Saturday, October 4, 2014

ዘመን ሲሸሽ – ዘመን ሲመጣ!


ዲቮሽን .21/2007 ረቡዕ፣ መስከረም 21/2007 ..
(
በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ


ዘመን ሲሸሽዘመን ሲመጣ!


እንግዲህ እንደ ጥበበኞች እንጂ ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንዴት እንድትመላለሱ በጥንቃቄ ተጠበቁ፤ ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ (ኤፌ 515-16)

በደቡቡ የአገራችን ክፍል በሲዳማ ዞን ‹‹ጊጊሾ›› እና ‹‹ኮኬ›› የሚባሉ ሁለት ተመሳሳይ ዝርያ ኖሯቸው፣ ነገር ተቃራኒ ምኞት ያላቸው ወፎች አሉ፡፡ ‹‹ጊጊሾ›› የሚባለው ወፍ በአንዳንድ አካባቢዎች ‹‹ዘነበ›› በመባል ይታወቃል፡፡ የዚህ ወፍ ሳይንሳዊ ስሙ ‹‹ሬድ ቼስተድ ካኩ›› ይባላል፡፡

‹‹ጊጊሾ›› ወፍ የክረምቱን ወቅት አፍቃሪ ነው፡፡ ‹‹ጊጊሾ›› የክረምቱ ጊዜ ዘማሪ፣ የልምላሜው አብሳሪ ነው፡፡ ‹‹ጊጊሾ›› የበጋውን ጊዜ አይወድደውም፡፡ በበጋው ወቅት ያለበት ቦታ አይታወቅም፣ የኮቴው ኮሽታ አይሰማም፣ የድምጹ እልልታም አይደመጥም፡፡

 
ክረምቱ በበጋ መተካት ሲጀምር ‹‹ጊጊሾ›› የድምጹን ቮልዩም መቀነስ ይጀምራል፡፡ በክረምቱ ጊዜ የነበረው አረንጓዴውና ልምላሜው እየጠወለገ ሲሄድ ‹‹ጊጊሾ›› ድምጽም እየደበዘዘ መሄድ ይጀምራል፡፡ ከአቅጣጫው እየተፍቀለቁ ይፈስሱ የነበሩ የውሃ ምንጮች የፍሰት መጠናቸው እየቀነሰ ሄዶ መንጠባጠብ ሲጀምሩ፣ ‹‹ጊጊሾ›› ድምጽም ከመደመጥ ወደ አለመደመጥ ይወርዳል፡፡ በዝናቡ ረስርሶ፣ ረክቶና ረግቶ የነበረው መሬት መሰነጣጠቅ ሲጀምር፣ አቧራው እየቦነነ ከመሬት ወደ ሰማይ መበተን ሲጀምር ያኔ ‹‹ጊጊሾ›› ድምጹን ለወራት ያጠፋል፡፡ ‹‹ጊጊሾ›› የሚባል ወፍ ስለመኖሩ እንኳ እስኪረሳ ድረስ ድምጹ ድራሹ ይጠፋል፡፡

ነገር ግን የበጋው መጠናቀቂያ ጊዜ ሲደርስ ‹‹ጊጊሾ›› ድምጽ እንደገና ቀስ እያለ አልፎ አልፎ ሊደመጥ ይጀምራል፡፡ የበጋው የመጨረሻው የጸሐይ ትኩሳት ካባውን ደርቦ ስጋና ነፍስን ሲለበልብያኔ ‹‹ጊጊሾ›› ወፍ መቃተት ይጀምራል፡፡ አይኑን ወደ ሰማይ አንስቶ፣ አፉን በሰፊው ከፍቶ፣ ልብን በሚቀሰቅስ ስሜት ‹‹....›› የሚል የጣር ድምጽ ዝማሬ ማሰማት ይጀምራል፡፡

 
‹‹ጊጊሾ›› ድምጽ በሁሉም የምድሪቱ አቅጣጫ መደመጥ ሲጀምር የአገሩ አርሶ አደር ማረሻና ቀንበሩን ከሰቀለበት አውሮዶ መወልወል ይጀምራል፡፡ ለሚቀጥለው የመኸር ወቅት ቅድመ ዝግጅት ያደርጋል፡፡ ለወራት ተሰቅሎ የነበረውን የዘር እህል ቋጠሮ መፍታትና መፈተሽ፣ እንዲሁም ለመጪው የመኸር ስራ መንፈሱን ያነቃቃል፡፡

በዚህ ወቅት የአገሬው እንቦቃቅላ ሕጻናት ለወራት ተለይቷቸው የቆየው የዝናቡ ወቅት ተመልሶ ሊመጣ መሆኑን ‹‹ጊጊሾ›› ብስራት ስለሚረዱ በቃላት ሊገለጥ በማይችል ናፍቆት ውስጥ የሚወድቁበት ጊዜም ነው፡፡ ክረምቱ ደርሶ በንጹህ ሜዳ ላይ በሚተኛው የዝናብ ውሃ ላይ እየተንቦጫረቁ የሚጫወቱበትን ጊዜ በዓይነ ሕሊናቸው እየታያቸው በጉጉት እየተጠባበቁ ከጊጊሾ ጋር እየዘመሩ የሚናፍቁበት ወቅት ነው፡፡

‹‹ኮኬ›› የሚባለው ወፍ ደግሞ በተቃራኒ በጋውን ወቅት አፍቃሪ ነው፡፡ ‹‹ኮኬ›› የበጋው ወቅት ዘማሪ ነው፡፡ የክረምቱን ጊዜ አይወድደውም፡፡ በክረምቱ ወቅት ድምጹ አይሰማም፡፡ ክረምቱ ሲበረታ፣ ጫካና ገላጣው በዝናብ ሲታጠብ ያኔ ይከፋዋል፡፡ ክንፉን አንከርፍፎ፣ አንገቱን ቀብሮ፣ ጸጉሩን አንጨብሮ ማልቀስ ይጀምራል፡፡ የክረምቱ ወቅት አልፎ፣ ደመናው ተገፍፎ፣ ጉሙ ሰማዩን ሲለቅቅ፣ ጸሐይ ስትፈነጥቅ፣ ጭቃ ምድር ስትደርቅያኔ የእንጉርጉሮ ዝማሬውን ማሰማት ይጀምራል፡፡

 
የአገሬው አርሶ አደሮች በዚህ ወቅት ለመጪው የአጨዳ ወቅት የሚረዳቸውን ማጭድና መንሻቸውን ለወራት ከሰቀሉበት ቦታ አውርደው መወልወል ይጀምራሉ፡፡ ያረጀውን ጎተራ ማደስ፣ የተቦተረፈውን ጎተራ መጥቀም፣ በአረም የተዋጠውን አውድማ መጠራረግ፣ የዘመመውን ማድጋ ማቃናት ይጀምራሉ፡፡ መንፈሳቸውንም ያነቃቃሉ፡፡

ሕጻናቱም በአደይ አበባ ውስጥ ድብብቆሽ የሚጫወቱበት ጊዜ በዓይነ ሕሊናቸው እየታያቸው በናፍቆት ይቅበጠበጣሉ፡፡ እንጆሪና ሾላው፣ ጥንቅሽና ሸንኮራው፣ ባቄላና ቦይናው፣ በቆሎና ቦሎቄው አብበው፣ ጎምርተው፣ አሽተው፣ ተንዠርግገው የሚገምጡበትን ጊዜ እየናፈቁ አብረው ከኮኬ ጋር ይዘምራሉ፡፡

መንፈሳዊ ሰው እንደ ‹‹ጊጊሾ›› እና ‹‹ኮኬ›› ወፍ አንዱን ዘመን በደስታ፣ በእልልታና፣ በፌሽታ ተቀብሎ፣ ሌላው ዘመን ሲመጣ ግን ድምጹን አጥፍቶ፣ ተደብቶ፣ በሐዘን፣ በእንጉርጉሮና በእሮሮ ማሳለፍ የለበትም፡፡ መንፈሳዊ ሰው እንደ ታታሪ ገበሬ ሁሉንም ወቅት እንደ አመጣጡ ተቀብሎ በሚገባ ተጠቅሞበት ሊሸኘው ይገባል፡፡

 
ለሁሉ ጊዜ አለው፡፡ ለሁሉም ጊዜ ደግሞ ወቅት አለው፡፡ ሁሉም ወቅት ደግሞ የየራሱ የሆነ ብርቅዬ ዕድል አለው፡፡ ሁሉም ብርቅዬ ዕድሎች ብንጠቀምባቸው በረከት አላቸው፡፡ ሁሉም በረከቶች እርካታና ደስታ አላቸው፡፡ ሁሉም እርካታና ደስታ ደግሞ ምስጋናና ዝማሬ አላቸው፡፡

ስለሆነም ያለንበት ወቅት የሚመችም የማይመችም ሁኔታዎች አስከትሎ ቢመጣ እንደየአመጣጣቸው ተቀብለን እንድንሰራባቸው ጌታ ይርዳን፡፡ ዘመን ሲሸሽ ዘመን ሲመጣ በጊዜውም አለጊዜውም፣ በሚመችም በማይመችም ወቅት፣ ወገባችን ሳይላላ፣ ትጥቃችን ሳይፈታ፣ በሁኔታዎች ሳንረታ ዘመናችንን እንድንዋጅና ጊዜያችንን እንድንገዛ ጌታ ይርዳን፡፡

(ይህን ዕለታዊ ዲቮሽን ላይክ እና ሼር ያድርጉ፣ ወዳጅ ጓደኞችዎም እንዲያገኙ ያግዙ፡፡ ዲቮሽኑ ሳይቋረጥ ዓመቱን ሙሉ እንዲቀጥል በጸሎትዎና ጌታ በልብዎ በሚያስቀምጥ ማናቸውም ነገር ሁሉ ይደግፉ፡፡ ጌታ ይባርክዎ፡፡)

No comments:

Post a Comment