ጭንገፋ
... ይጨንግፍ!
ሁለት ሰዎች ቢጣሉ፥ ያረገዘችንም ሴት ልጁን እስክትጨነግፍ ቢገፉአት ባትጐዳ ግን፥ የሴቲቱ ባል የጫነበትን ያህል ካሳ ይስጥ ፈራጆቹም እንደ ፈረዱበት ይክፈል። ጕዳት ግን ቢያገኛት ሕይወት በሕይወት፥ ዓይን በዓይን፥ ጥርስ በጥርስ፥ እጅ በእጅ፥እግር በእግር፥ መቃጠል በመቃጠል፥ ቍስል በቍስል፥ ግርፋት በግርፋት ይከፈል (ዘጸ 21፡22-25)
አንዲት ሴት በደረቷ የአንድ ዓመት ሕጻን ታቅፋ ወደ ሆስፒታል ሄደችና ዶክተሩን ታገኘዋለች፡፡ ለዶክተሩም፣ ይህ የምታየው ሕጻን ገና አንድ ዓመቱ ነው፡፡ እርሱን አሳድጌ ትንሽም ሳላርፍ ሌላ አረገዝኩ፡፡ እኔ ግን እረፍት እፈልጋለሁ፡፡ ስለዚህ ወደዚህ የመጣሁት አዲስ የተጸነሰውን ጽንስ እንድታቋርጥልኝ ነው፡፡ ትለዋለች፡፡
ዶክተሩም ትንሽ አሰበና፣ እንዲህ አላት፡፡ ‹‹እሺ ይህን የታቀፍሽውን ልጅ ልግደልልሽ፣ እርሱ ከሞተ በኋላ አዲሱ ሕጻን እስኪወለድ ድረስ ቢያንስ ትንሽ ታርፊያለሽ፡፡›› ይላታል፡፡ ሴትየዋ በጣም ደንግጣ እየተርበተበተች ‹‹እንዴ! ይኼማ አይሆንም፣ ልጄ እንዲገደልብኝ አልፈልግም!›› ትለዋለች፡፡
ዶክተሩም ቀበል አድርጎ፣ ‹‹በእጅሽ ያለውም ተገደለ፣ በሆድሽ ያለውም ተገደለ፣ ያው ልጅሽ ስለሆነ ምንም ለውጥ የለውም፡፡ ስለዚህ፣ አይዞሽ ይህን የታቀፍሽውን ልጅ ልግደልልሽ›› ይላታል፡፡ ሴትየዋም፣ ‹‹ልጄን አልገድለውም! አልገድለውም!›› እያለች እየተንቀጠቀጠች ተናገረች፡፡
ያኔ ዶክተሩ፣ ‹‹እንግዲያውስ በሆድሽም ያለው ጽንስ ሕይወት ያለው ልጅሽ ስለሆነ ይቅርብሽ፡፡ የተወለደ ልጅ መግደልም ሆነ ያልተወለደ ልጅ መግደል ያው እኩል መግደል ነው›› በማለት ሐሳቧን አስቀይሯታል፡፡
ያልተወለደ ልጅ መግደል፣ የተወለደን ከመግደል እኩል ነው! የተጸነሰውም ነፍስ፣ የተወለደውም ነፍስ ነው፡፡ ነፍስ
ደግሞ በሆድ ውስጥም ይሁን በእቅፍ ያው እኩል ነው፡፡ ነፍስ እስከያዘ ድረስ ሽል ሙሉ የሆነ የሰው ነፍስ ነው፡፡ ይህችው ነፍስ፣
ሰው ሲወለድም፣ ሲያድግም ሲያረጅም ሲጃጅም ሲገፈጅፍም አብራው ትዘልቅና ሲሞት ስጋን ተለይታ ወደ ፈጣሪዋ ትሄዳለች፡፡
ጽንስ ማቋረጥ ማለት
ነፍስ መግደል ነው፡፡ ሆነ ብሎ ነፍስን መግደል ደግሞ ቅጣት አለው፡፡ ያልተወለዱ ሕጻናት በእግዚአብሔር ፊት እንደ ሙሉ ሰው ይታያሉ፡፡
እነዚህ ራቸውን መከላከል የማይችሉ ያልተወለዱ ሕጻናት የእናቲቱን እርዳታ ይሻሉ፡፡ ጤናማ እናት ደግሞ የገዛ ልጇን አትገድልም፡፡
ጤናማ እናት ጽንሷም የሚጎዳ ነገር እንዲኖር አትፈቅድም፡፡
ጽንስን መግደል በእግዚአብሔር
ፊት ከባድ ኃጢአት ነው፡፡ ጽንስን መግደል በብሉይ ኪዳን ሞት የሚያስከትል ኃጢአት ነው፡፡ ከአስርቱ ትዕዛዛት መካከል አንዱ
‹‹አትግደል›› የሚል ነው፡፡ ይህ ሕግ ዛሬም አልተቀየረም፡፡ መግደል
ዛሬም ያው መግደል ነው፡፡ በጌታ በኢየሱስ ስም ጭንገፋ ይጨንግፍ!
ጽንስ የሚያቋርጡ ሰዎች
ለተለያየ የጤና መቃወስ ይጋለጣሉ፡፡ ስነልቦናዊ ቀውስ፣ መንፈሳዊ ድርቀት፣ እና የማህጸን ጤና መታወክ ያጋጥማቸዋል፡፡ ጽንስ ከሚያቋርጡ
ሰዎች መካከል አብላጫው የመካንነት ችግር ያጋጥማቸዋል፡፡
በሐኪም ማስጠንቀቂያ
ካልሆነ በስተቀር፣ በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት ጽንስ የሚያቋርጡ ሰዎች ለከባድ ጸጸት መጋለጣቸው አይቀሬ ነው፡፡ ነገር ግን የክርስቶስ
ደም የማያነጻው ኃጢአት የለምና፣ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ በዚህ አደጋ ላይ የወደቁ ወገኖቻችን ንስሐ ሊገቡ ያስፈልጋል፡፡ በደሙ
ታጥበው፣ ከኃጢአታቸው ሊነጹ፣ ከሚከስሳቸውም የበደለኝነት መንፈስ ነጻ መውጣት ይችላሉ፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስ ደም የማያነጻው ኃጢአት
የለም!
(ይህን ዕለታዊ ዲቮሽን ላይክ እና ሼር ያድርጉ፣ ወዳጅ ጓደኞችዎም እንዲያገኙ ያግዙ፡፡ ዲቮሽኑ ሳይቋረጥ ዓመቱን ሙሉ እንዲቀጥል በጸሎትዎና ጌታ በልብዎ በሚያስቀምጥ ማናቸውም ነገር ሁሉ ይደግፉ፡፡ ላይክና ሼር እንዲያደርጉ የፈለግሁት በሶስት ዓላማዎች ነው፡፡ (1) መልዕክቱ በሁላችንም ኮኔከሽን በኩል በመላው ዓለም ወደሚኖሩ ሐበሾች እንዲዳረስ (2) ጽሁፉ ፖስት በሚደረግባቸው ቀናት እየተከታተሉ በታማኝነት ላይክና ሼር በማድረግ አብረውኝ ለሚተጉና ከፍተኛ ብልጫ ላላቸው 40 ሰዎች ልዩ የሕይወት ዘመን ስጦታ ስላዘጋጀሁ (3) ጽሁፉ ፖስት ከተደረገበት ቀን ጀምሮ ባሉት ተከታታይ 3 ቀናት ውስጥ በታማኝነት ላይክና ሼር በማድረግ በከፍተኛ ብልጫ ላላቸው 100 ሰዎችም ልዩ ስጦታ ስላዘጋጀሁ ነው፡፡ ጌታ ይባርክዎ፡፡)
No comments:
Post a Comment