፡፡

በርግጥ ለዚህ ፖለቲካዊ መደንግጽ ሕዝባችንን ያጋለጡት ባለፉት ዘመናት ሀገሪቱን ያስተዳድሩ የነበሩ የፖለቲካ መሪዎች ናቸው፡፡ አሁንም ቢሆን በወረዳና በክልሎች ቢሮዎች ውስጥ የሚገኙ የግል ጥቅም ፈላጊዎች እኩልነታችንን አምነው ለመቀበልና ለመናገር ይተናነቃቸዋል፡፡ ጴንጤዎች ሰላማዊ ዜጎች መሆናቸው እየታወቀ ማግለልና መድልዎ ይደረግባቸዋል፡፡ ቢሆንም፥ በርካታ ተከታዮቻችን እምነታቸውን ሳይጥሉ፥ ፖለቲካን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ማኅበራዊ ተቋማት ውስጥ ገብተው ሕዝባቸውንና ሀገራቸውን በማገልገል ላይ መሆናቸውን ግን ማወቅ ይገባናል፡፡

እነዚህ ወገኖቻችን በሀገሪቱ እያበረከቱ ያሉት አገልግሎት ተጠናክሮ እንዲቀጥል፥ የጴንጤዎቹ ሰላማዊና ሕገመንግሥታዊ ኑሮ በተረጋጋ ሁኔታ እንዲቀጥል፥ የወንጌል ሥራና ልዩ ልዩ ሰላማዊ የእምነት እንቅስቃሴ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ዕድል ልንሰጥ ይገባል፡፡ አለበለዚያ፥ የሚፈልጉትን ሀይማኖታዊ መንግሥት በኢትዮጵያ ለመመሥረት ያለ እንቅልፍ ሲሰሩ የቆዩ ሀይማኖታዊ ፖለቲከኞች ዕድል ያገኛሉ፡፡

አንዳንዶች፥ የሀገሪቱን ሥልጣን በቁጥጥራቸው ሥር ለማድረግ "ብቻ" እንዲረዳቸው ፖለቲካዊ አጀንዳ አንግበውና ፖለቲካዊ ጭንብል አጥልቀው እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡ የኛ ቸልተኝነት በዚህ መሰል ዓላማ እየተንቀሳቀሱ ላሉ ኃይሎች ማሸነፍና፥ ከድሉም ማግሥት ጀምሮ ወዲያውም ሕገመንግሥቱን የመለወጥ፥ ቀጥሎም ሐይማኖታዊ መንግሥት መመሥረት፥ ወዲያውም ተከትሎ አገሪቱ በሐይማኖታዊ አክራሪዎችና አሸባሪዎች እጅ የመውደቅ አደጋ ሊያጋጥማት ይችላል!

ስለሆነም መጻኢ ዕድላችን ጥያቄ ውስጥ ሳይገባ በዚህ ምርጫ ላይ በበነቂስ ወጥተን ሐይማኖታዊ ነጻነታችንን ቢቻል የበለጠ የሚያቆይልንን፥ ካልተቻለም ባለበት ሊያስከብርን የሚችለውን፥ አቅም ያለውን፥ አካል በጸሎት አስበን እንምረጥ!

በየክፍለ ከተሞቹና በየወረዳዎቹ የሚገኙ የመሬት አስተዳደር ቢሮዎችና ኃላፊዎች በጴንጤዎች ላይ በተለይ ሲያደርሱብን በነበሩ የመልካም አስተዳደር እጦት በደሎች ምክንያት ቂም በመያዝ፥ "አያ በሬ ሆይ፥ ሳሩን አየህና ገደሉን ሳታይ" እንደተባለው፥ እነዚህን በምርጫ ካርድ ለመቅጣት በማሰብ፥ ጊዜያዊ ችግርን ለማስወገድ አስበን ዘላቂ ችግር በራሳችን ላይ እንዳናመጣ፥ ዋናው የክርስትና እምነት እንቅስቃሴያችንና ሕልውናችን ላይ አደጋ እንዳንጋብዝ አደራ እላለሁ!

"በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፥ ነገር ግን አይዟችሁ፥ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁና"(ዮሐ 1633) ያለንን ጌታ በማሰብ፥ የመልካም አስተዳደር እጦት በዚህ ምድር ላይ እስካለን ድረስ ሙሉ በሙሉ ሊወገድ የማይቻል ጉዳይ መሆኑን በማወቅና፥ ለወደፊቱም ሕጋዊ በሆነ መልኩ መብታችንን ለማስከበር የሚያስችል ዕድል መኖሩን በማሰብ የሚሻለንን መምረጥ ይኖርብናል፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!