Saturday, October 4, 2014

እግዚአብሔርን እንዳትረሳ ተጠንቀቅ!


ዲቮሽን .14/2007 ረቡዕ፥ መስከረም 14/2007 ..
(
በፓ/ ተስፋሁን ሐጢያ)


እግዚአብሔርን እንዳትረሳ ተጠንቀቅ!


ያልሞላሃቸውንም ሀብትን የተሞሉ ቤቶች፥ ያልማስሃቸውንም የተማሱ ጉድጓዶች ያልተከልሃቸውንም ወይንና ወይራ በሰጠህ ጊዜ፥ በበላህና በጠገብህም ጊዜ፥ በዚያን ጊዜእግዚአብሔርን እንዳትረሳ ተጠንቀቅ! (ዘዳ 612-13)
ያልተለወጠ ሰው አለመለወጡ ከሚታወቅባቸው ግልጽ ባህርያቶች መካከል አንዱ፥ ስጋዊ ትምክህት ነው! ያልተለወጠ ሰው አዘውትሮ ስለራሱ ያወራል፥ ባለው ነገር ይመካል፡፡ ዲግሪ ጭኜአለሁ፥ ማስተር በጥሼአለሁ፥ እዚህ ደርሻለሁ፥ ይህንን አውቃለሁ፥ ያንን አቅጃለሁ ሲል ይደመጣል፡፡ ይህንን አግኝቼ፥ እኔ ምን አጥቼ፥ ሁሉ በእጄ፥ ሁሉ በደጄእያለ ራሱን ከፍ ከፍ ያደርጋል፡፡ የእውቀትን ራስ፥ የጥበብን ጌታ፥ የጤናና የሀብትን ባለቤት፥ የብልጽግናና የስኬትን ምንጭ ይረሳዋል!
መንፈሳዊ ሰው ግን የራሱን ማነንት ያውቃል! ሲያገኝ፥ ሲሞላለት፥ ሲማር ሲመራመር፥ ሲቀናውና ሲደላውበሁሉ እግዚአብሔርን ያመሰግናል፡፡ የተቀበላቸውን ነገሮች ሁሉ ከጌታ ስለመሆኑ እውቅና ይሰጣል!
ታውቃላችሁ፥ የመልካም ነገሮች ሁሉ ምንጭ እግዚአብሔር ነው! ገንዘብ ከፍለን ብንማር፥ ዋጋ ከፍለን ብንገዛ፥ ጥረን ግረን ብንበላ፥ ታክመን ብንድንሁሉ የሆነው ከእግዚአብሔር ነው!
ታውቃላችሁ፥ ስለደከምን የምናገኝ ቢመስለንም፥ ስለተማርን የሚከፈለን ቢመስለንም፥ ስለነገድን የምናተርፍ ቢመስለንም፥ ቢገባንም ባይገባንም፥ ሁሉ የሆነው ከጌታ ነው!
ታውቃላችሁ፥ ከእኛ የሆነ አንዳች የለም! ጤና ሰላማችን፥ ብርታት ጉልበታችን፥ ስጋና ነፍሳችን ሁሉ የእርሱ ነው! መኖሪያ ቤታችን፥ ትዳር ልጆቻችን፥ መኪና ፎቃችን፥ እቁብ ቁጠባችን፥ እርሻ አክሲዮናችንሁሉ የእርሱ ነው! ከእኛ የሆነ የለም!!
ታውቃላችሁ፥ እግዚአብሔር ያልነበረውን ወደ መኖር ሊያመጣ የሚችል አምላክ መሆኑን ካመንን፥ ዛሬም ያልዘራነውን ሊያሳጭደን፥ ያላጨድነውን ሊያሳቅፈን፥ ያላየነውን ሊያወርሰንይችላል! ከባዶ ቤት ጥጋብ፥ ከባዶ ሰማይ ዝናብ፥ ከባዶ ኪስ ሂሳብ፥ ከባዶ ቡሀቃ ቀለብሊሞላ ይችላል!
ታውቃላችሁ፥ የምናመልከው አምላካችን ሁሉን ቻይ ነውና፥ ከሞትም ሊያድን፥ የሞተን ሊያስነሳ ይችላል! ሕመምን ሊፈውስ፥ ሽባ ሊተረትር፥ ጎባጣ ሊያቀና፥ እውሩን ሊያበራ፥ ደንቆሮ ሊያሰማ፥ ለመጻሙን ሊያነጻ ይችላል፡፡ ጌታ ታሪክ ቀያሪ ነውና፥ መካኒቷ ወልዳ፥ ሚስኪኗ ተወድዳ፥ ያጣችው አግኝታ፥ ያገኘችውም ለምታ እናያለን!
ይህ ሁሉ ሲሆንልን ታዲያ፥ የስጦታዎቻችን ምንጭና የስኬታችን አልፋና ኦሜጋ የሆነውን ጌታ ረስተን፥ ስኬታችንን "የቃላቴ መጀመሪያ አንቺ ነሽ፥ መጨረሻም አንቺ ነሽ" እያልን እንዳናመልካት ጌታ ይጠብቀን! የመልካም ነገር ሁሉ ባለቤት የሆነውን ጌታ ረስተን ስለራሳችን እንዳንዘምር ጌታ ይርዳን!
(ይህን ዕለታዊ ዲቮሽን ላይክ ያድርጉ፥ ለወዳጅ ጓደኞችዎም ያስተላልፉ፡፡ ጌታ ይባርካችሁ፡፡ )

No comments:

Post a Comment