Saturday, October 4, 2014

መንገዱ ሲዘጋ !

ዲቮሽን .23/07 አርብ፣ መስከረም 23/2007 ..
(
በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)

መንገዱ ሲዘጋ !


….እግዚአብሔርም በለዓምን፦ (ከሞዓብ አለቆች) ጋር አትሂድ የተባረከ ነውና ሕዝቡን(እስራኤልን) አትረግምም አለው።….በለዓም ሲነጋ ተነሣ፥ አህያይቱንም ጭኖ ከሞዓብ አለቆች ጋር ሄደ። እርሱም ስለ ሄደ እግዚአብሔር ተቈጣ የእግዚአብሔርም መልአክ ሊቋቋመው በመንገድ ላይ ቆመ…. (ዘሁ 22፡1-41)


ሰው የፈለገውን መንገድ መርጦ እንዲጓዝ ነጻ ፈቃድ ተሰጥቶታል፡፡ እግዚአብሔር የሰውን ነጻ ፈቃድ በጉልበት አይጠመዝዘውም፡፡ ሆኖም የሰው ነጻ ፈቃድ በእግዚአብሔር እቅድ ላይ በተጽዕኖ በሚነሳበት ጊዜ እግዚአብሔር የራሱን እርምጃ ከመውሰድ ወደኋላ አይልም፡፡
የመጀመሪያው የእግዚአብሔር እርምጃ መንገድ መዝጋት ነው፡፡ መንገድ የሚዘጋው ሰው መሄጃ ስከሚያጣ ቆም ብሎ እንዲያስብ ነው፡፡ ሰው ቆም ብሎ ስለመንገዱ ማሰብ ሲጀምር ብዙ ሊስተካከሉ የሚገባቸው ነገሮች እንዳሉ ወለል ብለው ሊታዩት ይጀምራሉ፡፡ 

እግዚአብሔር የበለአምን መንገድ ዘጋበት፡፡ በለአም በተከለከለ መንገድ ሊሄድ ነበር፡፡ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ሊረግም፣ የመንግስት ጉርሻ ሊወስድ ነበር የወጣው፡፡ በእግዚአብሔር ዘንድ ይህ የተከለከለ ነው! እግዚአብሔር ለሕዝቡ ካለው መልካም ሐሳብ አንዱ በረከት ነው፡፡
የእግዚአብሔር ሕዝብ በክርስቶስ በኩል ለበረከት ተጠርቷል፡፡  የእግዚአብሔር ሕዝብ ሰማያዊና ምድራዊ በረከቶች እንዲቀበል ተጠርቷል፡፡ ይህ ነው የጌታ እቅድ! ይህን እቅድ መቃወም እግዚአብሔርን መጻረር ነው፡፡ ይህን ሕግ ተጻርሮ ነው፣ እግዚአብሔር የበለአምን መንገድ የዘጋው፡፡

መንገዳችን በእግዚአብሔር ሲዘጋ አህያችንን እንኳ አያልፍም፡፡ ጌታ ከተጣላን በመርፌ ቀዳዳ ክራችን አትገባም፡፡ ቢዝነስ እንቨስትመንት ኪሳችን አይሞላም፡፡ የእቁብ አክሲዮናችን ዕጣችን አይወጣምም፡፡ ጌታና ሎሌ ተጣልቶ፣ ቅልና ድንጋይ ተማትቶ ነገር አያምርና ስኬት አይገኝም፡፡ 

ስለሆነም፣ የበለአም አህያ ከመስመሩ ወጣች፡፡ ነገር ግን በለአም ታውሯልና አህያዪቱን ወደ መስመሩ ሊመልሳት ይደበድባት ጀምር፡፡ አህያዪቱ ግን ወይ ፍንክች፣ ወይ ንቅንቅ አላለችም! ነገሮቻችን ከመስመር ሲወጡ ምንድነው የምናደርገው? 

ታውቃላችሁ፣ እግዚአብሔር መንገዳችንን ከዘጋና በመስመራችን ላይ ከቆመ ነገሮቻችን በትክክል ሊሄዱ አይችሉም፡፡ ብንደክም ብንለፋ ከመስመሩ አይገቡም፡፡ መንገዳችንን  እግዚአብሔር ከዘጋው እውቀት ብልሃታችን፣ የስራ ልምዳችን ሊሰራ አይችልም፡፡ 

በለአም በሞአብ መንግስት የገንዘብ ጉርሻና ክብር ታውሮ ነበርና በመንገዱ የቆመውን መልአክ ማየት አልቻለም፡፡ ታውቃላችሁ፣ ገንዘብ ካሳወረን አምላክ አይታይም፡፡ ገንዘብ ካሳወረን ጽድቅና ኩነኔው ጠርቶ አይታይም፡፡ ገንዘብ ጌታ ሲሆን ብርሃን ይጨልማል፣ ዓይንም ይታወራል፡፡ 

በለአም ታወረ፡፡ እንደ ቶምቦላ ሎተሪ ከመቅጽበት ዕድል በሹመት ሽልማት፣ በዝናና ክብር፣ በወርቅና በብር ሲንበሸበሽ እንዴት አይታወር! እንዲህ ዓይነት ነገር ሲያጋጥም ማነው የማይታወር? ከፊት ለፊታችን የተዘረገፉ ዕድሎችን ተሻግረው ጌታን የሚያዩ የስንቶቻችን አይኖች ናቸው? ምቾት ሲበዛልን፣ ድሎት ሲትረፈረፍ፣ ስንንደላቀቅና ስንሞላቀቅ የማናችን አይን ነው የማይጠፋ? 

በለአም አህያው ከመንገድ ስትወጣ የወሰደው የማስተካከያ እርምጃ ዱላ ነበር፡፡ ጥበብ የጎደለው የሰው ልጅ ለችግር መፍቻነት ኃይልን ይጠቀማል፡፡ ነገር ግን ጥበብ ከኃይል ይበረታል፡፡ እግዚአብሔርን መፍራት መፍትሔ ያመጣል፡፡

በለአም አህያው ከመንገድ ስትወጣ፣ ይህ ለምን ሆነ ብሎ ራሱን መጠየቅ ነበረበት፡፡ የሰው ልጅ በተዘጋ መንገድ እየሄደ ውጤት ሲያጣ ሴሚናር፣ ወርክሾፕ፣ ኮንፍረንስ እያለ መከራውን ያያል፡፡ ፕሮግራም ክለሳ፣ በጀት ቅነሳ ለማድረግ ይጥራል፡፡ ጉዳዩ ግን ከፕሮግራሙም ሆነ ከበጀቱ አይደለምና ልፋቱ ይበዛል፡፡ ችግሩ ከመንገዱ ላይ ነው፡፡ መንገዱ ያልተፈቀደ ነው፡፡ መንገዱ ዝግ መንገድ ነው፡፡ 

------------------------
(
ይህን ዕለታዊ ዲቮሽን ላይክ እና ሼር ያድርጉ፣ ወዳጅ ጓደኞችዎም እንዲያገኙ ያግዙ፡፡ ዲቮሽኑ ሳይቋረጥ ዓመቱን ሙሉ እንዲቀጥል በጸሎትዎና ጌታ በልብዎ በሚያስቀምጥ ማናቸውም ነገር ሁሉ ይደግፉ፡፡ ጌታ ይባርክዎ፡፡)

No comments:

Post a Comment