Saturday, October 4, 2014

የሚያመልኩትን አንንቀፍ፥ አናስቸግራቸው!


ዲቮሽን .12/2007 ሰኞ፥ መስከረም 12/2007 ..
(
በፓ/ ተስፋሁን ሐጢያ)


የሚያመልኩትን አንንቀፍ፥ አናስቸግራቸው!



 (ኢየሱስ) በቢታንያ በለምጻሙ ስምዖን ቤት በማዕድ ተቀምጦ ሳለ፥ አንዲት ሴት ዋጋው እጅግ ውድ የሆነ ንጹህ የናርዶስ ሽቱ በአልባስጥሮስ ቢልቃጥ ይዛ መጣች፥ ቢልቃጡንም ሰብራ ሽቱውን በራሱ ላይ አርከፈከፈችው፥ በዚያ ከነበሩት አንዳንዶች በድርጊቱ ተቆጥተውሴትየዋን ነቀፏት፡፡ ኢየሱስ ግን እንዲህ አላቸው፥ "ተዉአት፥ ለምን ታስቸግሯታላችሁ፥ መልካም ነገር አድርጋልኛለች፡፡ (ማር 143-6)
እውነተኛ አምልኮ ሲኖር፥ ሁሌም እንቅስቃሴ ይኖራል፡፡ የሽብሸባ፥ የጭብጨባ፥ የእልልታ፥ የዝላይ፥ የጭፈራነገር ይኖራል፡፡ እጅ ማንሳት፥ መንበርከክ፥ ወለል ላይ በደረት መደፋት፥ በጀርባ መንጋለልና የመሳሰሉት ይገኛሉ፡፡ አልፎ አልፎም የመውደቅና የመነሳት፥ የመንከባለልና የመንፈራፈር ሁኔታም አለ፡፡ እነዚህን ነገሮች የሚቀበሉ የሚወድዱና የሚደግፉ እንዳሉ ሁሉ የማይቀበሉ የሚጠሉና የሚቃወሙ አሉ፡፡
ልጆች በገዛ ወላጆቻቸው ቤት እንዴት ነው የሚሆኑት? ቢፈልጉ ሶፋ ላይ በስርዓት ይቀመጣሉ፥ ቢፈልጉ ወለል ላይ ይንከባለላሉ፡፡ የገዛ ቤታቸው ነዋ! ቤተክርስቲያን የክርስቶስ ኢየሱስ ነች! ምዕመናን ደግሞ በገዛ ደሙ የተዋጁ ልጆች ናቸው፡፡ ስለሆነም ምዕመናን በገዛ አባታቸው ቤት፥ በገዛ ቤታቸው ውስጥ በነጻነት የማምለክ መብት አላቸው፡፡ ውስጣቸው እንደተነካ ምላሽ እየሰጡ ማምለክ ይችላሉ፡፡ የውስጣቸውን መነካትም ሆነ ስሜት ተከተለው ጎንበስ ቀና እያሉ ሊሰግዱ፥ ጥሩንባና መለከት እየነፉ ሊጨፍሩ፥ ወይንም ፉጨትና ጩኸት እያሰሙ ለጌታ ያላቸውን ፍቅር ሊገልጹ ይችላሉ፡፡
የአላዛርና የማርታ እህት የነበረችው ማርያም ጌታን ያመለከቸበት መንገድ ደግሞ የተለየ ነበር፡፡ እጅግ ውድ ሽቱ በጌታ ላይ በማፍሰስ አመለከችው፡፡ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፥ የማርያም ውድ ሽቱ ውድ ነፍሷን ይወክላል፡፡ የሽቱዋ መፍሰስ የነፍሷን መፍሰስ ይገልጻል!
ታውቃላችሁ፥ እውነተኛ እምልኮ ከነፍስ ይመነጫል! በጌታ ፊት ነፍሳችን ካልፈሰሰ በስተቀር እውነተኛ አምልኮ ለማቅረብ ይቸግራል፡፡ ነፍሳችንን ስናፈስስ ደግሞ ነፍስ አይቀርልንም! ሺህ ጊዜ ሺህ ፕሮቶኮል ብናሳምር፥ እልፍ ጊዜ እልፍ ባንድ ብናቆም ነፍሳችንን በጌታ ፊት እንድናፈስስ አይረዳንም፡፡ የአዳራሻችን ውበት፥ የአካውንታችን ስፋት፥ የመጋቢዎቹ ግዝፈት፥ የመዘምራኑ ፕሮፌሽናል ጥራት ነፍሳችንን ጠልቆ አያገኘውም፡፡ በእውነትና በመንፈስ ጌታን ማምለክ ግን ነፍሳችንን ያገኘዋል!
ታውቃላችሁ፥ ነፍስን በጌታ ፊት የሚያፈስስ አምልኮ በቤተክርስቲያን ደንብና ስርዓት ውስጥ አይገኝም! እውነተኛ አምልኮ በባህልና ወጋችን ውስጥም የለም! ስታይላችን፥ ፕሮፋይላችን፥ ፕሮግራማችንም ሆነ ፕሮሴሽናችን ከነፍስ የመድረስ፥ ነፍስን የመንካት አቅም የላቸውም! ነፍስን የሚነካ አምልኮ ያለው በመንፈስ ቅዱስ እጅ ነው! ታዲያ ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነክተው ለአምልኮ ምላሽ ሲሰጡ አንንቀፋቸው፥ አናስቸግራቸው!
አንዳንድ ሰዎች ሲያመልኩ ለስርዓትና ደንባቸው ያደገድጋሉ! አስር ጊዜ ክራባታቸውን ያስተካክላሉ፥ አስር ጊዜ የኮት ቁልፋቸውን እየከፈቱ ይዘጋሉ፥ አስር ጊዜ ፊትና ኋላቸውን ግራና ቀኛቸውን ያቃኛሉ፥ አስር ጊዜ ሰዓታቸውን ይመለከታሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች አስሬ ሲኳፈሱ፥ አስሬ ሲኩነሰነሱ፥ አስሬ ሲክበሰበሱየአምልኮ ጊዜው ያበቃል! ችግሩ ታዲያ የእነርሱ ራሳቸውንና ልብሳቸውን "ማምለካቸው" ላይ ሳይሆን - ነፍሳቸውን አፍስሰው የሚያመልኩትን መንቀፋቸውና ማስቸገራቸው ላይ ነው! ዳዊት በሜልኮል ሲነቀፍ፥ ማርያም በደቀመዛሙርት ተነቅፋለች! ዳዊት ራሱን ዲፌንድ ሲያደርግ፥ ለማርያም ደግሞ ጌታ ኢየሱስ ዲፌንድ አድርጎላታል!
ታውቃላችሁ፥ ነጻ አምልኮ የሚጠሉና ተሰጥተው የሚያመልኩትን የሚነቅፉ ሰዎች ችግር ያለባቸው ናቸው! ሜልኮልን አስቧት፥ ችግር አለባት! ደቀመዛሙርቱን፥ በተለይም ይሁዳን አስቡት፥ ችግር አለበት! ታውቃላችሁ፥ የተፈታ አምልኮ የማይወዱ ሰዎች ችግር ያለባቸው ናቸው!
ጌታ ያደረገልንን ስናስብ ራሳችንን አዋርደን፥ ክብራችንን ጥለን፥ ነፍሳችንን አፍስሰን ለማምለክ አንቸገርም! ምሕረቱንና ፍቅሩን ስናስብ፥ በጎነቱንና ቸርነቱን ስናሰላስል ተሰጥተን ለማምለክ አይከብደንም፡፡ ከጌታ ያገኘነውን ስሰላምና ደስታ፥ እፎይታና እርካታ ስናስብነፍስ አይቀርልንም! የተቀበልነውን ድንቅና ተአምራት፥ ፈውስና በረከትስናስብ ነፍስ አይቀርልንም!
ሆኖም፥ ሰዎች የውስጥ ስሜታቸውን የሚገልጹት በተለያየ መንገድ ነው፡፡ አንዳንዱ በጸጥታና በእርጋታ ማምለክ ሲመርጥ ሌላው ደግሞ ጭር ሲል አይሆንለትም፡፡ አንዳንዱ ያለ ሙዚቃ ድምጽ የለሽ እንባውን እያፈሰሰ ማምለክ ሲወድ ሌላው ደግሞ አጥቢያዋ ባላት ሙሉ ባንድ ላይ በተጨማሪ ጥሩንባ ይዞ በመምጣት በየመሃሉ እየነፋ ማምለክ ይወዳል! ስለሆነም የያንዳንዱን ሰው የአምልኮ ፍላጎት መጠበቅ ካለብን እርስ በርስ መቀባበል አለብን፡፡ ሁሉ በስርዓት ይሁን እንጂ፥ ሁሉ በእውነትና በመንፈስ ይሁን እንጂ፥ በጌታ ዘንድ ምንም ችግር የለም!
(ይህንን ዕለታዊ ዲቮሽን ላይክ ያድርጉ፥ ለወዳጅ ጓደኞችዎም ያስተላልፉ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!)

No comments:

Post a Comment