Saturday, November 22, 2014

መኖርዎም መሞትዎም እንዲጠቅም!

ዲቮሽን ቁ.73/07     ቅዳሜ፣ ሕዳር 13/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)


መኖርዎም መሞትዎም እንዲጠቅም!

አንዳንድ ጊዜ በሕይወት ሞኖርን እመርጣለሁ፡፡ አንዳንዴ ደግሞ እጅግ የሚመረጥ ነውና ሞቼ ከክርስቶስ ጋር አብሮ መሆንን እናፍቃለሁ፡፡ ይሁን እንጂ የማውቀው አንድ ነገር አለ፤ ይህም በሕይወት መኖሬ ለእናንተ ብዙ የሚጠቅም መሆኑን ነው (ፊል 1፡21-24)

ወገኖች ሆይ፣ በዚህች ምድር ላይ እየኖርን ያለነው በዋነኛነት ለራሳችን ጥቅም ከሆነ በሕይወት ከምንኖር ይልቅ ብንሞት የተሻለ ነው! እውነተኛ አማኞች በዚህ ዓለም የሚኖሩት ለራሳቸው ሳይሆን ለእግዚአብሔር ክብር ነው፡፡ የምንኖረው ሌሎች መልካሙን ሥራችንን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችንን እንዲያከብሩ ብርሃናችንን በሰው ፊት እንድናበራ ነው፡፡ የምንኖረው በቃልና በሥራ ስለጌታ በመመስከር፣ ለእግዚአብሔር ክብር ነው!

ታውቃላችሁ፣ ‹‹አማኞች ነን›› ባይ አንዳንድ ሰዎች ነጻነታቸውንና ጊዜያቸውን፣ ገንዘባቸውንና ጉልበታቸውን ሰው እንዲያይባቸው፣ ሰው እንዲነካባቸው አይፈልጉም! ‹‹አማኞች ነን›› ባይ ሌሎችም ‹‹ነጻነታችንን ይጋፋል›› በሚል ትዳር መያዝ አይፈልጉም፡፡ እንዲህ ከሚናገሩ ‹‹አማኞች ነን›› ባይ አንዳንዶች፣ በውስልትና ሕይወት ይመላለሳሉ፡፡

ታውቃላችሁ፣ ‹‹አማኞች ነን›› ባይ አንዳንዶች ደግሞ ትዳር ቢመሠርቱም፣ ነገር ግን ልጅ መውለድ አይፈልጉም፡፡ ልጅ ወልዶ ማሳደግ የሚያስከፍለውን ዋጋ መሸከም አይሹም፡፡ ስለሆነም ልጅ እንዳይረገዝ ይከላከላሉ፡፡ መከላከያውን ጥሶ ጽንስ ከመጣም ውርጃ ይፈጽማሉ!

ታውቃላችሁ፣ አንዳንዶች በቤተክርስቲያን አገልግሎት መሳተፍ አይፈልጉም፡፡ ዕውቀት–ችሎታቸውን፣ ክህሎት–ልምዳቸውን ማካፈል አይሹም፡፡ በልዩ ልዩ አገልግሎቶች መሳተፍ የግል ጊዜያቸውንና ነጻነታቸውን ይጋፋባቸዋል፡፡ ገንዘብ–ሀብታቸውን፣ ንብረት–ጥቅማቸውን ይነካባቸዋል!

ታውቃላችሁ፣ አንዳንዶች መኖሪያ ቤታቸውን ለመንፈሳዊ ፕሮግራም ለመፍቀድ እንኳን ይጨናነቃሉ! በሳምንት አንድ ጊዜ ለአንድና ሁለት ሰዓት ለሚደረግ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መስጠት ይቸገራሉ፡፡ አለ አይደል፣ ከቤታቸው አቧራ ይራገፍባቸዋል፣ ጭቃ ይቀባባቸዋል፣ ሶፋቸው ይጎዳባቸዋል!


ወገኖች ሆይ፣ በዚህች ምድር የምንኖረው ለእግዚአብሔር ክብር ነው! ለእውነተኛ አማኝ በሕይወት መኖር ማለት ክርስቶስን ማልገል ነው! በሕይወት መኖራችን ሰዎችን ከእግዚአብሔር ጋር ለማስታረቅ ነው! የእግዚአብሔር ሰው እንዲህ ዓይነት ሕይወት እንዲኖር ተጠርቷል፡፡

ታውቃላችሁ፣ ለእግዚአብሔር ክብር መኖር ስንጀምር ከመሞት ወይም ከመኖር መምረጥ ያስቸግራል! ይህን ሕይወት መኖር ለሌሎችም፣ ለራስም ይጠቅማል! ለእግዚአብሔር ክብር ስንኖር፣ በሕይወት መኖራችን ከራሳችን ይልቅ ለሌሎች ይጠቅማል!

ታውቃላችሁ፣ ብዙ ሰዎች ለእግዚአብሔር ክብር ስለማይኖሩ፣ በሕይወት መኖራቸው ሳይሆን መሞታቸው ይጠቅማል! ታውቃላችሁ፣ አንዳንዶች እንዲያውም ኖረውም ሞተውም አይጠቅሙም!

ወዳጄ ሆይ፣ በሕይወት ሲኖሩ ለሌሎች ጠቃሚ እንዲሆኑ ይፈልጋሉ? እንግዲያውስ ኑሮዎትን ለእግዚአብሔር ክብር ይኑሩ! በቃልና በሥራ ለእግዚአብሔር ክብር መኖር ይጀምሩ!

--------------------------------

(ከመስከረም 1/2007 ጀምሮ ዕለታዊ ዲቮሽን ፖስት በማድረግ ላይ ነኝ፡፡ ሁሉም ወዳጆቼ ትምህርቱ ጠቃሚ ሆኖ ካገኙት፣ ላይክና ሼር እንዲያደርጉ፣ ወዳጅ ጓደኞቻቸውም መጠቀም እንዲችሉ እንዲያግዙ በአክብሮት እጠይቃለሁ፡፡ ይህ ዲቮሽን የመማማሪያ መድረካችን እንዲሆን ፍላጎት አለኝ፡፡ ስለሆነም፣ ያልተብራራ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥያቄ፣ ወይም ማግኘት የምትፈልጉት መንፈሳዊ ምክር ካለ አቅርቡ፣ ጌታ እንደረዳኝ ለመመለስ እሞክራለሁ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!)