Tuesday, August 25, 2015

በምድረበዳችን አፈራን!!!!!!

ዲቮሽን 349/07፥ ማክሰኞ፥ ነሐሴ 18/07 ዓ/ም 
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)

በምድረበዳችን አፈራን!!!!!!

እግዚአብሔር በመከራዬ አገር አፈራኝ። ዘፍ 41፡52

እንግዲህ እግዚአብሔር የኃይሉ ልክ ከሰው ዓእምሮ በላይ መሆኑን ሊያሳየን ተንቀሳቅሷል። እኛ አንዳንዴ እግዚአብሔርን ለሰው እንዳደረገው እንዲያደርግ ስለምንፈልግ የምንጠብቀውም ያንኑ ነው። እሱ ግን ምንም እንኳን ዓላማው አንድ ቢሆንም፣ እሱም እኛን ማዳን ሲሆን፤ አሰራሩ በራሱ ምርጫ ላይ ላይ የተመሠረተ ነው።
መከራችንን እግዚአብሔር አስረስቶ ዝም አላለም። አያልቅበት የእኛ ጌታ! ደግሞ አበዛን። ፍሬ አፈራን። ጠላታችን ሊገለን፣ሊያሳብደን፣ እስረኞችና ባሪያዎች አድርጎ ሊያስቀረን ነበር ወደ ምድረ በዳ የወሰደን። ከሰው ከዘመድ ነጥሎ፣ ከአማኞች ከወገናችን ሁሉ ነጣጥሎ፣ ጓደኞቻችንን ሁሉ ከእኛ አርቆ፣ አንድ ቀን በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ገብተን ራሳችንን እንድንጠላ ከዚያም ራሳችንን እንድናጠፋ ነበር ዓላማው። በዘላለም ፍቅር እንደተወደድን ያላወቀ ጅል!!!!!!
እኛ እኮ በዘላለም ፍቅር ተ-ወ-ደ-ና-ል። ገና ሳንወልድ፣ ገና ሳንጸነስ፣ ፍሬያማ እንድንሆን ተጠርተናል። ስለዚህ ኢየሱስ ሁሉንም ለበጎ አደረገልን። አሁንስ ጠፍተው ይሆናል እያሉ ሰዎች ሁሉ ሲጠብቁን ጭራሽ ተገኘን፣ ደርቀው ቀርተዋል እያሉ ሲያሟርቱብን እኛ ግን ለምልመን አረፍነው። አይገርምም ወገኖቼ?
በምድረበዳ ላይ ማፍራት የሚቻለው ከኢየሱስ ደም የተነሳ ብቻ ነው። እና በመከራችን አገር አፈራን። ኤፍሬም ሆነልን። እንግዲህ ክብር ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ እንሰጣለን እንጅ ሌላ ምን እንላለን!!!! አንድ ነጠላ ነበርን፣ ግን አልፈን ተርፈን አገር ሆንን! ዳርቻችን ሰፋ!
ሕዝብን አበዛህ፣ አቤቱ ሕዝብን አበዛህ፣ አንተም ተከበርህ፣ የአገሪቱንም ዳርቻ ሁሉ አሰፋህ። ኢሳ 26፡15
---------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 17 ቀን ቀርቶታል

ምናሴ ሆነልን!!!!!!

ዲቮሽን 348/07፥ ሰኞ፥ ነሐሴ 18/07 ዓ/ም 
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)

ምናሴ ሆነልን!!!!!!

እግዚአብሔር መከራዬንና የአባቴን ቤት አስረሳኝ። ዘፍ 41፡50
ያ ሁሉ ለቅሶ ያ ሁሉ የማይታለፍ የሚመስለው የመከራ መንገዳችን አለፈ። በየመንገዱ በየአደባባዩ ስናለቅስ በየቤተክርስትያኑ ስናለቅስ፣ በየጓደኞቻችን ስናለቅስ፣ የጌታ የማዳን ክንድ ወዴት ነው እያልን እንባችን እንደ ጎርፍ ሲፈስ .... በቃ ጌታ በቃ ሲለው ሃዘናችን አበቃ። ረሳነው። እግዚአብሔር አስረሳን።
የሚያድነን እና የሚታደገን ማነው? ወዴት ቤተክርስትያንስ ይኬዳል? እውነት የእግዚአብሔር ቃል ይሠራል ወይ እያልን የተንከራተትንበት ያ ጊዜ አለፈ። አሁን እኮ አንዳንዶቻችን የመከራችንን ዓይነት እንኳን በቅጡ አናስታውሰውም። ምናሴ ሆነልን።
አሁን ዮሴፍ ወንድሞቹ ሊገድሉት ሲማከሩ፣ ከዚያም ሲሸጡት፣ ከዚያም የጲጥፋራ አሽከር ሲሆን፣ ከዚያም ሲሾም፣ ከዚያም እሥር ቤት ሲወርድ፣ በእስር ቤት ላገኘው የመጠጥ አሳላፊ፣ ከዚህ እስር ቤት አስወጣኝ እያለ ሲማጸን፣ ሰውዬውም ሲረሳው፣ ...... አ..ቤ....ት... ስንት የጨለማ ጊዜ እኮ አለፈ!!!
እውነት በዚያን ጊዜ ዮሴፍ ስለራሱ ምን ይሰማው ይሆን? ያው ጠዋትና ማታ በሰው አገር ታሥሮ እንባውን ቁርስ ምሳና እራት አድርጎ፣ በትካዜ በጨለማ ቤት ሲቀመጥ... በግብጽ ምድር ላይ ኃላፊ፣ የንጉሥ አማች፣ የትውልዱ ተስፋ ይሆናል ብሎ ማን አመነ!!! ግን ይገርማል! ሆነ። በቃ ሆነ። ምክንያቱም መከራው የበዛበት እኮ ባለ ራእይ ስለነበረ ነው።
እና ዛሬ ምናሴ ሆነልን። መከራችንን እግዚአብሔር አስረሳን። ታዲያ ደስ አይልም-ወገኖቼ!!!!
የጻድቃን መከራቸው ብዙ ነው፣ እግዚአብሔር ግን ከሁሉ ያድናቸዋል። መዝ 34፡19
---------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 18 ቀን ቀርቶታል

ተሻገርን!!!

ዲቮሽን 347/07፥ እሁድ፥ ነሐሴ 17/07 ዓ/ም 
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)

ተሻገርን!!!

እነዚህማ በዚያ ስፍራ አይገኙም፤ የዳኑት ብቻ ይሄዳሉ። ኢሳ 35፡5
አይ ጠላት!!! የሞተ መሆኑን ራሱ በራሱ ጊዜ ማስመስከር ፈለገና፣ በሰረገላና በፈረስ ሆኖ ሊያሳድደን ጀመረ አይደል? እኛ፣ በጌታ መንፈስና እና ኃይል እንደምንንቀሳቀስ አላወቀ! የትኛው ቴክኖሎጂ እና ጥበብ ነው፣ ውሃን እንደ ግድግዳ ያቆመ! የትኛው አስማተኛና ጠንቋይ ነው ተከታዮቹን በውሃ ውስጥ ያስኬደው! የትኛው የሉሲፈር ጥበብ ነው በእሳት ውስጥ ጭፍሮቹ ሲያልፉ የታደጋቸው!
እኛማ ድነናል! ጠላት ይስማ! ድ-ነ-ና-ል!!! ኢየሱስ በመስቀል ላይ ኃጢያታችንን በደላችንን መከራችንን ሁሉ ተ-ፈ-ጸ-መ ብሎ አዲስ ሰው አድርጎናል።
ስለዚህ በውሃ ውስጥ እንሄዳለን፣ አንሰጥምም!! በእሳት ውስጥ እናልፋለን አንቃጠልም፣ ነበልባሉም አይፈጀንም!!!!
ለእኛ የተከፈተ መንገድ ለእኛ ብቻ ነው። ጠላትን አይመለከተውም።
አይ ጠላት ሞኙ፣ ደሞ ብሎ ብሎ አባታችን ለእኛ በከፈተው መንገድ ሊሄድ ያምረዋል? ምን ያለው ትእቢተኛ እና ክፉ ነው! ምንስ ያህል አመፀኛ ነው! ለነገሩ አንዴ ለጥፋት ስለተጻፈ፣ መከታተሉ አይቀርም። ምክንያቱም እግዚአብሔር የጠላታችን መታሰቢያው እስከማይገኝ ድረስ ነውና ድምጥማጡን ማጥፋት የሚፈልገው፣ ስለዚህም ዝም ይለዋል።
ዲያብሎስ ከነጭፍሮቹ ሰጠመ፣ እኛ ግን በደረቅ ተሻገርን። የፈርዖን ፈረሶች፣ ሰረገሎችና፣ ፈረሰኞች ተሰብስበው ሰጠሙ፣ እኛን ግን አምላካችን ውሃውን ግራና ቀኝ እንደግድግዳ አድርጎልን በደረቅ ባሕሩን ተሻገርን።
ዐይን ያላየውን፣ ጆሮ ያልሰማውን፣ የሰውም ልብ ያላሰበውን እግዚአብሔር ለሚወዱት አዘጋጅቷል። 1ቆሮ 2፡9
---------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 19 ቀን ቀርቶታል