Saturday, October 4, 2014

ነቢያቶቻችንን አንውገር አንግደል



ዲቮሽን .11/2007 እሁድ፥ መስከረም 11/2007 ..
(
በፓ/ ተስፋሁን ሐጢያ)

ነቢያቶቻችንን አንውገር! አንግደል!!!

ኢየሩሳሌም፥ ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ነቢያትን የምትገድል፥ ወደ እርስዋ የተላኩትንም የምትወግር፥ ዶሮ ጫጩቶችዋን ከክንፎችዋ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን እሰበስብ ዘንድ ስንት ጊዜ ወደድሁ! አልወደዳችሁምም፥ እነሆ ቤታችሁ የተፈታ ሆኖ ይቀርላችኋል! (ማቴ 2337)

ላለፉት 20 እና 30 ዓመታት እግዚአብሔር ውድ አገራችንን ኢትዮጵያን እንደሚባርክ በልዩ ልዩ ነቢያቶች ሲነገር ቆይቷል፡፡ የውጭ ነቢያቶቹን እንኳ ትተን የራሳችንን ነቢያት ለአብነት ብንጠቅስ፥ (ነቢይ) ዶክተር ቶሎሳ ጉዲና በኢትዮጵያ ላይ የክብር ደመና እየመጣ መሆኑን በምድረበዳ ላይ ቆመው ተንብየዋል፡፡ (ነቢይ) ቄስ በሊና ሳርካ በባዶ ሜዳ ላይ ቆመው ኢትዮጵያ 30 ዓመታት ውስጥ በፈጣንነቱና በዓይነቱ በዓለም ታሪክ ሆኖ የማያውቅ የከፍታ ዘመን እየመጣ መሆኑን ተንብየዋል፡፡ (ነቢይ) መጋቢ አሮን ማንያዘዋል መርገም ከኢትዮጵያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፥ እንዲሁም ከወንዞቿ ተራሮቿ ፈጽሞ እንደሚወገድና ምድሪቱ እንደምትበልጽግ ተንብየዋል፡፡ ከጸሐፊዎች ደግሞ ወጣቱ የተሐድሶ (ነቢይ) ጸጋአብ በቀለ ይጠቀሳል፡፡ ለአይነት ያህል እነዚህን የእግዚአብሔር ሰዎች ጠቀስኩ እንጂ ሌሎችም በርካታ ነቢያቶች የምድራችንን ተሐድሶና መባረክ ተናግረዋል፡፡

ለብዙ ዘመናት መታወቂያዋ ድህነት፥ ኋላቀርነትና ጦርነት የሆነችው ይህች ምድር ዛሬ ዛሬ በሁሉም ማህበራዊ ሴክተሮች የፈጣን ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ምሳሌ ተደርጋ እየተወሰደች ነው፡፡ ዘወትር የምንሰማው የመንግስታቱ ድርጅት መሪዎች ምስክርነቶች፥ የአውሮፓና የአፍሪካ መንግስታት ሪፖርቶች፥ እንዲሁም የዓለማቀፍ የንግድና ኢንዱስትሪ ባለሀብቶች ጉባኤዎችና የስራ እንቅስቃሴዎች የምንሰማው ሁሉ አገራችን ኢትዮጵያ በማደግ ላይ መሆኗን ነው! ዓይናችንን ጨፍነን አላይም ካላልን፥ ጆሮችንን ሽፍነን አንሰማም ካላልን በቀር ኢትዮጵያ በሚያስገርም የዕድገት መስመር ላይ ነች!

አገራችን ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ሰማይ ላይ ብትወጣና በመንፈሳዊ ነገርዋ ብትጠወልግና ብትደርቅ እንዲሁም ብትሞት ምን ይረባናል? ስጋችን ደልቶት መንፈሳዊ ሕይወታችን ቢከሳና ቢጎሰቁል ምን ይጠቅመናል? ዓለማችንን ሁሉ አትርፈን፥ ዓለማችንን ሁሉ ቀጭተን፥ ነፍሳችንን ግን ብናጎድል ምን ይረባናል?

ታውቃላችሁ፥ የአገራችንን ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን በመንፈሳዊ ሪቫይቫልና ተሐድሶ ካልተዋጠ በስተቀር ከባድ አደጋ ይከተላል! አገራችን በኢኮኖሚው አቅጣጫ ብቻ አድጋና ተመንድጋ፥ በቤተክርስቲያን አገልግሎቶች ግን ብትጫጫ መንፈሳዊ ድርቅ ይመታታል! መንፈሳዊ ድርቀቱ ወደ ምድረበዳነት ይቀየርና በሌሎች አገሮች የምናያቸው እርኩሰቶች በቤተክርስቲያኖቻችን ውስጥ ለመገርሰስ የሚከብዱ ዙፋኖቻቸውን ይተክላሉ፡፡ ቤተክርስቲያንም ትልቅ ችግር ውስጥ ትገባለች፡፡

ይህ እንዳይመጣ፥ እግዚአብሔር ነቢያትን በልዩ ቅባት ቀብቶ እያስነሳ ነው! ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአገራችን ባልተለመደ መልኩ የነቢያት ቅባት በምድሪቱ ላይ እየፈሰሰ ነው፡፡ ነቢያቶቻችንም ከዚህ ቀደም ታይተው የማይታወቁ አገልግሎቶች እየሰጡ ነው፡፡ የትምህርት ደረጃን፥ ጾታና ዕድሜን፥ ቋንቋና ልምድን፥ እንዲሁም ብሔርና ክልልን ከመስፈርቱ የማያስገባው ጌታ መነፈስ ቅዱስ ያለአድልዎ ወንዶችና ሴቶች ነቢያትን ቀብቶ እያስነሳ ነው! ክብሩ ሁሉ ለእርሱ ይሁን!!

በአገራችን እየመጣ ያለው በዓይነቱ ከዓለም ልዩ የሆነው ፈጣን ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን፥ ቀድሞን እንዳይሄድ፥ በቤተ ክርስቲያንም በዓይነቱ ልዩ የሆነ የአገልግሎት ቅባት ያስፈልገናል! በሚፈስሰው ልዩ ቅባት ታግዛ ቤተክርስቲያን የተቀቡ የአገር መሪዎችን፥ ፖሊቲሻኖችን፥ ኢኮኖሚስቶችን፥ ሳይንቲስቶችን፥ ቴክኖሎጂስቶችንታፈራለች፡፡

ስለሆነም ለዚህ ታላቅ መለኮታዊ ዓላማ እግዚአብሔር በምድራችን ቀብቶ እያስነሳ ያላቸውን ነቢያቶች ለመውገር ያነሳናቸውን ድንጋዮች እንጣል! እነዚህን አገልጋዮች ለመውጋት እየለጠጥን ያለነውን ቀስትና ፍላጻ እንጣል! በእግዚአብሔር ቅቡአን ላይ የጀመርነውን የመቃብር ቁፋሮ ዘመቻ እናቁም! ነቢያቶቻችን አፈራችንን ይዘው ይጸልያሉ፥ ወንዞቻንን ይዘው ይጸልያሉ፥ ተራሮቻችን ላይ ወጥተው ይጸልያሉ፥ ስቴዲዬሞቻንን ይዘው ይጸልያሉ! ለፓርላማችን፥ ለምክር ቤታችን፥ ለዳር ድንበራችን፥ ለሰላማችንይጸልያሉ!

ወገኖች ሆይ፥ ነቢያቶቻን ስለእኛ ዋጋ እየከፈሉ ነው! ጌታ ለምድራችን የተናገረው ተስፋ ቃል እንዲፈጥን በጾምና በጸሎት እየተራቡና እየተጠሙ የጌታን ፊት እያዩ ነው፡፡ ከሆነልን እኛም በጾምና በጸሎት ራሳችንን በማዋረድ የመንፈስ ቅዱስ ቅባት እንቀበል፡፡ ጊዜው የእግዚአብሔር የስራ ጊዜ ነውና፥ ከጌታ ጋር ለመስራት አብረን እንሰለፍ፡፡ ካልሆነልን ደግሞ ለሌሎች መሰናክል ከመሆን እንቆጠብ! ነቢያቶቻችንን አንውገር! ነቢያቶቻንን አንግደል!!! እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ፡፡

(ይህን ዕለታዊ ዲቮሽን ላይክ ያድርጉ፥ ለወዳጅ ጓደኞችዎም ያስተላልፉ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!)

No comments:

Post a Comment