ዲቮሽን ቁ.25/07 እሁድ፣
መስከረም 25/2007 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)
ባይወለዱ ኖሮስ ?
… መጽሐፍ እንደሚል ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሞተ፥ ተቀበረም፥ መጽሐፍም እንደሚል በሦስተኛው
ቀን ተነሣ፥ ለኬፋም ታየ በኋላም ለአሥራ ሁለቱ፤ ከዚያም በኋላ ከአምስት መቶ ለሚበዙ ወንድሞች በአንድ ጊዜ ታየ፤ ከእነርሱም
የሚበዙቱ እስከ አሁን አሉ አንዳንዶች ግን አንቀላፍተዋል፤ ከዚያም በኋላ ለያዕቆብ ኋላም ለሐዋርያት ሁሉ ታየ፤ ከሁሉም በኋላ እንደ ጭንጋፍ ለምሆን ለእኔ ደግሞ ታየኝ። እኔ ከሐዋርያት ሁሉ የማንስ ነኝና፥ … ከሁላቸው ይልቅ ግን ደከምሁ፥
ዳሩ ግን ከእኔ ጋር ያለው የእግዚአብሔር ጸጋ ነው እንጂ እኔ አይደለሁም።(1 ቆሮ 15፡3-10)
ውድ አንባቢዬ፣ ለጽንስ ማቋረጥ አስፈላጊ የሚመስሉ ሌሎች አራት ምክንያቶችንም ላቅርብልዎት፡፡
ምክንያት (1)፣ አንድ ወንጌላዊና ሚስቱ እጅግ በጣም ድሃ የሆነ ኑሮ ይመራሉ፡፡ ሁለቱም 14 ልጆች ወልደዋል፡፡ በዚህ ላይ ሳይዘጋጁበት ሚስትዬው 15ኛ ልጃቸውን ማርገዟን አረጋገጡ፡፡ ባልና ሚስቱ በድህነት እየማቀቁ ናቸው፡፡ ስለሆነም፣ የእነዚህን ባልና ሚስት ድህነት ከግንዛቤ በማስገባትና የዓለም ሕዝብ ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን በማየት ሴትየዋ የተረገዘውን ልጅ በውርጃ ብታስወጣው እንደሚሻል ይመክሩ ይሆናል፡፡
ምክንያት (2)፣ አባትየው የመተንፈስ ችግር አለበት፡፡ እናት ደግሞ የሳንባ በሽታ አለባት፡፡ ሁለቱም አራት ልጆች ወልደዋል፡፡ የመጀመሪያ ልጃቸው ዓይነስውር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ሞቶባቸዋል፡፡ ሶስተኛው ልጃቸው መስማት የተሳነው ሲሆን አራተኛው የሳንባ በሽተኛ ነው፡፡ እናት በድንገት አምስተኛ ልጃቸውን አረገዘች፡፡ በእነዚህ ከአቅም በላይ በሆኑ ምክንያቶች የተነሳ ውርጃ መፈጸም የተሻለ አማራጭ መሆኑን ይደግፉ ይሆናል፡፡
ምክንያት (3)፣ አንድ ነጭ፣ የአስራ ሶስት ዓመቷን ጥቁር ልጅ አስገድዶ በመድፈሩ ምክንያት አረገዘች፡፡ እርስዎ የዚህች ልጅ ወላጅ ቢሆኑ ውርጃ እንደሚሻል ያስቡ ይሆናል፡፡
ምክንያት (4)፣ አንዲት ወጣት ልጅ ከጋብቻ በፊት አረገዘች፡፡ እጮኛ ነበራት፡፡ ነገር ግን እጮኛዋ የልጁ አባት አይደለም፡፡ ከዚህም የተነሳ እርስዎ ልጅቱ እንድታስወርድ ይመክሩ ይሆናል፡
በ1ኛው ምክንያት ጽንስ ተቋርጦ ቢሆን ኖሮ፣ ታላቁ የ19ኛው ምዕተ ዓመት ወንጌላዊ ጆን ዊስሊ ተገድሎ ነበር ማለት ነው፡፡ በ2ኛው ምክንያት ውርጃ ተፈጽሞ ቢሆን ኖሮ፣ ታላቁ የሙዚቃ ቀማሪው ቤትሆቨን ተገድሎ ነበር ማለት ነው፡፡ በ3ኛው ምክንያት ጽንስ ተቋርጦ ቢሆን ኖሮ፣ ታላቋን ጥቁር ዘማሪ ኤትል ዋተርስን ተገድላ ነበር፡ በ4ኛው ምክንያት ጽንስ ተቋርጦ ቢሆን ኖሮ፣ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገድሎ ነበር ማለት ነው፡፡
ውድ አንባቢ ሆይ፣ ስለሐዋርያ ጳውሎስ ያስቡ፣ ባይወለድ ኖሮ? ጨንግፎ
ቢቀር ኖሮ? የጌታ ኢየሱስን ደቀመዛሙርትም ያስቡ፡፡ ባይወለዱ ወይም ጨንግፈው ቢሆን ኖሮ?
ነገስታቶቻችንን እነአጼ ላሊበላን፣ አጼ ቴዎድሮስን፣ አጼ ዮሐንስን፣ አጼ ሚኒሊክን፣ አጼ ኃይለስላሴን ያስቡ፡፡ የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትራችንን መለስ ዜናዊን እንዲሁም ያሁኑን አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን ያስቡ፡፡ እነዚህ ሰዎች እንዳይወለዱ ተፈርዶባቸው ቢሆን ኖሮስ?
እነሼክ አላሙዲንን፣ እነሜትር አስቲስት አፈወርቅ ተክሌን፣ እነአበበ ቢቂላን፣ እነኃይሌ ገብረስላሴን፡ እነደራርቱ ቱሉን ያስቡ፡፡ እነዚህ ሰዎች እንዳይወለዱ ተፈርዶባቸው ቢሆን ኖሮስ?
ከአገር ወጣ ብለው ባራክ እነ ኦባማን፣ ዴቪድ ካሜሮንን፣ እነ ኔልሰን ማንዴላን፣ እነ ማዘር ቴሬዛን፣ እነ አንድራ ጋንዲን ያስቡ፡፡ እነዚህ ሰዎች እንዳይወለዱ ተፈርዶባቸው ቢሆን ኖሮስ? ከዘማሪዎችም እነዶን ሞይንን፣ እንዳርሊን ዘችን፣ እነተስፋዬ ጋቢሶን፣ እነሊሊን ያስቡ፡፡ እነዚህ ሰዎች እንዳይወለዱ ተፈርዶባቸው ቢሆን ኖሮስ?
ከእግር ኳሱም ዓለም እነሮናልዶን፣ እነሜሲን አስቡ፣ እነዚህ ሰዎች እንዳይወለዱ ተፈርዶባቸው ቢሆን ኖሮስ? ከሳይንቲስቶች እነቶማስ ኤዲሰን እነኒውተንን አስቡ፣ ከሐኪሞችም፣ ከፋርማሲስቶችም፣ ከአንትሮፖሎጂስቶችም፣ ከአርኪዎሊጂስቶችም …አስቡ፡፡ እነዚህ ሰዎች እንዳይወለዱ ተፈርዶባቸው ቢሆን ኖሮስ?
ውድ ወዳጄ፣ ጽንስ ማቋረጥ ይቅር! የተጸነሰው ልጅ ምን ሊሆን እንደሚችል አይታወቅም፡፡ ለሰውነቷ ማሞቂያ ጨርቅ ካጠራት ድሃ ሴት ቢሊየነር ሊወለድ ይችላል፡፡ ከዓይነስውሯ ሆድ ዓይናማ፣ ከፈሪዋ ጀግና፣ ከማይሟ ሳይንቲስት …ሊወለድ ይችላል፡፡ ነገ የሚሆነው አይታወቅምና፣ ሰው አፍረን፣ ይሉኝታ ፈርተን፣ በማናቸውም ሁኔታ የተረገዘን ጽንስ አንግደለው! በዚህ ጽንስ ነገ ስማችንን በዓለም የሚያስጠራ፣ ሀገርን የሚያኮራ …ሊሆን ይችላል! ጽንስ ማቋረጥ ይቅር! ነገ የሚሆነው አይታወቅምና ነፍስ ማጨንገፍ ይቅር!
------------------------
(ይህን ዕለታዊ ዲቮሽን ላይክ እና ሼር ያድርጉ፣ ወዳጅ ጓደኞችዎም እንዲያገኙ ያግዙ፡፡ ዲቮሽኑ ሳይቋረጥ ዓመቱን ሙሉ እንዲቀጥል በጸሎትዎና ጌታ በልብዎ በሚያስቀምጥ ማናቸውም ነገር ሁሉ ይደግፉ፡፡ ጌታ ይባርክዎ፡፡)
No comments:
Post a Comment