Saturday, October 4, 2014

ያልተሰቀለው መስቀል!


ዲቮሽን .17/2007 ቅዳሜ፥ መስከረም 17/2007 ..
(
በፓ/ ተስፋሁን ሐጢያ)


ያልተሰቀለው መስቀል!


ከክርስቶስ ጋር ተሰቅያለሁ፥ ከእንግዲህ እኔ አልኖርም፥ ነገር ግን ክርስቶስ በውስጤ ይኖራል፡፡ አሁንም በስጋ የምኖረው ኑሮ በወደደኝና ስለእኔ ራሱን አሳልፎ በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለኝ እምነት ነው (ገላ 220)
በየዓመቱ በኢትዮጵያ የመስቀል በዓል እጅግ ደማቅ በሆነ ሁኔታ ይከበራል፡፡ ከዝማሬውም፥ ከዘፈኑም እየተቀላቀለ፥ ከደመራውም ከገድ ትንበያውም ጋር እየተደባለቀ የመስቀሉ በዓል ይከበራል፡፡ ሽብሸባው ከእስክስታው፥ መብል ከመጠጡ ጋር እየተቀየጠ የመስቀሉ በዓል ይከበራል፡፡ ከሰፈር እስከ ሕዝብ አደባባይ ችቦ እየተለኮሰና፥ ርችት እየተተኮሰ የመስቀሉ በዓል ይከበራል፡፡ በዓሉ ይከበራል፥ የበዓሉ ጌታ ግን ከውስጡ የለም!
የመስቀሉ በዓል ሲከበር ቅርጫው፥ የዘፈን ምርጫው፥ ጭፈራ ዳንኪራው ይጦዛል! በየግሮሰሪው በየቡና ቤቱ ስካር ዘፋኝነት መዳራትና ዝሙት ጣኦትና እርኩሰት ጣራ ላይ ይወጣል! በአሉ ይከበራል፥ የበዓሉ ጌታ ከውስጡ የለም!
ታውቃላችሁ፥ በዓሉ ከጌታው፥ መስቀሉ ከተሰቀለው በልጧል! የመስቀሉ ጌታ ተረስቶ በአሉ ታስቧል፥ ጌታችን ተንቆ መስቀሉ ተከብሯል! ይኼ ከሆነ ዘንዳ፥ መስቀላችን አልተሰቀለም! በዓላችን አልተቀደሰም!
ታውቃላችሁ፥ በመስቀሉ ምክንያት ጠጥተን ከሰከርን፥ በበዓሉ ምክንያት እርኩሰት ከሰራን፥ አዝማሪ አቁመን ዳንኪራ ከረገጥን፥ የመስቀሉን ጌታ ላፍታም ካላሰብን፥ የመስቀሉ ጌታ ከውስጡ ከሌለ ምኑን መስቀል ሆነ? ምኑስ ተከበረ?
ታውቃላችሁ፥ በዓላችን ለኃጢአታችንና ለበደላችን በመስቀል ላይ የተሰቀለውን ጌታ አስረስቶናል! በመስቀሉ ላይ የተደረገልንን የኃጢአት ስርየት ስራ ሸፍኖብናል! የጌታ ፈቃድ ከክርስቶስ ጋር እንድንሰቀል፣ በምድራዊ ሕይወታችን በየዕለቱ በቅድስናና በጽድቅ እንድንኖር መሆኑን ጋርዶብናል!! ከተሰቀለው ጌታ ይልቅ እንጨቱን፥ ከመስቀሉ ስራ ይልቅ በዓሉን እንድናከብር በማሳወር አፍዝዞናል!!!
እናንተዬ፣ ለእውነት እንዳንታዘዝ አዚም ያደረገብን ማነው? የተሰቀለልንን ትተን እንጨቱን እንድንከተል፣ ከመስቀሉ ስራ ይልቅ በዓሉን እንድናከብር ያፈዘዘን ማነው? በመንፈስ ጀምረን በስጋ እንድንፈጽም ያደረገን ማነው? መንፈሳዊውን ስራ ዓለማዊ ያደረነው ምን ሆነን ነው?
(ይህን ዲቮሽን ላይክ ያድርጉ፣ ለወዳጅ ጓደኞችዎም ያስተላልፉ፡፡ ጌታ ይባርክዎ)

No comments:

Post a Comment