Tuesday, July 28, 2015

አትምረጡ!!!!!

ዲቮሽን 321/07፥ ማክሰኞ፥ ሐምሌ 21/07 ዓ/ም
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)


አትምረጡ!!!!!

የምታመልኩትን ዛሬ ምረጡ። እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን። ኢያሱ 24፡ 15

ኢያሱ የእሥራኤላውያን ነገር አንዴ ያዝ አንዴ ለቀቅ ያለ ዘይቤ ቢይዝበት ደከመውና፣ ምክሩን ሁሉ ሲፈልጉ ሲቀበሉ፣ ሳይፈልጉ ሲጥሉ፣ ሞቅ ያላቸው እንደሆነ ጣዓት ሲያመልኩ፣ መከራ ሲደርስባቸው ወደ እግዚአብሔር ሲመለሱ፣ እንዲያው ታከተውና፣ ራሴን ባድንስ፣ ሲፈልጉ እግዚአብሔርን ያምልኩ፣ ካለፈለጉ ይተውት በማለት ይመስለኛል፣ “የምታመልኩትን ዛሬ ምረጡ። እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን።” ኢያሱ 24፡ 15 በማለት እግዚአብሔርን የማምለክን ጉዳይ ምርጫ ውስጥ ያስገባላቸው።

ዛሬ ግን እኔ እንዲህ እላችኋለሁ! ግዴላችሁም አትምረጡ!!! በሞትና በሕይወት መካከል ሰፊ ልዩነት አለና ለማን ይድላው ብላችሁ ነው፣ ሞትን የምትመርጡት? በሲኦልና በመንግስተ ሰማያት መካከል ከቃላት በላይ የሆነ ልዩነት አለና፣ ለማን ይመቸው ብላችሁ ነው ሲኦልን የምትመርጡት?

ዘመኑ የምርጫ ነው። ሰፊ አማራጭ አለን። ብንፈልግ ኢየሱስን እንደ ሞራል አስተማሪ ልንቀበለው እንችላለን፣ ብንፈልግ እንደ አሪፍ መሪ ልንቀበለው እንችላለን፣ እንደ ትልቅ ምሁርም ልናየው እንችላለን፣ በየወቅቱ ከተነሱት ፈላስፎችም እንደ አንዱ ማየትም መብታችን ነው። ግን ይህ ሁሉ ከሞት አያድነንም። ከሞት የሚያድነው፣ ኢየሱስን እንደ እግዚአብሔር ልጅ መቀበል ብቻ ነው።

ስለዚህ ግዴላችሁም፣ ኢየሱስን ከስነልቦና ምሁራን ጋር አታወዳድሩት፣ ከፈላስፎችም ጋር አታነጻጽሩት። እንዲህ ያለው እውቀታችን የትም አያደርሰንም፣ ከዘላለም ሞት በቀርም የሚያመጣልን ምንም ነገር የለም። ለዚህም ነው ጳውሎስ፣ “በውሸት እውቀት ከተባለ ለዓለም ከሚመች ከከንቱ መለፍለፍና መከራከር እየራቅህ የተሰጠህን አደራ ጠብቅ፣ ይህ እውቀት አለን ብለው አንዳንዶች ስለእምነት ስተዋልና ያለው።” 2 ጢሞ 6፡20።

ኢየሱስ ያድናል!!!!!

አባትዬ፣ እንዲህ እንድናገር ድፍረቱንም ዓቅሙንም ስሰጠህኝ አመሰግንሃለሁ። የምድረበዳየ ኢየሱስ ሆይ፣ እወድሃለሁ። ወንዶች እና ሴቶች ልጆችህ ሁሉ አንተን በማወቅ እንዲሞሉ አሁን መንፈስህን አፍስስባቸው። ሰምተህኛልና ተባረክኝ።

--------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 45 ቀን ቀርቶታል

እንጮሃለን፣ እንድናለን!!!!!!

ዲቮሽን 320/07፥ ሰኞ፥ ሐምሌ 20/07 ዓ/ም
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)


እንጮሃለን፣ እንድናለን!!!!!!

በተጨነቁ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እርሱም ከመከራቸው አዳናቸው። መዝ 107፡ 28

ያው አሥራ አንደኛው ሰዓት ላይ ስለሆንን፣ የጠላታችንን ውድቀት ልናይ፣ እኛ ደግሞ እግዚአብሔርን ወዳሰበልን ልንገባ የተቃረብንበት ጊዜም ስለሆነ ያለን ብቸኛ አማራጭ በሰልፉ ልክ፣ በመከራችን ልክ፣ ወደ እግዚአብሔር መጮህ ነው።
ዙሩ ከርሯል ወገኖቼ!!!!!!!!

አንዳንዶቻን፣ ጭው ባለ በረሐ እየተቅበዘበዝን፣ የእግዚአብሔርን ክብር እየተራብን፣ እየተጠማን፣ ወደ ሰማይ እየጮህን ያለን ሰዎች አለን አይደል? እርሱ የተጠማችውን ነፍስ ያረካልና፣ የተራበችውንም ነፍስ ከበጎ ነገር ያጠግባልና፣ ወደ እግዚአብሔር እንጮሃለን!!!!!!

አንዳንዶቻን፣ በብረት ሰንሰለት የታሰርን ፣ መውጫ መፈናፈኛ ያጣን፣ በጭለማ በጥልማሞት የተቀመጥን፣ የሚደግፈን፣ የሚያነሳን ያጣን፣ ከጉድጓድ ማን ያወጣናል የምንል፣ ከወህኒ ማን ይፈታናል የምንል፣ ወደ ሰማይ እየጮህን ያለን ሰዎች አለን አይደል? እርሱ የናሱን በሮች ይሰብራልና፣ የብረቱንም መቆርቆሪያ ይቆርጣልና፣ ወደ እግዚአብሔር እንጮሃለን!!!!!!

አንዳንዶች ደግሞ፣ ከበደላችን የተነሳ ችግር ውስጥ የገባን፣ ሰውነታችን የምግብ አይነት የተጸየፈች፣ ወደ ሞትም ደጃፍ የቀረብን አለን አይደል? ቃሉን ልኮ ይፈውሰናል፣ ከመቃብርም አፋፍ ይመልሰናልና፣ ወደ እግዚአብሔር እንጮሃለን!!!!!!

አንዳንዶቻችን ደግሞ፣ ከነፋሱና ከማዕበሉ የተነሳ ሐሞታችን የፈሰሰ፣ እንደ ሰከረ ሰውም የምንንገዳገድ፣ መላው ጠፍቶብን የምናደርገውን ያጣን አለን አይደል? እርሱ ዐውሎ ነፋሱን ጸጥ ያደርጋል፣ የባሕሩንም ሞገድ ረጭ ያደርጋል፣ ወዳሰብነውም ወደብ እንደርሳለንና፣ ወደ እግዚአብሔር እንጮሃለን!!!!!!

አባት ሆይ፣ እጆቻችንንም ሰልፍ፣ ጣቶቻችንንም ዘመቻ ስላስተማርክልን፣ ወደ ምልጃ ጸሎትም፣ ወደ ጩኸትም ስላስገባህን ተባረክ። ሁሉ ለስምህ ክብር ይሁን፣ ሰምተህኛልና ተባረክ። አሜን!!!!!!

--------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 46 ቀን ቀርቶታል

እለምንሃለሁ!!!!!!

ዲቮሽን 319/07፥ እሁድ፥ ሐምሌ 19/07 ዓ/ም
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)



እለምንሃለሁ!!!!!!

ከእኔ ትለይ ዘንድ እለምንሃለሁ። ዘፍጥረት 13፡9

እንኳን በሰው ሃገር ቀርቶ በትውልድ ሃገራችንም የስጋ ዘመዶቻችንን እንፈልጋለን። አጠገባችን እንዲሆኑ፣ ደስታንም ሆነ ሃዘንን አብረውን እንዲካፈሉን እንሻለን። አብርሃም ግን ሲፈራ ሲቸር ፣ አንድ ቀን ጨከነና፣ ይህንን የማያዛልቅ፣የትም የማያደርስ ዝምድና ሊለየው ፈለገ። ሒድ ብሎ ሎጥን ሊያባርረው አልቻለምና፣ “ከእኔ ትለይ ዘንድ እለምንሃለሁ”። ዘፍጥረት 13፡9 ብሎ ይለማመጠዋል።

እንዲያው ዛሬስ በኛ ዘመን እንደ ሎጥ የሆኑብን ጨክነን ልናርቃቸው ያልቻልናቸው አመሎች ይኖሩብን ይሆን? እግዚአብሔርን እያመለክን ግን ደግሞ ብዙ ጸያፍ የሆኑ ነገሮች፣ አስተሳሰቦች አብረውን ተጣብቀው ይኖሩብን ይሆን?


ለምሳሌ፣ ጫት መቃም እየወደድን፣ መጠጣት እየወደድን፣ ማመንዘር እየወደድን፣ መዋሸት እየወደድን፣ መዝፈን እየወደድን፣ ማማት እየወደድን ..... በአንጻሩ ደግሞ እግዚአብሔርን ማምለክ እንፈልግ ይሆን? እንዲያው ምናልባት እንዲህ ያለ አጣብቂኝ ውስጥ ያለን ሰዎች እንኖር ይሆን? የምንወዳቸው ክፉ ልምምዶቻችን የእግዚአብሔርን ክብር እንዳናይ ከልክለውንስ ቢሆን? መቼም ለእግዚአብሔር የሚያቅተው ነገር የለምና፣ ለምን ተስማምተን አንጸልይም?

አባት እግዚአብሔር ሆይ፣ በሕይወታችን ላይ ተጣብቀው ያሉ የተለያዩ የምንወዳቸውን ሐጢያቶች እባክህ እንድንጠላቸው እርዳን? ካለነሱ መኖር የሚያቅተን የሚመስለንን፣ ለስጋችን የሚመቹንን ክፋቶች፣ ወዳጄ ሆይ አንተ ቻልና እባክህ ከእኛ አርቃቸው? እንድንጠላቸው አድርገን? የሚጣፍጡንን ሐጢያቶቻችንን፣ እንደ ማር ወለላ የሆኑብንን ከንቱ ልማዶቻችንን እባክህ አንተ በስልጣንህ ከእኛ አርቃቸው? እጠበኝ ከበረዶም ይልቅ ነጭ እሆናለሁ እንዳለ ዳዊት (መዝ 51፡7)፣ ወዳጄ ሆይ፣ ሥጋችንን ባይፈቅድ እንኳን እንደ ሕጻን ልጅ ገርፈህ ዛሬ እጠበን። አባብየ፣ ታደርገዋለህና ተባረክ።

--------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 47 ቀን ቀርቶታል፡፡

እንደ መንጋ!!!!

ዲቮሽን 318/07፥ ቅዳሜ፥ ሐምሌ 18/07 ዓ/ም
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)


እንደ መንጋ!!!!

ዮሴፍን እንደ መንጋ የምትመራ!!!!! መዝ 80፡ 1

ያ በልጅነቱ እናቱን በማጣት የተጎዳው ዮሴፍ፣ በወንድሞቹ ዘንድ ደግሞ የመግደል ሙከራ ተደርጎበታል። እሱንም ሲያልፍ ደግሞ የቀረበለትን የዝሙት ፈተና እምቢ በማለቱ፣ በእስር ቤት ማቅቋል። ብቻ ታሪኩን ብታጠኑት ከልጅነቱ ጀምሮ በስጋ ዘመዶቹም ሆነ በባእድ ሰዎች ዘንድ ብዙ ሸክምን የተቀበለ ሰው ነው-ዮሴፍ። ቢሆንም አልሞተም፣ አልፎ ተርፎም፣ እግዚአብሔርን ያየለትን ነገር ሁሉ አንድም ሳይቀር አየ። ለብዙ ክፉ ነገር ታጭቶ የነበረው ዮሴፍ፣ በመዝ 80፡ 1 ላይ ዮሴፍን እንደ መንጋ የምትመራ ሆይ ተብሎ፣ በዝቶ ተባዝቶ እናየዋን።

እንግዲህ እናንተ እግዚአብሔር የምትፈሩ ሆይ፣ በከባድ መንገድ እያለፋችሁ ይሆን? በቤተሰብም፣ በሥራ ቦታችሁም፣ በመንደርም፣ በስደትም ያላችሁ፣ በመከራ እያለፋችሁ ይሆን? ምናልባት በወህኒ ቤት፣ ወይም በሆስፒታል ያላችሁ ትኖሩ ይሆን? ወይም ደግሞ ሁሉም ሰው ተስፋ ቆርጦባችሁ ይሆን?

ታዲያ ለምን ተስማምተን አንጸልይም፣ እንዲህ በማለት፣

እግዚአብሔር ሆይ፣ ዳዊት (143) ሲናገር ህያው ሁሉ በፊትህ ጻድቅ አይደለምና ከባርያህ ጋር ወደፍርድ አትግባ እንዳለ፣ ከዚህ ከደካማ ሥጋችን የተነሳ ሥፍር ቁጥር የሌለበት ሐጢያት ውስጥ እየገባን ልብህን ባሳዘንንበት ነገር ሁሉ፣ ኤልሻዳዩ ሆይ፣ በእንባ እለምንሀለሁ፣ አሁን ይቅር በለን። ጠላት ላልተገባ ነገር እና ባልተገባ ቦታ እንደ ዮሴፍ ሸጦን ቢሆን እንኳን፣ እባክህ ዛሬ አንተ በኢየሱስ ደም መልሰህ ግዛን። ከወህኒም አውጣን። ከዚያም ወደ አየህልን ነገር አንድም ሳይቀር አስገባን፣ እንደ መንጋም አድርገን። ወዳጄ ሆይ፣ ሰምተህኛልና ተባረክ።
--------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 48 ቀን ቀርቶታል፡፡

ካላየሁ አላምንም!!!!!

ዲቮሽን 317/07፥ አርብ፥ ሐምሌ 17/07 ዓ/ም
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)


ካላየሁ አላምንም!!!!!


የችንካሩን ምልክት በእጆቹ ካላየሁ..... እጄንም በጎኑ ካላገባሁ አላምንም አላቸው። ዮሐንስ 20፡ 25


እንግዲህ ክርስትና የመጠማት፣ የመፈለግ፣ እና ከኢየሱስ ጋር የሚኖረን የግል ልምምድ ነው። አንዱ ጋር የሚኖር ልምምድ ሌላው ዘንድ ላይኖር ይችላል። ኢየሱስ የግል አዳኛችን ነው። በግላችን እሱን እንፈልጋለን፣ በደረስንበት እንመላለሳለን። መቼም እመን/ እመኚ ስለተባልን ማመን አንችልም። መሆን የምንችለው ራሳችንን ነው።


ስለዚህ ዛሬ በጌታ ፊት በፍጹም ቅንነትና እውነተኛነት ብንቀርበስ? ቶማስ ያደረገው እንደዚህ ነው። ተጠራጣሪ ልብ እያለው ራሱን አማኝ አስመስሎ በጌታ ፊት አልተመጻደቀም፤ በወንድሞቹም መካከል አልዋሸም። ይልቅስ በይፋ በግልጽ “የችንካሩን ምልክት በእጆቹ ካላየሁ፣ ጣቴንም በችንካሩ ምልክት ካላስገባሁ፣ እጄንም በጎኑ ካላገባሁ አላምንም አላቸው። ዮሐንስ 20፡ 25። የልቡን ቅንነት ያየው ኢየሱስም አላሰፈረውም። የቶማስንም የልብ ጭንቅ እና ጥርጣሬ መፍትሔ አበጀለት።


እንግዲህ ምናልባት እንዲህ ያለ ሁኔታ ውስጥ ካላችሁ ለምን ተስማምተን አንጸልይም፣ ኢየሱስ ሆይ ከስጋ ድካማችን የተነሳ፣ ከዘገየ ተስፋችንም የተነሳ፣ በጥርጣሬ ውስጥ ላለን ሁሉ እባክህ ዛሬ ተገለጥ። እባክህ ወዳጄ ሆይ፣ እኛም በዓይኖቻችን እንይህ፣ በእጆቻችንም እንዳስህ፣ እንደ ቶማስም ጌታየ አምላኬ እንበልህ። ዘመዴ ሆይ ተባረክ።


--------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 49 ቀን ቀርቶታል፡፡