Saturday, October 4, 2014

አሁን ከሆንለት በላይ እንሁንለት!


ዲቮሽን .9/2007 አርብ፥ መስከረም 9/2007 ..
(
በፓ/ ተስፋሁን ሐጢያ)

አሁን ከሆንለት በላይ እንሁንለት!

የእግዚአብሔር ታቦት ወደ ዳዊት ከተማ ሲገባ፥ የሳኦል ልጅ ሜልኮል በመስኮት ሆና ትመለከት ነበር፡፡ ንጉስ ዳዊት በእግዚአብሔር ፊት ሲዘልልና ሲያሸበሽብ ባየችው ጊዜ በልቧ ናቀችውየእስራኤል ንጉስ በመኳንንቱ ገረዶች ፊት እንደ አንድ ተራ ሰው ራቁቱን መታየቱ ክብሩ ሆኖ ነው¡ (2 ሳሙ 616,20)

አንዳንድ ድርጅቶች ከቀረጥ ነጻ መብት አላቸው፡፡ አንዳንድ ግለሰቦች ደግሞ ያለመከሰስ መብት አላቸው፡፡ ልክ እንደዚሁ፥ በቤተከርስቲያን ውስጥ በብዙ ቦታዎች ላይ እንደሚታየው፥ መሪዎች ያለማምለክ ነጻነት ያላቸው ይመስላል፡፡ ብዙ መሪዎች ያለማሽብሽብ፥ ያለማጨብጨብ፥ ያለመንበርከክ፥ ያለመስገድ ፈቃድ የተሰጣቸው ይመስላል፡፡

የመሪዎቻችን መቀመጫ ከፊት፥ አምልኳቸው ግን ከኋላ ነው፡፡ አንገታቸው በክራባት ስለሚታነቅ፥ ነገረ አምልኳቸው ከአንገት በላይ ነው፡፡ በዝማሬ ጊዜ ከንፈራቸው ይነቃነቃል፥ ድምጽ ግን የለም፡፡ በጭብጨባ ጊዜ እጃቸው ይንቀሳቀሳል፥ ድምጽ ግን የለም፡፡ ፊታቸው ላይ ፈገግታ አለ፥ ደስታ ግን አይታይባቸውም፡፡

ለባለስልጣናትና ለባለሀብቶች ዝቅ ብሎ ለማጎንበስ የማይቸገረው ወገባችን ለአምልኮ ሲሆን ግን ይለግማል፡፡ ከመሪዎች እጅ የሚደመጥ ጭብጨባ የሚወጣው ቃለጉባኤ ሲጽድቅ ብቻ ይመስላል፡፡ መሪዎች ማዕረጋቸውንና ደረጃቸውን በሚያሳብቁ ልብሶች ተጀቡነው ወደ ቤተክርስቲያን ስለሚገቡ፥ እንደ ልባቸው መሆን አይችሉም፡፡ በአጠቃላይ ማለት ይቻላል፥ መሪዎች በአምልኮ ጊዜ ሲኮፈሱ ይስተዋላል፡፡

የገባቸው መሪዎች ደግሞ አሉ! እንደ ንጉሱ ዳዊት በአምልኮ ላይ ቀልድ የማያውቁ፥ ባላቸው ስልጣን የማይኮፈሱ፥ በማዕረጋቸው የማይጎርሩ፥ በእውቀታቸው የማይመኩ፥ በይሉኝታ የማይታሰሩአሉ! ክብራቸውን ጥለው፥ ማዕረጋቸውን ረስተው፥ ሁሉን ትተው ጌታን የሚያመልኩና የተረዱ መሪዎች አሉ፡፡ ለሽብሽባ የማያፍሩ፥ ለጭብጨባ የማይራሩ፥ ለጭፈራ የማይፈሩ፥ አሉ፡፡ የእውቀታቸውን ምንጭ፥ የክብራቸውን ሰጪ፥ የማዕረጋቸውን ምስጢር፥ የኑሮቸውን ማግና ድርያውቁታል፡፡

የተደረገላቸውን የሚያውቁ፥ የሆነላቸውን የተረዱ ጌታን ለማምለክ አይቸገሩም፡፡ "እባካችሁን እስኪ አጨብጭቡ፥ እስኪ አንዴ እልል በሉ፥ በናታችሁ አሸብሽቡ፥ ውጡ፥ ውረዱ፥ ያዙ፥ ልቀቁ" አይባሉም! ገብቷቸዋላ!

(ይህን ዕለታዊ ዲቮሽን ላይክ ያድርጉ፥ ለወዳጅ ጓደኞችዎም ያስተላልፉ)

No comments:

Post a Comment